ልሙጥ “ዲሞክራሲ”


ሰውየው ከሚስቱ ጋር አብረው መንገድ እየሄዱ ወንዝ ጋር ሲደርሱ ደራሽ ጎርፍ ያጋጥማቸዋል ባልም “ወንዙ እስኪቀንስ ትንሽ እንጠብቅ” ሲላት ሁሌ የሱ ተቃራኒ መሆንን ኑሮዋ ስላደረገችው ምክሩን ሳትሰማ የተለመደ ተቃራኒ ተግባሯን በማራመድ ወንዙ ውስጥ እንደገባች የወንዙ ሙላት ይዟት ጭልጥ አለ።

ባል በጣም በመደናገጥ የድረሱልኝ ጬኸቱን ሲያቀልጠው የአከባቢው ሰው ይደርስና “ምንሆንክ?” ሲሉት “ሚስቴን ውሃ ወሰደብኝ” እያለ ማልቀሱን ተያያዘው። የአከባቢው ሰውም እየተረባረበ ውሃውን ተከትሎ ፍለጋ ሲያደርግ ባል ጮክ ብሎ “ሚስቴ ሁሌ ተቃራኒ ስለሆነች ውሃው ወደሚፈስበት አቅጣጫ ሳይሆን ወደተቃራኒው ወደላይ ፈልጓት” አለ አሉ።

የኛም ዲሞክራሲ እንዲሁ ነው። በተቃርኖ ላይ የተመሠረተ ልሙጥ አስተሳሰብየተጫጫነው። ለአመክኗዊነት የማይገዛ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረ ግራ የገባው ዝግ አስተሳሰብ ቀፍድዶ ይዞታል።

የመጣውን መርቆ፣ አወድሶ፣ አጅቦና አጨብጭቦ ይቀበልና የሚሄደውን ሃጥያቱን አብዝቶ ረግሞ የሚያባርር ማህበረሰብ ዲሞክራሲን የመገንባትና የመለማመድ ባህል አይኖረውም። ምክንያቱም ሃገርን በሂደት የመገንባት ባህል ሳይሆን የትላንቱን በጎ ነገር ከስር መሠረቱ በማፍረስ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ መስተጋብሩ በአመክኗዊነት እና በዘላቂ ሃሳብ ሳይሆን በማስመሰልና በጊዜያዊ አርተፊሻል ሁኔታዎች ላይ ብቻ የተንጠላጠለ ማንነት ስለሆነ ማለት ነው።

እንደ ሃገር በአብሮነት ረጅም ጉዞ እንጓዛለን ስትለው “ሰዓቱ አሁን ነው” ይልሃል፣ ሃገር ስትለው ሰፈር፣ አንድነት ስትለው አንዳይነትነት፣ ተሳተፍ ስትለው ሰበብ በመደርደር መራቅ፣ በሰብአዊነትስም ኢሰብዓዊነትን ያበረታታል፣ ከምርጫ ይልቅ በአቋራጭ ለስልጣን ይቋምጣል፣ ነፃነት ስትለው ባርነት ይናፍቀዋል፣ መደመር ስትለው መቀነስ፣ መቀራረብ ስትለው መራራቅን፣ አቃፊ ይመስልና ገፊ፣ እኩልነት ስትለው የበላይነትን የሚያቀነቅን፣ ህጋዊ ስትለው ህገወጥነት፣ ፍቅር ስትለው ጥላቻ፣ ባህሌን ላበልፅግ ስትለው ዘረኛ ይልሃል፣ ብዝሃነት ስትለው ልሙጥ ይልሃል እረ ምኑ ቅጡ …

ፍላጎቱን ለማወቅ ይቅርና ለመገመትም ያስቸግራል። የጥዋት እና የማታ ፍላጎቱ ይለዋወጣል። ጠዋት ያወደሰውን ማታ ይዘረጥጠዋል። ለምን ስትለው “ዲሞክራሲያዊ መብቴ ነው!” ይልሃል። ድንቄም ዲሞክራሲ

ባሻዬ ዲሞክራሲን ዲሞክራሲ የሚያሰኘው የቃላት ድርደራና ማሳመር ሳይሆን በዋናነት ብዝሃነትንና ልዩነትን በተጨባጭ ማስተናገድ መቻሉ ነው። ለብዙሃኑ ሃሳብ ተገዥ መሆኑ ጭምር። ይህን ለማድረግ ደግሞ የጠራ አስተሳሰብና አቋም ይጠይቃል።

See also  ታሪክን የሁዋሊት - በእውቀቱ ስዩም

ለዲሞክራሲ ባህል መሠረቱ ደግሞ የህብረተሰቡ ዝግጁነት እና ልዩነትን የመረዳትና የመቀበል ፍላጎቱ ሲጎለብት ብቻ ነው።

ለዚህም ይመስለኛል ዲሞክራሲያችን ከዳይፐር አልላቀቅ ብሎ ከልሙጥ አስተሳሰብ ተቃርኖ ውስጥ መፋታት ያቃተው።

ስለዚህ የዲሞክራሲ ግንባታ በልሙጣዊ አስተሳሰብ ሳይሆን የተለያዩ የአስተሳሰብና ተግባራዊ ግብአቶችን ይፈልጋል የሚባለው። በመሆኑም እንደ ሃገር የዲሞክራሲን ባህል ለመገንባት የሚያስችል የቅድመ-ሁኔታ ስራ ለመስራት ቀዳሚው የቤት ስራ ሊሆን የሚገባው ማህበረሰቡን በማዘጋጀት ነው።

አቢዮታዊ ብሎ ዲሞክራሲ ማለት የማይጣጣም ሁለት አብሮ የማይሄድ ሃሳብ እንደመሆኑ ሁሉ ልሙጥ ሆኖ ዲሞክራሲን ማሰብ ቅዥት ነው።

ልሙጡ ይሄንንም እኔን ነው ብለህ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ጬኸትህን ጩህ አሉ ደግሞ።

By Belay Bayisa

https://www.facebook.com/belay.bayisa
ጥር 19/2013 ዓ.ም

Leave a Reply