Site icon ETHIO12.COM

“ጁንታው የሚደበቅበትና መከላከያ የማይደርስበት የኢትዮጵያ ምድር የለም” ሲሉ ጄ/ባጫ ቀኑ ሳያልቅ እጅ ስጡ ሲሉ ጥሪ አቀረቡ

ሸፍተው የሚገኙ የጁንታው ቀሪ አመራሮች መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥሪ በመቀበል እጃቸውን በሠላም እንዲሰጡ በመከላከያ ሚኒስቴር የሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ ጥሪ አቀረቡ።ብላቴ የሚገኘው የልዩ ዘመቻዎች ሃይል ማሰልጠኛ ማዕከል 12ኛ ዙር አየር ወለድ ብርጌድና የ34ኛ ዙር ኮማንዶ አባላት ትናንት በተረቁበት ሥነ-ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ እንደተናገሩት፤ የወራት ዕድሜ የማይኖረው የጁንታው ርዝራዥ በመደበኛ ውጊያ ያልቻለውን በሽምቅ ውጊያ ትግራይን ነፃ አውጥቼ አዲስ አበባ እገባለሁ እያለ ነው።

ህዝብን ለማደናገር የሽምቅ ውጊያ እያካሄድን ነው በማለት በኩንቱ እየተውተረተረ መሆኑንም ገልጸዋል።ቡድኑ በትግራይ ውስጥ ቆመንልሀል የሚሉትን ህዝብ እየገደሉና የሚላክለትን የእርዳታ እህልና መድሀኒት እየዘረፉ መከራውን እያበዙበት እንደሚገኙ ጠቅሰዋል። “ጁንታው የሚደበቅበትና መከላከያ የማይደርስበት የኢትዮጵያ ምድር የለም” ያሉት ሌተናል ጀኔራሉ፤ “መንግስት ያቀረበላቸውን ጥሪ በመቀበል እጃችሁን በሠላም በመስጠት ለእናንተና እያሰቃያችሁት ላለው ህዝብ እፎይታ እንድትሰጡት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል” ብለዋል።

የ34ኛ ዙር ኮማንዶ አባላት ትናንት በተረቁበት ሥነ-ሥርዓት

“ይህ ሣይሆን ቢቀርና በሽፍትነት እንቀጥላለን ብትሉ ከፍተኛውን ቅጣት የምትቀበሉ አለያም እንደ ጓደኞቻችሁ ባላችሁበትና በተደበቃችሁት ጎሬ የምትደመሰሱ ይሆናል” ሲሉ አስታውቀዋል።ተመራቂ የኮማንዶና አየር ወለድ አባላትም የኢትዮጵያ ህዝብ መከታና እምነት የተጣለባቸው በመሆኑ በታማኝነትና ቅንነት ለማገልገል ዝግጁ እንዲሆኑ ሌተናል ጀኔራል ባጫ አሳስበዋል።የልዩ ዘመቻዎች ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ በበኩላቸው የመከላከያ ሰራዊት የአቅም ግንባታ ግብ በሁሉም የውጊያ አውዶች መፋለም የሚችል ጠንካራ ሃይል ማፍራት መሆኑን ገልጸዋል።

ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅት በህዝቦች ሠላምና ደህንነት ላይ በየትኛውም አቅጣጫ ሊቃጣ የሚችለውን የጠላት ጥቃት ለመመከትና ለማንበርከክ ዝግጁ እንደሆነም አስታውቀዋል።የልዩ ዘመቻዎች ሃይል ማሰልጠኛ ማዕከል ተወካይ ኮሮኔል ተዝገራ ከበደ ለስድስት ወራት የተሰጠውን ፈታኝና ውስብስብ የኮማንዶና አየር ወለድ ስልጠና በታላቅ ወኔ፣ ጀግንነትና ጽናት ላጠናቀቁ ተራቂዎች የ‘እንኳን ደስ አላችሁ’ መልዕክት አስተላልፈዋል።ከዕለቱ ተመራቂዎችም ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በስልጠና የቀሰሙትን ትምህርት በመጠቀም በማንኛውም ግዳጅ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version