“የክንደ ብርቱዎች እናት ‘ኢትዮጵያ’ በልጆቿ ትንፋሽ ሰንደቋ ዳግም ከፍ ብሎ ይውለበለባል”

  • ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ኢትዮጵያ የሚለው ስም ለሺዎች ዘመናት ከነጻነት፣ ከአሸናፊነትና ከአልደፈር ባይነት ጋር የተያያዘ ስም ነው። ከግሪክ እስከ ሮም ፈላስፎች፣ ከዕብራውያን እስከ ፋርስ አባቶች፣ ከሩቅ ምሥራቅ እስከ ዐረብ ሊቃውንት፤ ከብሉይ እስከ ሐዲስ፤ ከክርስትና እስከ እስልምና፣ ኢትዮጵያ ነጻነት ወዳድነቷ፣ አሸናፊነቷና አልደፈር ባይነቷ ሲነገር ኖሯል። ይኖራልም።

ይሄንን የመሰለው ታላቅ ስም እንዲሁ የሚገኝ አይደለምና፣ ይሄ ለምን ሆነ? ብለን መጠየቅ አለብን። እንዲሁ የሚገኝ ቢሆን ኖሮ ታላላቅ የዓለም ሀገሮች አንድም በወርቅ አንድም በገንዘብ ይገዙት ነበር። ግን አልተቻለም። እንዲህ ያለው የክብር ስም የሚገኘው በታላቅ መሥዋዕትነት ነው። ኢትዮጵያውያን ደግሞ ያለ ምንም ልዩነት፣ ለሀገራቸው መሥዋዕትነትን ለመክፈል ምንጊዜምና መቼም ዝግጁዎች ናቸው። ሺ ዘመናትን ቢያልፉ እንኳን ለሀገሩ መሥዋዕትነት የማይከፍል የኢትዮጵያ ልጅ የለም። እንዲያውም የኢትዮጵያ ልጆች የሆኑትን ካልሆኑት የመለያው ሁነኛ ፈተና፣ ለኢትዮጵያ መሥዋዕትነትን ለመክፈል የሚኖር ቁርጠኝነት ነው። ከሌላው ዓለም መጥተው የኢትዮጵያ ልጆች የሆኑ ወገኖች በታሪክ ውስጥ ታይተዋል። መሥዋዕትነትን ከፍለው አፈሯን ወርሰዋልና። ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥረው የኢትዮጵያ ልጆች ያልሆኑም አሉ። ለኢትዮጵያ መሥዋዕትነትን ላለመክፈል ብለው ብኩርናቸውን በጥቅም ሸጠው ባንዳነትን የመረጡ ጥቂት አሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በደሙ ውስጥ ጀግንነት የሚመላለስ ሕዝብ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው። በእርሻ፣ በንግድ፣ በመንግሥት ሥራ፣ በሃይማኖት አገልግሎት፣ ሕይወታቸውን የሚገፉ ኢትዮጵያውያን፤ ሀገራቸው የተነካች መሆኗን ሲያረጋግጡ፣ ከመቅጽበት ወደ ወታደርነት ተቀይረው፣ ያገኙትን መሣሪያ አንሥተው፤ መሣሪያ ቢያጡ ወኔያቸውን ሰንቀው፣ ሀገራቸውን በአጥንትና በደም ዋጋ ሊታደጉ ይሰለፋሉ፤ እነሱ ወድቀው ሌላው እንዲቆም፣ እነሱ ተደፍተው ሀገር ቀና እንድትል በአንድ ነፍሳቸው ይወራረዳሉ። ለዚህ ነው በክፉ ዓይናቸው ለሚያይዋት ጠላቶች “ኢትዮጵያ መቶ ሚልዮን የቁርጥ ቀን ወታደሮች አሏት፤ ይቅርባችሁ አትንኳት” የምንለው።

