Site icon ETHIO12.COM

ማንነት ሲማሰል – ” … መስማማት ውዴታ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው”

በአሜሪካ የጀመረው የኢንደስትሪ አብዮት በተቀጣጠለበት ወቅት ከፍተኛ ሰዎችን ማሳተፍ የሚችል የስራ እድል ተከፍቶ ነበር። በዚህ ምክንያት ስራ ለመስራት ከተለያየ አህጉር እጅግ ቁጥራቸው የበዛ ሰዎች ወደ ምድሪቱ በህብረት ይተምሙ ነበር።

በላይ ባይሳ

እነዚህ ሰዎች ስራ ለመስራት በህብረት (massive) በሆነ መልኩ ከአፍሪካ፣ ከኤዥያ፣ ከአውሮፓና ሌሎች የአለማችን ክፍሎች ስለተንቀሳቀሱ ያለምንም ችግር ባህላቸውን እንዲያሳድጉና እንዲያበለፅጉ እንዲሁም የራሳቸውን ማንነት መገለጫ ባህል ይዘው እንዲቆዩ አስችሏቸዋል።

አሜሪካውያን እነኚህ የራሳቸውን ማንነትና ባህል ይዘው የመጡ የተለያዩ ማህበረሰቦች በምድረ አሜሪካ መሰባሰብ እጅግ ያላማራቸውና ያላስደሰታቸው ከመሆኑም ባሻገር ታላቋን አሜሪካን እና አሜሪካዊነትን አደጋ ውስጥ እንደጣላት ተሰማቸው። አሜሪካዊነት ጥያቄ ውስጥ የገባ መስሎ ስለታያቸው እጅግ ተጨነቁ። እንቅልፍም ነሳቸው።

ድንገት የተፈጠረ ክስተት በመሆኑ ወዲያው ወደ መፍትሄው ማትኮርን መረጡ። አደጋ ውስጥ የገባውን አሜሪካዊነት መታደግ ዋና ተግባራቸው አደረጉ።ለዚህም አሜሪካ ጠንካራ ሆና እንድትቀጥል ብዙ ሙከራዎችን ካደረጉ በኃላ Melting pot theory (የተለያየ ማንነት ያላቸውን ሰዎችን በገንቦ ውስጥ በመክተት በመቀላቀል እና በማማሰል አንድ ወጥ ማንነት ያለው ሰው መፍጠር እንደ ማለት ነው) ንድፍ ሃሳብ በመቀመር ለተግባራዊነቱ ተንቀሳቀሱ።እቅዱ ግን እንዲሁ እንደዋዛ ተግባራዊ የሚሆን ቀላል ንድፈ-ሃሳብ አልነበረም። ብዙ እንከኖች ገጠሙት።እነዚህ ከተለያዩ የዓለም ክፍል የመጡትን የራሳቸው ባህል፣ ወግና እሴት ያላቸውን ማህበረሰቦች “አንድ ወጥ አሜሪካዊ ማንነት” እንዲኖራቸው በማሰብ በቀላሉ መጨፍለቅ አልተቻለም።

ከረጅም ጊዜ ሙከራ በኃላ ከዚህ የማይተገበር ሃሳብ ትምህርት በመውሰድ ብዝሃ ባህልን (Multi culturalism) ማለትም ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል ልዩነትን በሁለንተናዊ መልኩ (የባህል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የቀለም …) ለአሜሪካ ችግር መፍትሄ እንደሆነ አመኑ። ለተግባራዊነቱም በተመሳሳይ ተንቀሳቀሱ።ዛሬ አሜሪካ ከማንነትና ከባህልም ባሻገር ድህረ-ዘመናዊነት ሲጨመርበት አሁንም ያላለፈቻቸው እና የተጋረጡባት ብዙ ፈተናዎች እንዳሉባት የሚያመላክቱ ምልክቶች ይታያሉ።

ይሁንና እነዚህን መሰል ችግሮች ቢኖሩባትም ጠንካራ ተቋማትንና ግዙፍ የአለም ኢኮኖሚ ለመገንባት መቻልዋ መሰረታዊ ሚስጢሩ ብዝሃነትን ለማክበር ጥረት ማድረጓ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ።ይህ የሚያመላክተን የተለያየ ማንነትን በመጨፍለቅ አንድ ወጥ አሜሪካዊነትን መገንባት እንደማይቻል ነው።እኛ ኢትዮጵያኖች እንደ አሜሪካ በግድ በገንቦ ውስጥ የተዋሃድን ሳንሆን በልዩነት ውስጥ ብዙ የሚያስተሳስሩን ነገሮች ያሉን የተጋመድን፣ ክፉና ደጉን አብረን ያሳለፍን፣ አብረን ተዋግተን ያሸነፍን፣ የተዋደቅን፣ ተጋብተን የተዋለድንና፣ የተሳሰርን አንድነት ያለን ህዝቦች ነን። ግን ይህም በራሱ ምሉዕ አልነበረም። የሚጎድለው ነገር አለ።

