Site icon ETHIO12.COM

በጋምቤላ ፓርክ ነጭ ጆሮ ቆርኬዎችና ዝሆኖች በህገወጦች እየታደኑ ነው

በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በሚገኙ እንስሳት ላይ ከፍተኛ ህገ ወጥ አደን እየተካሄደ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ “በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የብዝሃ ህይወት ሀብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ያስፈልጋል” ብሏል።

በፓርኩ በሚገኙ የእንስሳት ሀብት ላይ ከፍተኛ ህገ ወጥ አደን እየተካሄደ መሆኑን የተናገሩት የፓርኩ ጽህፈት ቤት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሄኖከ ታምሩ፤ “በተለይም የነጭ ጆሮ ቆርኪ እና ዝሆኖች ላይ ከፍተኛ አደን እየተካሄደ ነው” ብለዋል።

በዘንድሮ ዓመት ብቻ አምስት ዝሆኖችም መገደላቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። “ችግሩን ለመከላከል ጥረት እየተደገ ቢሆንም የተፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም” ብለዋል።

የቀድሞ የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የአሁኑ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋልዋክ ኮርት “ቀደም ሲል በፓርኩ ከ550 በላይ ዝሆኖችና ከ1 ሚሊዮን የሚበልጡ የነጭ ጆሮ ቆርኪዎች ነበሩ” ሲሉ አስታውሰዋል።

የዝሆኖችም ሆነ የነጭ ጆሮ ቆርኪና የሌሎች እንስሳት ቁጥር እየቀነሰ እንደሚገኝ አመልክተው፤ “በፓርኩ ብዝሃ ህይወት ሀብት ላይ ተደቅኖ ያለውን ችግር ለመከላከል ሁሉም ሊሰራ ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ በፓርኩ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለማቃለል ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አመላክተዋል።

የፓርኩን ወሰን ግምት ውስጥ ያላስገባ የግብርና ኢንቨስትመንት፣ ህገ ወጥ ሰፈራን፣ አደንና ሌሎች ድንበር ዘለል የአርብቶ አደሮች ጥቃት በመከላከል ረገድ ቢሮው በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በፓርኩ ላይ እየደረሱ ያሉትን ድንበር ዘለልና ውስጣዊ ተጽዕኖዎች ለመከላከልና የባለድርሻ አካላትን አጋርነት ለማጠናከር የንቅናቄ ስራዎችን እያካሄደ ነው።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ  ፓርኩ በእንስሳት ፍሰቱ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ከሚታወቀው የሰረንጌቲ ፓርክ ቀጥሎ ተጠቃሽ ቢሆንም በሀብቱ ልክ ለምቶ ጥቅም እየሰጠ አይደለም ብለዋል።

በፓርኩ ላይ እየደረሱ ያሉትን ተጽዕኖዎች በመከላከል ሀብቱን ለኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል እየተደረገ ላለው ጥረት በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራር አካላትና የማህበረሰቡ የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በ1960 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ባለው 4 ሺህ 575 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ውስጥ 69 የአጥቢ፣ 327 አዕዋፍ፣ ሰባት የተሳቢ እንስሳትና 493 የእጽዋት ዝርያዎች ይገኙበታል ሲል የዘገበው ፋና ነው

Exit mobile version