Site icon ETHIO12.COM

በሑመራ ከተማ ትምህርት ተጀመረ፡፡

ዛሬ በሑመራ ከተማ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መደበኛ የመማር ማስተማር መጀመሩን የከተማዋ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ በሕግ ማስከበር ሂደቱ ከተማዋ ከጥፋት ኃይሎች ነፃ ከወጣች በኋላ ማኅበረሰቡ ልጆቹን ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ተደጋጋሚ ጥያቄ ማንሳታቸውን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራ አስፈፃሚ አባል በሪሁን እያሱ ተናግረዋል፡፡ ይሕንን ተከትሎም በከተማዋ ትምህርት ለማስጀመር ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን አስታውቀዋል፡፡

አቶ በሪሁን እንዳሉት በትምህርት ቤቶች የነበሩ ችግሮችን በመለዬት ቁሳቁስ እንዲሟሉ ተደርጓል፤ መምሕራንን በማሟላትም ደመወዝ እስከመክፈል ተደርሷል፡፡ በመሆኑም ዛሬ በአምስት ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥትም ባለሙያዎችን በመመደብ፣ መምሕራንን በማሟላትና ማኅበረሰቡን በማወያዬት ትምህርት ቤቶችን መልሶ በማደራጀት ሥራው ስኬታማ እንዲሆን ደግፏል ብለዋል፡፡ አሁንም ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ነው አቶ በሪሁን ያስታወቁት፡፡

የሥራ አስፈጻሚ አባሉ እንዳሉት በሑመራ ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ከተጀመረ ሳምንት አልፎታል፤ ተማሪዎች ጥሩ የመማር ፍላጎትና ተነሳሽነት እንዳላቸውም ተስተውሏል፡፡

በሕግ ማስከበር ሂደቱ ምክንያት ዘግይቶ የተጀመረውን ትምህርት ለማካካስ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ የትምህርት ክፍለ ጊዜን ረዘም ለማድረግ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ እንደ ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ የሑመራ ከተማ ነዋሪዎች ላለፉት 30 ዓመታት ያለማንነታቸው ማንነት ተሰጥቷቸው ሲጨቆኑ ቆይተው ነበር፤ ባሕላቸውን እንዳያሳድጉ፣ በቋንቋቸው እንዳይዳኙና በፍላጎታቸው እንዳይተዳደሩ በመደረጋቸውም ከፍተኛ ማኅበራዊና ሥነልቦናዊ ጫና ውስጥ ገብተዋል፡፡

በአማራ ክልል ልዩ ኃይልና መደበኛ ሚሊሻ እንዲሁም በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አካባቢው ነጻ ከወጣ በኋላ ግን በነጻነት መደበኛ እንቅስቃሴ ተጀምሮ የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛል ብለዋል፡፡ መማር ማስተማሩ ያለምንም ችግር እንዲቀጥል በቂ ኃይል መሠማራቱንም አቶ በሪሁን አረጋግጠዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ (አብመድ)

Exit mobile version