በታመነ ህቦሮ – የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ

• በ1996 ዓ.ም ስራ ላይ የዋለው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 346 መሰረት የውጭ ምንዛሪ ያለፈቃድ መያዝ የሚያቀጣ ድርጊት ስለመሆኑ ተደንግጓል፡፡

• የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር FXD/49/2017 አንቀጽ 3 መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ ነዋሪ የሆነ ሰው የውጭ ምንዛሪ ካገኘበት ወይም ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ለጉምሩክ ኮሚሽን ካሳወቀበት ቀን ጀምሮ ባሉት በሰላሳ ቀናት ውስጥ በባንኮች ወይም በህግ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት እንዲሰጡ በተፈቀደላቸው ተቋማት ቀርቦ ማስመንዘር እንዳለበት እንዲሁም በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ማንኛውም ሰው የውጭ ምንዛሬ መያዝ የሚችለው ቪዛው ጸንቶ የሚቆይበት ጊዜ እስከሚጠናቀቅ ጊዜ ድረስ ብቻ እንደሆነ ተቀምጧል፡፡

• በተሻሻለው የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 አንቀጽ 26 (1) (መ) መሰረት ይህን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው በመመሪያው መሰረት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡

• መመሪያው አንቀጽ 6 ላይ የዚህን መመሪያ ድንጋጌዎችን የተላለፈ ማንኛውም ወንጀል የሰራበት ሀብት መወረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀል ህጉ መሰረት ይቀጣል ሲል በህግ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

መንግስት የውጭ ሀገር ገንዘብ ቁጥጥር ማድረግ ያስፈለገበት ዓላማ ለአገራችን ኢኮኖሚ ልማት የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ምጣኔ እና ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት አስፈለጊ በመሆኑ እንደሆነ ከአዋጅ ቁጥር 591/2000 መረዳት ይቻላል፡፡

በዚህም መሰረት ቀደም ብሎ በ 1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግም ሆነ እርሱን ተከትለው በ2000 ዓ.ም በወጣው አዋጅ እና 2009 ዓ.ም እንዲሁም 2013 ዓ.ም በወጡ መመሪያዎች መሰረት መያዝ የተከለከለው የውጭ አገር ገንዘብ መጠን ስላልተቀመጠ ሰዎች የያዙት የውጭ ምንዛሪ መጠን አነስተኛም ሆነ ብዛት ያለው ቢሆን በወንጀል ተጠያቂ ናቸው፡፡ በዚህም አግባብ ማንኛውም መጠን ያለውን የውጭ አገር ገንዘብ በያዙት ሰዎች ላይ የወንጀል ክስ እየቀረበ እና እየተቀጡ ይገኛሉ፡፡

ሆኖም አነስተኛ መጠን ያላቸው የውጭ ሀገር ገንዘብ ይዘው በሚገኙ ሰዎች የወንጀል ክስ ማቅረብ የዐቃቤ ህግን ሆነ የፍ/ቤት ጊዜን እና የመንግስት ሀብት የሚያባክን በመሆኑ እስከ 100 የአሜሪካን ዶላር ወይም ተመሳሳይ የምንዛሬ ዋጋ ያላቸው ሌሎች የውጭ ሀገር ገንዘቦች ይዘው በሚገኙ ሰዎች የገንዘቡ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ የወንጀል ክስ ማቅረብ ቀሪ እንዲደረግ አቅጣጫ እንዲሰጥ ይህንን ስራ የሚከታተለው የስራ ክፍል ለክቡር ሚኒስትሩ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ጥያቄው ተቀባይነት አግኝቶ እስከ 100 የአሜርካን ዶለር ወይም ተመሳሳይ የምንዛሬ ዋጋ ያላቸውን ሌሎች የውጭ ሀገር ገንዘቦች ይዘው በሚገኙ ሰዎች የገንዘቡ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ የወንጀል ክስ ማቅረብ ቀሪ እንዲደረግ መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

ይህ አቅጣጫ/ውሳኔ እስከ 100 የአሜርካን ዶላር ወይም ተመሳሳይ የምንዛሬ ዋጋ ያላቸው ሌሎች የውጭ ሀገር ገንዘቦችን ይዘው በሚገኙ ሰዎች የወንጀል ክስ ሲቀርብ ከላይ የተገለጸውን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የተቀመጠውን ዓላማ ከማሳካት አንጻር ፋይዳ የሌለው መሆኑን እና ጉዳዩን ተከታትሎ የመጨራሻ ውሳኔ ለማሰጠት እና ውሳኔውን ለማስፈጸም በዐቃቤ ህግ ተቋም፣ በፍርድ ቤት እና በማረሚያ ቤት የሚወጠው የመንግስት ሀብት፣ የሰው ሀይል እና ጊዜ የሚባክን መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

ሆኖም በዚህ ውሳኔ መሰረት የተቀሰውን መጠን የውጭ ሀገር ገንዘብ በያዙ ሰዎች ላይ የወንጀል ክስ የማይቀርብ ቢሆንም ከፍ ሲል በተጠቀሱት ድንጋጌዎች መሰረት ገንዘቡ የሚወረስ መሆኑ እንደተጠበቀ ነው፡፡
ታመነ ህቦሮ
የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ

Via attorney general

Leave a Reply