ETHIO12.COM

24 ሠዓታት በወታደር ህይወት – ምስክርነት ክፍል 4 “ህይወትን በአግባቡ ያላጣጣሙ የቁርጥ ቀን ትንታጎች”

የቁርጥ ቀን ልጆች አብዛኞቹ ወጣቶች ነበሩ ። ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ ትንታጎች። ህይወትን በአግባቡ ያላጣጣሙ፤ በአዲስ ህይወት መጀመሪያቸው ወቅት ላይ ለሀገር ክብር ነፍጥ ያነገቡ ነበሩ። በሚገርም ሁኔታ ጥያቄያቸው በተገኘው አጋጣሚ ከነባልባሉ ተርፈው በህይወት መቆየት ሳይሆን በግንባር ቀደምትነት መስዋዕት ሆነው ሉዓላዊነታቸውን ማስከበር ነበር። ሀገራዊ ስምና ዝናን ለተተኪው ትውልድ ማኖር ብቻና ብቻ ነበር።

በ1991 እና በ1992 ዓ.ም ወደ ሠራዊቱ የተቀላቀሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ጀግንነት የኢትዮጵያውያን ማንነት እና መለያ መሆኑን በተግባር እንዳሳዩ ሻለቃው ምስክር ነኝ ይላሉ። የደርግ መንግስትን ጥለው የሀገሪቱን መንበረ ስልጣን የተቆጣጠሩ አካላት ስለ ጀግንነት ይነዙት የነበረው ኘሮፓጋንዳ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የገባው ከኤርትራ ጋር በተደረገው የመጀመሪያው ውጊያ እንደነበር መኮንኑ መቼም አይዘነጉም።እነሱ ‘የደርግ ወታደር’ የሚሉት የወቅቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት በአፍሪካ ተወዳዳሪ አልነበረውም፡፡

ያ ታጋይ ባይሆን ምንም ምድራዊ ሐይል የማይረታው እንደነበር በስነ- ጥበብና በኪነ-ጥበብ ጭምር ታግዘው ብዙ በመስበክ ለመታመን ጫፍ ደርሰው ነበር። ምን ዋጋ አለው? ከኤርትራ ጋር የተደረገው ጦርነት ነገሩን ቆም ብለን እንድናጤነው አድርጎናል ።በመጀመሪያ ባድመን የማስለቀቅ ውጊያ ፈንጂ እየተራመዱ፤ የጠላትን ምሽግ በቦንብ እያጋዩ ምሽግ ያስለቀቁት ፤ ከዚያ በፊት ምንም ዓይነት የውጊያ ልምድ ያልነበራቸው ፤ ጦርነትን በፊልም ብቻ የሚያውቁ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ነበሩ።

ውጊያ የሰለጠኑበት ስለሆነ አያስገርምም ሊባል ይችላል። የሚያስገርም ፣ ምንም ዓይነት ማስተባበያ ሊቀርብበት የማይችል ተግባራትን የፈፀሙ ደግሞ አሉ። ነባር እና የውጊያ ኤክስፐርት የተባሉት ሲሰዉ ሬዲዮ ተቀብሎ አዋግተዋል። ክላሽ ምድብተኛ ሆኖ ሳለ ከሞተ የተቃራኒ ወታደር የቡድን መሣሪያዎች ለአብነት መትረየስ ፣ ዲሽቃና እስናይፐር ተቀብለው ድጋፍ ሰጥተዋል።

አዋጊ ሲሰዋ አባል አዋጊ ነበር። ተኳሽ ሲሞት ረዳት ሚናውን ተወጥቷል። አባል ሆኖ ጀምሮ መቶና ሻምበል አመራር ሆኖ የጨረሰ የቁርጥ ቀን ልጅ ቁጥሩ በርካታ ነበር። ነባር ታጋዩ ውስጥ ጀግና አዋጊና ተዋጊዎች የነበሩ ሲሆን ፣ የተባለውን ያህል በተግባር ከተባለው በተቃራኒ የተገለፁም ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም።

የውጊያው ምክንያት ፣ አስፈላጊ መሆንና አለመሆንን ለታሪክ ትተን አንድ ድምደሜ ላይ ግን መድረስ ይቻላል። (ሁሉም አባባሎች የተራኪው ናቸው።) ኢትዮጵያውያን በአጭር ጊዜ የተዋጣለት የአውደ ውጊያ ጀግና መሆን ይችላሉ።በ1969 ዓ.ም በጎረቤት ሶማሊያ ወራራ በሦስት ወር ስልጠና ተዓምር የሠራው ሚሊሻ ነፍስ ዘርቶ በተረኞቹ ኢትዮጵያውያን በ1991 እና በ1992 ዓ.ም ሰሜን ላይ ተከስቷል።

ለብዙ ሺህ ዘመናት በነፃነት የመኖር ምስጢራችን ዳግም ተፈቷል።“24 ሠዓታት በወታደር ህይወት” የመኮንኑ ትራካ ይቀጥላል። ‘ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” የመኮንኑን እውነተኛ ምስክርነት ተተኪው እንዲማርበት እየጨለፍን ማስነበባችንን እንቀጥላለን።

ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ – ከመከላከያ ፌስ ቡክ የተወሰደ


Exit mobile version