Site icon ETHIO12.COM

‹‹የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያን እውነታ የተረዳ አይመስልም… የተሳሳተ መረጃዎችም የሚሰጧቸው አሉ››

‹‹የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያን እውነታ የተረዳ አይመስልም። የመረጃ እጥረቶች አሉባቸው። የተሳሳተ መረጃዎችም የሚሰጧቸው አሉ››፣ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመው አይነት ጥቃት በአሜሪካ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ አሜሪካኖች ኢትዮጵያ ያደረገችውን ነበር የሚያደርጉት ሲሉ በሰሜን ካሮላይና በኤ ኤንድ ቲ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የጋዜጠኝነት መምህሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ተናገሩ።

የአሜሪካ ዴሞክራት ፓርቲ አመራሮች በብቃታቸውና በአፈጻጸማቸው የተነሳ ጸረ-ኢትዮጵያ ከሆኑ እንደምነቀጣቸው፤ ድምጻችንንም ለሪፐብሊካን እንደምንሰጥ በግልጽ ነግረናቸዋል፤ በተጨባጭም ልዩነት እንደምንፈጥር አሳይተናቸዋል ብለዋል።

ፕሮፌሰር ብሩክ ‹‹ሃሽታግ ስለኢትዮጵያ ያገባኛል›› በሚል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚያቀርበው የኦንላይ ውይይት መድረክ ላይ በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላት ላይ የፈጸመው አይነት ክህደትና ጥቃት በአሜሪካ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ተፈጽሞ ቢሆን ኖሮ አሜሪከኖች ያለምንም ማመንታት ኢትዮጵያ የወሰደችውን አይነት እርምጃ ነበር የሚወስዱት።

ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር በህብረት የሚያደርጉትን ጥረት በማጠናከር በህብረትና በቅንጅት የውጭ ጫናን ሊቋቋሙ ይገባል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ በአሜሪካ በኢትዮጵያውያን የሚደረጉ ሰልፎች አገራችንን ለቀቅ አድርጉ መልዕክት የሚያስተላልፉ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በአገሩ ሉዓላዊነት የማይደራደርና አንድነት ያለው በመሆኑ አሜሪካ በራሷ አገር ወታደር ላይ ጥቃት ቢደርስ የማታልፈውን ኢትዮጵያ እንድታልፍ ግፊት እያደረገች ትገኛለች ብለዋል። ኢትዮጵያውያን በሰልፎች ላይ የሚይዟቸው መፈክሮችና ፖስተሮች የሚያሳዩት ይህንን ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች መልዕክቱ እንደሚተላለፍም ጠቁመዋል።

ለአሜሪካ ፖለቲከኞችም ‹‹በምርጫ ድምፃችንን በመንፈግ እንቀጣችኋለን›› የሚል መልዕክት መተላለፉን ጠቁመዋል። ይህ ደግሞ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ፕሮፌሰር ብሩክ አመልክተዋል። ‹‹የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የኢትዮጵያን እውነታ የተረዳ አይመስልም። የመረጃ እጥረቶች አሉባቸው። የተሳሳተ መረጃዎችም የሚሰጧቸው አሉ›› ሲሉ ተናግረዋል። መረጃውን የሚያገኙት ላለፉት 30 ዓመታት ካለፈው መሪ ፓርቲ ጋር በፈጠሩት ሰንሰለት መሆኑንም ተናግረዋል። ጦርነቱን ራሱ ህወሓት እንደጀመረው ፕሮፌሰር ብሩክ አስታውሰው፤ ጥቃቱን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግሥት ያደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ የአገር ሉዓላዊነትን የማስጠበቅ ሥራ መሆኑንም አመልክተዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።


Exit mobile version