Site icon ETHIO12.COM

ለአዲስ አመት ጌታ ሁለት ወንዶች ልጆች ሰጠኝ-(ሶፊያ ሽባባው)

ትላንት ለአንድ ስራ ወደ ቦሌ ሄጄ ቀጠሮ አስኪደርስ ለመቆየት ወደ አንድ በጣም ደስ የሚል ምግብ ቤት ስሙዚ ለመጠጣት ከመኪና ስወርድ ……
……ሁለት የቆሸሸና የተቦጫጨቀ ልብስ የለበሱ ህጻናት እጃቸውን ዘርግተው እየተከተሉኝ እትዬ ለዳቦ ሲሉኝ ኑ አብራችሁኝ ስሙዚ እንጠጣ ብዬ ይዣቸው ስገባ አስተናጋጆቹ እየተሯሯጡ መጡና እንቅ አርገው ይዘው እያመናጨቁ ውጡ ከዚ አሏቸው ማኔጀሩም መቶ እናንተ ውጭ ሁኑ አላቸው።

……እንደምንም ንዴቴን ተቆጣጥሬ ልጆቹን ወደኔ እየሳብኩ ከኔጋር ናቸው እኮ ስሙዚ ልገዛላቸው ነው ስላቸው ውጭ ሆነው ይጠጡ አሉኝ
…… ምግብ ቤት ውስጥ ያለው ሰው ትኩረት ሁሉ ወደኛ ሆነ።
ማኔጀሩን ቆጣ ብዬ ከኔ ጋር እውስጥ ቁጭ ብለው እንዲጠጡ ነው የምፈልገው በነጻ ሊለምኑ እኮ አይደለም ተከፍሎ ነው የሚጠጡት ስለው ለምን ግን ብሩን አትሰጫቸውምና ሌላ ጠቃሚ ነገር አይገዙበትም አለኝ።

……እኔም አይ ጁስ ለልጆች ጠቃሚ ነው ጂስ መጋበዝ እፈልጋለሁ ብርም የሚያሰፈልጋቸው ከሆነ እሰጣቸዋለሁ ስለው በፍጹም እንደማልሸነፍለት ገብቶት ነው መሰለኝ
ኦ እንደሱማ ከሆነ ጥሩ ነው ይግቡ በቃ ብሎ እየሳቀና እየተገረመ ግቡ ልጆች ብሎ በአክብሮት ወንበር ሰጣቸው።

……..ምግብ ቤት ውስጥ የነበረው ሰው ሁሉ አይናቸው በመገረም እኛላይ ሆነ።

ቁጭ ካልን በኋላ ስማቸውን ሰጠይቃቸው አድነው እና አለሙ እንደሚባሉ ነገሩኝ።
……. ከማንጋር ነው የምትኖሩት ስላቸው ከአባታችን ጋር ግን አሁን እሱ የለም ጎጃም ነው ያለው አሉኝ።
ለምንድነው የምትለምኑት ስላቸው መስከረም ላይ ት/ቤት ልንገባ ስለሆነ ለደብተር እና ለጫማ መግዣ ነው አሉኝ እንደዛ የተዋበ ምግብ ቤት ውስጥ ንጹህ ወንበር ላይ በመቀመጣቸው እየተሳቀቁ።

…..እናንተኮ የወደፊት የሀገር መሪዎች ሀኪምች ነጋዴዎች… ናችሁ ለናንተ እዚህ መቀመጥ ሲያንሳችሁ ነው ዘና ብላችሁ ቁጭ በሉ ስላቸው
…..በዚ ችግር ባደከመው ፊታቸው ፈገግ እያሉ ያዩኛል።
እናታችሁ የትናት ስላቸው እኔንጃ አናውቅም አሉኝ።እንዴት ሞታለች ማለትነው ስላቸው አይ መሞቷን አናውቅም አይተናትም አናውቅም እኛ አራስ ሆነን ነው የሄደችው ወዴት እንሄደች ምን እንደሆነች አባታችን አይነግረንም ከጠየቅነውም ይቆጣናል ሲሉኝ እምባዬን መቆጣጠር ተሳነኝ ምን እንደማደርጋቸው ግራ ገባኝ።
…….ለአንድም ቀን የናትን ፍቅር ለማግኘት ያልታደሉ መሆናቸውን ሳይ ሁለቱንም ማቀፍ ፈለኩ።
……እናታቸው የት አንደደረሰች የመጠየቅ መብትም የላቸውም።እንደምንም እራሴን ተቆጣጥሬ አሁን እኔ ደብተር እና ጫማ ብገዛላችሁ መለመን ትቀጥላላችሁ ስላቸው እኛ አንለምንም ትምህርት ቤት እንገባለን እኮ ወደ ጎጃም ተመልሰን አሉኝ።

…..ማኔጀሩን አስጠርቼ ስልኬን ሰጠሁትና የልጆቹ አባት ሲመጣ ደውለህ አገናኘኝ እነሱ ሲመጣ ወዳንተ ያመጡታል ብዬው ሂሳባችንን ከፍለን ወተን የሰዎች አይን አሁንም ስለሚከተለን ዞር ወዳለ ቦታ ወሰድኳቸውና እናት ትፈልጋላችሁ?! አልኳቸው።
…..ፍጹም ሀሴት በተሞላ መንፈስ አዎ አሉኝ ሁለቱም በአንድ አፍ። እሺ ከዛሬ ጀምሮ እኔ እናታችሁ ነኝ እኔ አስተምራችኋለሁ ደብተርና ልብስ ለመግዛት መለመን የለባችሁም ትምህርታችሁ ላይ ብቻ አተኩሩ ስላቸው ግን እኮ አንቺ ቤት እንድንኖር አባታችን አይፈቅድም አሉኝ።

….አይ ከአባታችሁ ጋር እየኖራችሁ እናት መሆን እችላለሁ ሁሌ አየመጣሁ እጠይቃችኋለው በጣም ነው የምወዳችሁ ልጆቼ ብዬ ሳቅፋቸው መንገደኞች ቆም እያሉ ከንፈራቸውን እየመጠጡ ያዩናል።

በሉ አናንተም መልካም እናት እንድሆን በጸሎታችሁ አግዙኝ!። via Ethio press


Exit mobile version