Site icon ETHIO12.COM

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ በሚጥሡ ሰዎች እና ድርጅቶች ላይ ከመጋቢት 20 ጀምሮ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ


መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር እና አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እና በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል የሚረዱ አስገዳጅ እርምጃዎችን እና ግዴተዎችን የሚጥለውን መመሪያ ቁጥር 30/2013 በሚተላለፉ ሰዎች ላይ የወንጀል ህጉን መሰረት አድርጎ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በዚሁ መግለጫ ላይ ተገልጿል፡፡

እርምጃውን ለመውሰድ ምክንያት የሆነው በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ አስገዳጅ የጥንቃቄ ዘዴዎችን ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆን፣ በተለይም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ያለማድረግ፣ ተቀራርቦ ወይም ተጠጋግቶ መቆም ወይም መቀመጥ፣ የእጅ ንጽህናን አለመጠበቅ እና በተቋማትም ደረጃ ማስክ ላላደረገ ሰው አገልግሎት መስጠት፣ ተገልጋዮች ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ያለማድረግ እና መሰል በመመሪያው የተከለከሉ ተግባራትን እና የተጣሉ ግዴታዎችን የሚጥሱ ሰዎች እና ድርጅቶች በመበራከታቸው እና ለስርጭቱ መንስዔ እየሆኑ በመምጣታቸው ነው፡፡

በመሆኑም ማንኛውም ሰው ከቤቱ ውጭ ማስክ ሳያደርግ መንቀሳቀስን እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ያለመጠጋጋት፣ የእጅን ንጽህና በመጠበቅ የህግ አስከባሪዎችን እንዲተባበር የተጠየቀ ሲሆን የመንግስትም ሆነ የግል ድርጅቶችም በመመሪያው የተጣለባቸውን ግዴታ በመወጣት የስርጭቱን መጠን ለመቀነስ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠይቋል፡፡

ይሁንና ይህን በሚተላለፉ ሰዎች ላይ ፖሊስ የህዝቡን ጤንነት ለመጠበቅ ሲል እንደ ሕግ ጥሰቱ ክብደት አጥፊዎችን ከመምከር እና ገደቡን እንዲያሟሉ ከማስገደድ ጀምሮ የወንጀል ምርመራ እስከመጀመር ሊደርስ የሚችል እርምጃ እንዲወስድ የሥራ መመሪያ የተሰጠው በመሆኑ ግዴታውን ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሆኖም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አዲስ መመሪያ ወጥቷል በሚል የተዘገበው ዘገባ ትክክል አለመሆኑን እየገለጽን መመሪያውን በተቀናጀ ሁኔታ የማስፈጸም ስራው አሁን ይጀመር እንጂ መመሪያው ከወጣ 5 ወራት ያለፉት መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

መግለጫውን የሰጡት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ፣ የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ጥናት ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ በላይሁን ይርጋ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር መንገሻ ሞላ ናቸው፡፡

Exit mobile version