ይሄንን ምክር ያልሰሙ የውጭና የውስጥ ጠላቶች ኢትዮጵያን ደጋግመው ፈትነዋታል። እርሷም ደጋግማ ፈተናውን አልፋለች፤ ጠላቶቿንም ደጋግማ አንገት አስደፍታለች። ከእነዚህ የፈተና ወቅቶች አንዱ ባለፈው ዓመት የገጠመን ፈተና ነው። ኢትዮጵያን ባለማወቅ በሽታ የተጠቃው አሸባሪው ሕወሐት፣ ጥቅምት 23 ቀን ምሽት፣ ሰሜን ዕዝን አጥቅቶ ኢትዮጵያን ለመድፈር ተነሣ። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ተደራራቢ ክህደት የታየበት ነበር። አሸባሪው ሕወሐት ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያን መከላከያ የማፍረስ ደባውን የተገበረበት እለት ነው። በታሪክ ታይቶ በማያውቅ መልኩ ራሱ የገነባውን መከላከያ በክህደት ራሱ ሊያፈርስ የተነሣ ድርጅት ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ከሃዲዎች ገጥመዋት ያውቃሉ። እንዲህ ዓይነት ክህደት ግን እንኳን ኢትዮጵያ፣ ዓለምም ገጥሟት የሚያውቅ አይመስልም። ኢትዮጵያውያን እንዲህ ያለውን አስነዋሪ ተግባር እፉኝት የተባለችው እባብ ብቻ እንደምትፈጽመው ነበር በባህላቸው የሚያውቁት። ዛሬ ግን እፉኝት የተደራጀ አሸባሪ ቡድን ሆኖ ነው የገጠማቸው። የእፉኝት ልጆች አባታቸውንም እናታቸውን ገድለው ለመኖርና ለማደግ የሚሞክሩ ከንቱዎች ናቸው።

ጥቅምት 23 ቀን ምሽት የተደረገውን ክህደት ጀግኖቹ የሰሜን ዕዝ አባላት በአስደናቂው ኢትዮጵያዊ የጦር ጥበብ እየተዋጉ፣ መሣሪያቸውን ይዘው ከጠላት ከበባ በመውጣት አከሸፉት። የተሠዉት ተሠውተው፤ የቆሰሉት ቆስለው፣ ኢትዮጵያ በሠፈር ጎረምሳ የምትሰበር ሀገር አለመሆኗን አስመሰከሩ። የሀገሩ መነካት እንደ እግር ቁስል ያንገበገበው ኢትዮጵያዊ ሁሉ፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ፣ ከሽበት እስከ ኩተት ነቅሎ በመነሣቱ፣ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ጠላትን ከስሕበት ማዕከሉ መቀሌ ወደ ተንቤን በረሃ ሸኝቶታል። የተማረኩብንን የሰሜን ዕዝ አባላትና ትጥቃችንን አስመልሰን፣ ለብዙ ጊዜ ቡኑ ከዐይኑ እንዳይርቅ አድርጎ የሰወረውን ስትራተጂያዊ መሣሪያ ወርሰን፤ የተወሰኑ የቡድኑን አባላት ደመስሰን፤ የተወሰኑትንም በቁጥጥር ሥር አደረግን።

የመከላከያ ኃይላችን ሕዝባዊ ኃይል ነው። ለስምንት ወራት ትግራይ ውስጥ በየቦታው እየተንከራተተ ርዳታ እንዲዳረስ፣ ሰላም እንዲሰፍን፣ በአሸባሪው የፈረሱ መሠረተ ልማቶች እንደገና እንዲገነቡ፤ ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ፣ መንግሥታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ለማድረግ ደክሟል። አመሉ ጥፋት፣ ጠባዩ ከህደት የሆነው ይህ አሸባሪ ቡድን ግን የሕዝብ ሰላም ሞቱ፣ የሀገር ዕድገት ሕመሙ ነው። ያለ ጥፋት ማደር፣ ያለ ጦርነት መኖር አይቻለውም።
በዚህም የተነሣ ርዳታ እንዳይደርስ፣ ገበሬው እንዳያርስ፣ የፈረሰው እንዳይጠገን፣ የተቋረጠው አገልግሎት እንዳይጀመር፣ ቀድሞ በዘረጋው የጥፋት መረቡ አማካኝነት መቀስቀስ ጀመረ። በዚያም ላይ የፕሮፓጋንዳ አመድ ነሰነሰበት፤ የመከላከያ ሠራዊታችንን መልካም ስም ጥላሸት ቀባው። ኢትዮጵያዊ ጀግንነት መልኩ እንዲጠይም አደረገ።

