ETHIO12.COM

ትግራይን እንደ ማይናማር!

ኘሮጀክቱ የግብፅን ፍላጎት ለማሳካት በሰብአዊ ድጋፍ ስም የሚካሄድ ሴራ ሊሆንም ይችላል። ግብፅ ደግሞ ከኢትዮጵያ የተሻለች የአሜሪካ ስትራቴጂክ ወዳጅ መሆኗንም መርሳት አያስፈልግም። ሱዳንም በኢትዮጵያ ላይ የታቀደውን እቅድ ማስፈፀምያ መሳርያ ነች። ህውሃትም ነብሷን አይማራትና በመጨረሻ አጣብቂኝ ውስጥ ስትገባ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በህቡዕ ያልተቀደሰ ጋብቻም ፈፅማ እንደ ነበር ይታወሳል። ስለሆነም ይህ ጉዳይ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋም ሃላፊነት ይሆናል ማለት ነው።የሃገር ሉዓላዊነት ከፓለቲካ ርዕዮት የላቀ ነውና!

በላይ ባይሳ


የሰሞኑን የተመድ የደህንነት ምክር-ቤት አባላት ውዝግብ ሳይ የማይናማርን የፖለቲካ ሁኔታ አስታወሰኝ። በእርግጥ የሁለቱም መነሻ እና መሠረታዊ ምክንያቶች ቢለያይም ሂደታቸው ላይ ግን መጠነኛ የቅርፅና የይዘት ተመሳስሎ ተስተውሏል።ምክንያቱ ደግሞ ምንም ይሁን ምን ሁለቱም በአግባቡ ካልተያዙ ለፖለቲካ ጡዘት እንደ ቤንዚን ሆነው ያገለግላሉ። አቅጣጫውንም ያስቱታል። ከሌሎች ገፊ ምክንያቶች ጋር ተዳምረው ከውስጥም አልፈው የሃገርን ሉዓላዊነት እስከ-መፈታተን ይደርሳሉና።የማይናማር አለመረጋጋት ለዘመናት ሲንከባለል የመጣ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ ችግሩን ካወሳሰቡት ብዙ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በውስጥ ጉዳያቸው ላይ በሰብአዊ ስራዎች ስም ከውጪ ጣልቃ ለመግባት የሚደረገው ፍላጎት እና ትንቅንቅ ነው።

በተመሳሳይ ወደኛ ሃገር ጉዳይ ስንመለስ የተመድ የደህንነት ምክር-ቤት አባላት የሁለት ጎራ ውዝግብም በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ያለውን ፍላጎት ያሳየ ነው።አሜሪካም ሆነች አብዛኞቹ ምዕራባውያን ደግሞ በዓለም ላይ መንታ ስታንዳርድ የፖለቲካ አካሄድ እንደሚከተሉ እሙን ነው።በተለይ ደግሞ አሜሪካ የራሷን ጥቅም እስካስጠበቀ ድረስ ከሰማይ በታች የማትፈነቅለው ድንጋይ፤ የማትቆፍረው ጉድጓድ፣ የማትገነባው ግንብ አይኖርም። ሃያሏ በቀኝ እጇ የአንድን ሃገር መንግስት በአደባባይ ትደግፍና በግራ እጇ ደግሞ በስውር የዛኑ ሃገር አማፂ ቡድን ልትረዳ/ልታስታጥቅ ትችላለች።የሁለቱም ስታንዳርድ መዳረሻው ደግሞ አንድ ነው። እሱም፦ “የአሜሪካንን ጥቅም ማረጋገጥ” ብቻ ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ የሚከሰት ሰብአዊ አደጋ፣ የፓለቲካ ስንጥቃት፣ ማህበራዊ መናጋትም ሆነ የህግ ጥሰቶች የአሜሪካንን ጥቅም እስካስጠበቀ ወይም እስካልጎዳ ድረስ ቁብ አይሰጣትም።ከዚህ አንፃር በትግራይ ያለውን ሁኔታ በተለያየ ደረጃ ከፋፍሎ ማየቱ ተገቢ ይመስለኛል።

1ኛ. የህግን የበላይነት ከማስከበር እና ሃገሪቷ ያጋጠማትን የህልውና አደጋ ከመቀልበስ አንፃር ስለተሰራው ስራለያዥ ለገናዥ ያስቸገረችው ህውሃት የመጨረሻ የአደባባይ ላይ ክህደት የፈፀመችው፣ ታሪካዊና የማይታረም ስህተት የሰራችውና ግብዓተ-መሬቷ ተፋጥኖ የተፈፀመው፦ አልመከር፣ አልዘከር፣ አልለመን፣ አልሸመገል ብላ በጥጋብ ተነርታ በስተመጨረሻም የማይነካውን እሳት ስለነካች ነው። እጅግ ከልክ ያለፈ ትዕግስትን ንቃ፣ ምህረትን ረግጣ፣ ኢትዮጵያን ገፍታለች። ያለኔ ወጡም ሆነ ለውጡ አይጣፍጥም ብላ በነውጥ አስደልቃለች፣ ዝታለች፣ ፎክራለች። ከዚህ አንፃር እንግዲህ በትግራይ ለተደረገው ሃገርን የማዳን ተልዕኮ ያልተገባ ውግዘትና ክስ ማቅረብ ሚዛናዊነትን ከማያውቁ በውጪም በውስጥም ካሉ ልዳዊያን፣ ጁንታውያንና ኢንጁዋዊያን በስተቀረ ለምን? ለሚል አካል መልሱ ቀላል ይመስለኛል።በነገራችን ላይ ለሃገር ብዙ ማበርከት ይችሉ የነበሩ ነገር ግን በጁንታው ኘሮፖጋንዳ ተማርከውና ተታለው የፋሲካ ዶሮ የሆኑት ግን እጅግ ያሳዝናሉ።