ጉድለቱ ምንድነው?የሃገራችን መሪዎች ኢትዮጵያዊነትንና ሃገረ-መንግስቱን ለመገንባት የሄዱበት መንገድ የራሱ በጎ ነገር ያለው ቢሆንም በዚያው ልክ ሃገሪቱን ዋጋ ያስከፈለ ችግርም ነበረበት።ባለፉት ስርዓቶች በሃገር ግንባታ ወቅት የተከናወኑ ተግባራት ሁለት መጣረዞችና ፅንፎች እንዲፈጠሩ አድርጓል።1ኛው. በቃ! “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ” የሚል አስተሳሰብ ነው። አስተሳሰቡ በራሱ ምንም ችግር የለበትም።

ችግር የሆነው ለብሄር ማንነት ቦታ የማይሰጥ እና እውቅናን የነፈገ በመሆኑ ነው።ይህ በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ግንባታ ላይ የራሱን ፅንፍ ይዞ ብዥታ ሲፈጥር ቆይቷል። በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ሳይሆን በጭፍን አንድ አይነት ትርክት የታጀበ በሩቁ ሃገራዊ ይዘት ያለው ቢመስልም በውስጡ ግን ዲሞክራሲያዊነት ይጎድለዋል። በስመ ኢትዮጵያ አሃድነትን በማቀንቀ ብዝሃነትን በአንድ የሚጨፈልቅ ጠቅላይነት የታየበት ነው። ኢትዮጵያዊነት በብዝሃነት የተገነባ አንድነት መሆኑን በግልፅ የማያመላክት ነበር።

በዚህ ምክንያት ዲሞክራሲያዊ የሆነ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ግንባታ አልተካሄደም። ምናልባት አሁን የሚጀመር ካልሆነ በስተቀር። ይሁንና ከእስካሁኑ ስህተቶች በመማር በትጋት ከተሰራ ተስፋ ያለው ይመስላል።2ኛው. ፅንፈኛ ብሄርተኝነት ነው። ከኔ ሌላ ማንም የለም የሚል አባዜ አንዱ ሲሆን እኔ የማልረባ የማልፈለግ ነኝ በማለት ማንነትን ለራስ የማሳነስ ችግር ደግሞ ሌላኛው ችግር ነው።

ትልቁን ሃገራዊ ስዕል በመርሳት ከኔ ውጪ ያለውን አልቀበልም የሚል አዝማምያ የተስተዋለበት ፅንፍም ነው። ይህ ደግሞ ከመገለልና ከመገፋት የተወለደ ባይተዋርነት ፈጥሯል። መነሻውም የማንነት/የብሄር ግንባታውም አንዱን በማሳነስና ሌላውን በማግነን የወገነ እንደ ሃገረ-መንግስቱ ግንባታ ችግር ነበረበት።

በነዚህ ሁለት መሰረታዊ ያደሩ እና ሲንከባለል በመጣው ችግር ምክንያቶች ኢትዮጵያዊነት ብዝሃነትን መሰረት ባደረገ መልኩ ስላልተገነባ ሁልጊዜ በየምዕራፉ ጥያቄ ይነሳል። ስለ ሃገር ግልፅ እና የጠራ ሁሉንም የሚያግባባ የጋራ እሴት ስላልገነባን ውህደት አጥተናል።በዚህ ምክንያት አንዱ የሚገነባውን ሌላው ለመናድ ይሯሯጣል። በለው! አፍርሰው! ስበረው…ማለት እንወዳለን።

ዛሬ ግን እስካሁን ከመጣንበት እጅግ ፈታኝ ውስብስብ ችግሮች በመማር በአዲስ አስተሳሰብ ከመምሰል ወጥተን ወደ መሆን በመቀየር ችግሮችን በማረቅ ወደፊት መጓዝ ይኖርብናል። ለቀጣይ ትውልድም ፍትሃዊ እና ምቹ ሃገር ለመፍጠር መትጋትና መግባባት ይገባል። እንደ ሃገር ጠንካራ ሆኖ ለመቀጠል መግባባትና መስማማት ውዴታ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው።አያቶቻችን ያስረከቡንን ሃገር የመገንባት ሃላፊነት የዚህ ትውልድ አደራ ጭምር ነው።ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

በላይ ባይሳ – ሚያዝያ 15/2010 ዓ.ም

ይሄህ ፅሁፍ ከሶስት አመት በፊት መፃፉ ልብ ይለዋል።


Exit mobile version