ይሄን የተመለከተው የኢትዮጵያ መንግሥት ለሕዝቡ ሲባል በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወስኖ ከትግራይ ወጣ። በዋናነት ዓላማው በተለይ ገበሬው ተደጋጋሚ የእርሻ ወቅት እንዳያልፈው ለማድረግ የታለመ ነበር። “ሞኝ ከሳቁለት ውሻ ከሮጡለት” እንደሚባለው የመንግሥትን ውሳኔ አሸባሪው ወያኔ እንደ ሽንፈት ቆጠረው። አሁንም ካለፈው ጥፋቱ ባለመማር ሕዝቡን በመንጋ አሰልፎ መከላከያን መውጋት ቀጠለ። የክህደት ተግባሩን ገፋበት፤ ከቅርብና የሩቅ ጠላቶቻችን ጋር ተመሳጥሮ ኢትዮጵያን ሊወጋ መጣ።

ኢትዮጵያ የተአምር ሀገር ናት። ምን ዐቅም እንዳላት የሚገለጥበት የራሱ ጊዜ አለው። ለሁለት ጊዜ በተፈጸመበት እፉኝታዊ ክህደት የተመታውን መከላከያ፣ አጠፋዋለሁ ብሎ አሸባሪው ኃይል ሲያስብ፣ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ መቶ ሺዎችን መልምሎ፣ አሠልጥኖ፣ አስታጥቆና አሠማርቶ የጠላትን ፍላጎት ለማክሸፍ ተቻለ። ጀግኖች ከየጎሬው ፈለቁ፤ ወጣቶች እምቢ ለሀገሬ አሉ። አረጋውያን የከረመ መሣሪያቸውን ወለወሉ። የቀድሞ ጦር አባላት የመጨረሻውን እድሜያቸውን በግንባር ለማሳለፍ ተመሙ። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከጦሩ ጋር ተሰለፉ፤ እናቶች ክንዳቸውን አፈርጥመው ወደ ውጊያ፣ ወገባቸውን ታጥቀው ወደ ስንቅ ዝግጅት ገቡ፤ ነጋዴዎች ከድጋፍ እስከ ግንባር ዘመቱ፤ የመንግሥት ሠራተኞች ሀገራቸውን ከአሸባሪ ደፋሪዎች ሊታደጉ ተመሙ፤ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች፣ አትሌቶች፣ ሐኪሞች፣ ሾፌሮች፣ ጋዜጠኞች፣ ውሎና አዳራቸው በግንባር ሆነ። ኢትዮጵያውያን ተቀየሩ። እንደ በሬ ሲያርሱ የነበሩት ሁሉ እንደ አንበሳ አገሡ። እንደ ፈረስ ለኑሯቸው ሲሯሯጡ የነበሩት ሁሉ እንደ አራስ ነብር ተቆጡ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ኮራች። ኢትዮጵያ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ዳግም ለጠላቶቿ አሳየች። የተዋጋነው ከአሸባሪው ወያኔ ጋር ብቻ አልነበረም። ወያኔ መርፌ ነው። መርፌ በሚቀድደው በኩል ሊገቡ የተዘጋጁ ብዙ ገመዶች ነበሩ። ወያኔን ከነግሣንግሡ ነው ድል ያደረግነው። አንዳንዶች በዓለም አቀፍ መድረኮች ይሟገቱለታል። ሌሎች በመረጃ ያግዙታል፤ አንዳንዶች በሳተላይት ይመሩታል፤ ሌሎች ደግሞ ከውስጥ ሆነው ይላላኩለታል፤ በርዳታ ድርጅት ስም፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት ስም፤ በሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ስም፤ በሚዲያ ስም፤ አብረውት ከአሸባሪው ኃይል ጋር ብዙዎች ተሰልፈው ነበር። ኢትዮጵያ ግን ሁሉንም ድል ነሥታ ታሪኳን አድሳለች።