2ኛ. ህግን ከማስከበር ተልዕኮው ጋር ተያይዞ ከተከሰተው ሰብአዊ አደጋ ምላሽ አንፃርእንኳን ጦርነት ተካሂዶ አንድ ቀን ስራ ቢያቆም የሚላስ የሚቀመስ የሌለው ነው-የኢትዮጵያ ህዝብ። በተመሳሳይ ተነፍቶ የነበረውን ፊኛ በማስተንፈስ ሂደት ውስጥ ደግሞ ምንም አይነት ሰብዓዊ ችግሮች አይከሰትም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። የተነፈሰው ፊኛ ደግሞ እጁም ሆነ ስሩ እጅግ የረዘመና ወደውስጥም ሆነ ወደ ውጪ ያደገ እንደነበር መርሳትም አያስፈልግም። ከዚህ አንፃር የአሌክስ አብርሃ ትችት እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት እና የኢትዮጵያ ህዝብ ለትግራይ ህዝብ ከሰላም ማስከበሩ ማግስት የሚቻላቸውን ሰብአዊ ድጋፍና እርዳታም ማድረጋቸው አይዘነጋም። ይህ ተግባር መጠናከር ይገባዋል።ነገር ግን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ዜጎች እንዳይጎዱና ወደ-መደበኛ የለት-ተዕለት ኑሮዋቸው እንዲመለሱ ለማስቻል በትጋት ሊሰራ ይገባዋል። ዓለም-ዓቀፍ የእርዳታ ተቋማትም ችግሩን ከመቅረፍ ረገድ የራሳቸውን አበርክቶ እንዲያደርጉና ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ (በሰብአዊ ድጋፍ ስም ሊሰራ የሚችልን ሸፍጥ በአይነ ቁራኛ በመከታተል) ሁኔታዎችን በማመቻቸት አጠናክሮ መስራት ተገቢ ነው።ህዝቡን ከህውሃት ቀምበር ስር “ነፃ ለማውጣት” በሚሰራው ስራም ሌላ ጭቆና እንዳይኖር ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባዋል።

3ኛ. “የኤርትራ ወታደሮች ኢትዮጵያ ገብተዋል” እንዲሁም “የአማራ ልዩ ሃይል ከትግራይ ክልል ለቆ ይውጣ” የሚለው ጉዳይ ላይ ግልፅ የሆነ መረጃ ያለመኖሩ ፈተና ሆኗል። በዚህ አጀንዳ ላይ የኤርትራ ወታደርም ሆነ የአማራ ልዩ ሃይል ትግራይ ስለመኖሩ ወይም አለመኖሩ ከሁሉም አካላት የሚወጡ መረጃዎች የተምታታ፣ የተዘበራረቀና ግልፅነት የጎደለው ነው።ይሁንና ሁለቱም ሃይሎች በክልሉ ውስጥ የመንቀሳቀስ ምንም አይነት ምክንያትና ህጋዊ መሠረት ስለሌላቸው እውነት በክልሉ ውስጥ ካሉ በአስቸኳይ መውጣት አለባቸው። ይሄንን ለማድረግም የተመድን ተግሳፅ መጠበቅ የለበትም። እውነት ከሆነም መንግስትም ይሄንን እንደ ሂስ ተቀብሎ ማስተባበል ይኖርበታል። ሁለቱም አካላት በስፍራው ሳይኖሩ እንዲሁ በሃይ-ኮፒ (high-Copy) የሚወራና ያልተገባ ምስል እንዲያዝ በተለይም ከሰብአዊ መብት ጥሰተቶች አንፃር የሚያስወራም ሆነ የሚሰራ አካል ካለ ውሸት ስለመሆኑ የተደራጀና የተሟላ መረጃ ለህዝቡም ሆነ ለዓለም ማህበረሰብ ሊሰጥ ይገባዋል። ደባውንም ማጋለጥ ይኖርበታል።”ርስቴ ነው! ድንበሬ ነው!” ወዘተ… የሚለው ህገወጥ አካሄድም በህጋዊ መንገድ እልባት እስኪሰጠው ድረስ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት አይኖረውም።በክልሉ ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፓሊስ በትኩረት እና በከፍተኛ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ተልዕኮዋቸውን እንደሚፈፅሙ ይታመናል።

