ETHIO12.COM

የዓለም ምግብ ፕሮግራም 400 ሚሊዮን ዶላር መድቦ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት እንደሚያቀርብ አስታወቀ።

በመቀሌ የምግብ ማከማቻ መጋዘን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ለሁለት ወራት መመገብ የሚያስችል እህል መከማቸቱን መንግስት አስታውቋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ዴቪድ ቤስሊን፣ በተባበሩት መንግስታት የሠብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚና የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ዛሬ በመቀሌ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎችና የድጋፍ አሰጣጡን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ዳይሬክተሩ ሚስተር ዴቪድ በትግራይ ክልል ከተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ የሠብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ የተለያዩ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቦታው ተገኝተው የሠብዓዊ ድጋፍ አሰጣጡን መመልከታቸውንና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ማነጋገራቸውን ተናግረዋል።

ሠብዓዊ ድጋፉን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለማዳረስ የመገናኛ አውታሮች ሁሌም ክፍት ሊሆኑና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሊቀላጠፍ ይገባልም ብለዋል።

ተቋማቸው በክልሉ እየተደረገ ያለውን የሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እየደገፈ መሆኑንና በተለይም ከውጭ ተገዝተው የሚመጡ የምግብ እህሎች ከጅቡቲ ወደ መቀሌ በቀላሉ እንዲጓጓዙ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በትግራይ ክልል በርካታ ዜጎች የዕለት ደራሽ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ መንግስት ሁሉንም ማዳረስ አዳጋች ስለሚሆንበት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በርካታ ህጻናትና እናቶችም የአልሚ ምግብ ድጋፍ የሚሹ በመሆኑ ይህም በስፋት ሊዳረስ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ መንግስት የክሊራንስና ሎሎች ህጋዊ ጉዳዮችን ሊያመቻች ይገባል ነው ያሉት።

የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው መንግስት በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ከተባበሩት መንግስታትና ከሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር እያደረሰ ነው ብለዋል።

መቀሌ በሚገኘው መጠባበቂያ ምግብ ክምችት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ለሁለት ወራት የሚበቃ የምግብ ክምችት መኖሩን አስታውቀዋል።

የሠብዓዊ ድጋፍ ስርጭቱን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና በ24 ወረዳዎች፤ ማህበረ ረድኤት ትግራይ ደግሞ በቀሪዎቹ 12 ወረዳዎች እያሰራጩ መሆኑ ተገልጿል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም 400 ሚሊዮን ዶላር መድቦ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን የዕለት እርዳታ የሚሹ ዜጎች ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

FBC

Exit mobile version