በሁሉም ግንባሮች፣ በተሰጣችሁ ሥምሪት፣ ይህችን ድንቅ ሀገር ኢትዮጵያን፤ በሕይወት መሥዋዕትነት አክብራችኋታልና፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ኮርተውባችኋል። ጓንት ሆኖ ያገለገለውን የሽብር ቡድን ብቻ ሳይሆን ጓንቱን ያጠለቁት የጠላቶቻችንን እጆች ጭምር ቆርጣችሁ ጥላችኋል። የእናንተ ወላጆች፣ ወንድሞችና እኅቶች፣ ወገኖችና ዘመዶች፣ ልጆችና የልጅ ልጆች በመሆናችን በታሪክ ጎዳናዎች ላይ በኩራት እንድንራመድ አድርጋችሁናል። ይሄንን ጀግንነታችሁን፤ ይሄንን አስደናቂ ጀብዷችሁን ለልጆቻችን በኩራት እንተርካለን። ድርሰትና ፊልም፣ ቅኔና ዜማ እናደርገዋለን። የኢትዮጵያ ተራሮች፣ ሸለቆዎችና ወንዞች የጀግኖቹን ገድል አይተው ተገርመዋል። መቼም እንደነርሱ በታሪክ የታደለ የለም። ጥንት አባቶቻችን ታሪክ ሲሠሩ ነበሩ። ዛሬም ልጆቻቸው እናንተ ታሪክ ስትሠሩ እነዚህ ተራሮችና ሸለቆዎች፣ ሜዳዎችና ወንዞች አሉ። ባይነግሩንም እንደሚደነቁ እናምናለን። እነ ሞት አይፈሬ፣ እነ ውጊያ ምሳው፤ እነ ምሽግ ደርማሽ፣ እነ ታንክ በጊሌ ማራኪ፣ እንደ ነብር አድብተው፣ እንደ ዘንዶ ቆርጠው ጠልቀው የሚገቡ፤ የእሳት ግማዶች፤ የፍም ትንታጎች፣ የገሞራ ተምዘግዛጊዎች፣ ክንደ ነበልባሎች፤ አቤት ስንቱን ጀግና ይህች ሀገር ወለደችው። አቤት ስንቶቹ ሞትን ራሱን አስደነገጡት፤ ለታሪክ በታሪክ ኖረን፣ ታሪክ ሲሠራ አየን።

እናንተ የኢትዮጵያ ጀግኖች!

ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት። ታላቅ የመከላከያ ተቋም ያስፈልጋታል። ይህ የመከላከያ ኃይል ጠላትን የሚያሸንፍ ብቻ አይደለም። በጠላት የሚፈራ፣ ገና ሳይዋጋ ውጊያን የሚገታ፤ ኢትዮጵያን ለመንካት ያሰቡ ሁሉ ቀና ብለው ለማየት ፈርተውት ሐሳባቸውን ርግፍ አድርገው እንዲተዉት የሚያደርግ ተቋም። እንዲህ ያለውን ተቋም መገንባት ገና ይቀረናል። ጀምረናል፤ ግን አላገባደድንም። በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች የሚገኙ ወጣቶቻችን ወደዚህ ተቋም መግባት አለባቸው። ተመራማሪዎችና የፈጠራ ሰዎች ያስፈልጉናል። መምህራንና ሳይንቲስቶች ያስፈልጉናል። ስፖርተኞችና የሕክምና ባለሞያዎች ያስፈልጉናል። ፈላስፎችና የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች ያስፈልጉናል። የመረጃና የቴክኖሎጂ ባለሞያዎች ያስፈልጉናል።