4ኛ. በህውሃት መጥፍት ጥቅማቸው የቆመ ዓለማቀፍ “የሚድያ” ተቋማትና በቡኒ ፖስታ (Brawn envelope) የደለበ ቡጬ የለመዱ “ጋዜጠኞች” ጩኸት ህውሃት የሚድያን ሃያልነት ቀድማ በመረዳት እንደዚህ አይነት የጭንቅ ቀን ሲመጣ እንደ መውጫ እና ማምለጫ ለመጠቀም ብሎም የዓለማቀፍ ማህበረሰብን ሆን ብሎ በውሸት ለማሳመን ለረዥም አመታት እጇን አስረዝማ ስትሰራ እንደነበር አብይ ማስረጃ ነው።ከዚህ አንፃር ሚዛናዊነት የጎደላቸው እና ወደ አንድ ጎራ ያጋደሉ ዘገባዎችን “ጋዜጠኞቹ” ሲያሰራጩ ማየት የጥቅም ተጋሪነትና ትስስሩን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ምን አይነት ኮራብትድ የሆነ ዓለማቀፍ መረብ/መዋቅር ተዘርግቶ እንደነበር እንዲሁም በሌሎች ሴክተሮችም ይህን መሰል መድልኦ ስለመኖሩ መገመት አያዳግትም።ይህ አጋጣሚ ከህዳሴው ግድብ መሞላት ሂደት ጋር ተዳምሮ የሃገሪቱን የውጪ ግንኙነት ስራዎችን የፈተነ ብቻ ሳይሆን በየሃገሩ ያሉትን የመንግስት ምስለኔዎች ሚናና ችሎታም ጥያቄ ውስጥ ያስገባ እንደነበር ልብ ይለዋል። እንደ መንግስት የኮሚዩኒኬሽንን ስራ በአጀንዳ ትኩረት አድርጎ በስትራቴጂ የሚሰራ መዋቅር አለመኖሩም ሌላ እንደ ክፍተት የታየ ጉዳይ ነው።

5ኛ. ኢትዮጵያ እንደሃገር እንዳትቀጥል ውስጣዊ እና ውጫዊ ከፍተኛ ተግዳሮቶችኢትዮጵያ እንደሃገር እንዳትቀጥል ካለው ውስጣዊ እና ውጫዊ ከፍተኛ ፍላጎት የነበረ፣ ያለና የሚኖር እንዲሁም በተለይ ደግሞ አሁን ላይ ግፊቱ የጨመረና ከፍተኛ መሆኑን መረዳት ተገቢ ይሆናል።ታሪክ የሚያሳየውም ደግሞ ኢትዮጵያ የውስጥና የውጪ ጠላቶቿን አንገት አስደፍታ በትውልድ ቅብብሎሽ በጀግኖች ልጆቿ ደምና አጥንት የተገነባች ሃገር መሆኗንም ማስረገጥ ተገቢ ይሆናል። ለዚህ አድዋ ህያው ምስክር ነው።

6ኛ. መሠረተ-ልማትን ማፈራረስ እና የዲያስፖራው ፍትሃዊነት የጎደለው ጬኸት ሃገርን የመዝረፍ ኘሮጀክት መምከንን እና ለትግራይ ህዝብ ያለማሰብን በተጨባጭ ማሳያ ጭምር ክስተት ነው። የመሰረተ-ልማት አውታሮችን መልሶ ማቋቋምና የመጠገን ስራም ትኩረትና ቅንጅት የሚሻው ጉዳይ ነው። ብዙ መዋዕለ-ነዋይ/ሃብትም የሚፈልግ መሆኑ እሙን ነው።

ሲጠቃለል በትግራይ ክልል ስም እንደ ምክንያት ሆኖ በአሜሪካም ሆነ በሌሎች ሃገሮች በ”ሰብአዊ ድጋፍ” እና “የኤርትራ ወታደር/የአማራ ልዩ ሃይል ከትግራይ ይውጣ” በሚል ድምፀት ነገር ግን በእጅ አዙር ሉዓላዊ በሆነች ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባትና የሃገርን ህልውና ለመፈታተን የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የለውም። ተገቢም አይደለም።

ኘሮጀክቱ የግብፅን ፍላጎት ለማሳካት በሰብአዊ ድጋፍ ስም የሚካሄድ ሴራ ሊሆንም ይችላል። ግብፅ ደግሞ ከኢትዮጵያ የተሻለች የአሜሪካ ስትራቴጂክ ወዳጅ መሆኗንም መርሳት አያስፈልግም። ሱዳንም በኢትዮጵያ ላይ የታቀደውን እቅድ ማስፈፀምያ መሳርያ ነች። ህውሃትም ነብሷን አይማራትና በመጨረሻ አጣብቂኝ ውስጥ ስትገባ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በህቡዕ ያልተቀደሰ ጋብቻም ፈፅማ እንደ ነበር ይታወሳል። ስለሆነም ይህ ጉዳይ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ዜጋም ሃላፊነት ይሆናል ማለት ነው።የሃገር ሉዓላዊነት ከፓለቲካ ርዕዮት የላቀ ነውና!

በላይ ባይሳ የካቲት 21/2013 ዓ.ም

Exit mobile version