ይህ የመከላከያ ኃይላችን፣ ኢትዮጵያዊ፣ ዘመናዊ፣ ሁለንተናዊና ዲሲፕሊን ያለው ሆኖ መገንባት አለበት። ኢትዮጵያዊ ስንል ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የሚሳተፉበት፣ በኢትዮጵያዊ ወኔና ዕሴት ላይ የተገነባ ማለታችን ነው። ዘመናዊ ስንል በሥልጠናው፣ በትጥቁና በአደረጃጀቱ ዘመኑ የደረሰበትን ደረጃ የያዘ፣ እንዲያውም ከነገ የቀደመ ማለታችን ነው። ሁለንተናዊ ስንል በሁሉም ዓይነት ኃይሎች፣ በሁሉም ዓይነት ዕውቀቶች፣ በሁሉም ዓይነት ዕዞች፣ በሁሉም ዓይነት ታክቲኮችና ቴክኒኮች የተሟላ ማለታችን ነው።

ከምንም በላይ መልካም ዲሲፕሊን ያለው ሠራዊት ያስፈልገናል። አንድን ሠራዊት “ሠራዊት” የሚያሰኘው ዲሲፕሊንና መርሆ ነው። ዲሲፕሊን የማይመራው የወታደሮች ስብስብ “ሠራዊት” ሊባል አይችልም። ለሠራዊት ዲሲፕሊንና መርሆ የጥንካሬው ምንጭ፣ የማሸነፉ ምክንያት፣ የአንድነቱ ገመድ፣ የነፍሱ ማረፊያዎች ናቸው። ያለ ዲሲፕሊን የወታደር ብዛት፣ የቴክኖሎጂ አቅም፣ የስትራቴጂ ረቂቅነት ልዩነት አያመጣም። ከእንግዲህ እነዚህ አራት ምሰሶዎች ላይ የቆመ ሠራዊት ከገነባን ያለ ጥርጥር ኢትዮጵያ አትደፈርም፤ በክፉ የሚያያትም ደጋግሞ ይጸጸታል። ይህ እንዲሳካ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ትግል ይፈልጋል። በተለይም ደግሞ እዚህ ያላችሁ መኮንኖች ትልቅ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡በተለይም ደግሞ የዛሬ ተሸላሚ መኮንኖች ትልቅ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡

የተሰጣችሁ ማዕረግ እና የተሸለማችሁት ሜዳልያ በመጀመሪያ ደረጃ በጦር ሜዳ ውሏችሁ የፈጸማችሁትን ጀብዱ ታሳቢ ያደረገ ነው። ለኢትዮጵያ ብሎ መዋደቅ፣ ለህዝብ ብሎ ዋጋ ለመክፈል መቁረጥ “ጀግና” ከሚል የክብር ስም ባለፈ፣ ጀብዷችሁ በማዕረግና በሜዳልያ መደገፉ ለእናንተ እንደ እውቅና ለሌሎች ደሞ እንደ ትምህርት ሆኖ ያገለግላል።

የሽልማቱ ሁለተኛ ምክንያት ቀብድ ነው። የእናንተ ጀግንነት በአንድ ጦር ሜዳ ላይ ብቻ ካከተመ ለእናንተም ለኢትዮጵያም ኪሳራ ይሆናል። ጀግንነታችሁ ተቋማዊ ቅርጽ እንዲይዝ፤ ትጋታችሁ ከግለሰባዊ እሴትነት አልፎ የሠራዊቱም እሴት እንዲሆን ከዛሬ ጀምሮ በርትታችሁ መሥራት አለባችሁ። በመሪነት ችሎታችሁ ተቋም እንድትገነቡበት፣ የሥራችሁ ፍሬ እንዲበዛ፣ እናንተን የመሰሉ በመቶና በሺዎች የሚቆጠሩ ጀግኖችን እንድታፈሩበት በማሰብ የተበረከተ ሽልማትና ማዕረግ ነው። ከእናንተ በኋላ የሚመጡ ጀግኖች የእናንተን ፈለግ ሲከተሉ ያኔ ጀግንነት በትውልድ ጅረት ላይ ኩልል ብሎ መፍሰሱን ይቀጥላል፡፡

በዚህ መልኩ የነጻነት ቀለም የሆነች ኢትዮጵያ፣ የክንደ ብርቱዎቹ እናት የተባለችው ሀገራችን፣ በልጆቿ ትንፋሽ ሰንደቅዋ እየተውለበለበ ለዘላለም ይኖራል።

Iኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ታኅሣሥ 30 ቀን 2014 ዓ.ም.

Leave a Reply