Site icon ETHIO12.COM

36 የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ ሲሞቱ 3 ሺህ 329 በቫይረሱ መተቃታቸው ይፋ ሆነ፤

ከ15 ወራት በላይ ስጋት ሆኖ የዘለቀው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ 36 የጤና ባለሙያዎችን ህይወት እንደነጠቀ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።በቫይረሱ 3 ሺህ 329 የጤና ባለሙያዎች ተይዘው እንደነበር እና ከነዚህም ውስጥ 36ቱ ህይወታቸው ማለፉን የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለሁ አባይነህ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ እስከ ሰኔ ሶስት ባለው ጊዜ በቫይረሱ ምክንያት 4 ሺህ 226 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል ተብሏል።ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ያሉት የጤና ሚኒስቴር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሐገራዊ የወረርሽኙን ስርጭት የሚያመላክተቱ ጥናቶች የሚቀርቡበት መድረክ ላይ ነው።

ወረርሽኙ ከባድ ጫና በሀገር ላይ ፈጥሯል ያሉት አቶ አባይነህ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተወሰዱ እርምጃዎች በቫይረሱ ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን የሞት መጠን መቀነስ እንዳስቻለም ጠቁመዋል።ምክትል ዳይክተሩ ወረርሽኙ ሲጀምር ምንም አይነት የመርመሪያ መሳሪያ ያልነበረ ሲሆን አሁን ላይ 82 የመንግስትንና የግል የላብራቶሪ ተቋማት የኮቪድ ምርመራ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ተናግረዋል።

የምርመራ ኪትም በሀገር ውስጥ እየተመረተ እንዳለ እና ይህም በውጭ ምንዛሬ እጥረት ይስተጓጎል የነበረውን የግዥ ሒደት ማስቀረት እንዳስቻለ ተነግሯል።የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እያገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።በቀጣይም በወረርሽኙ ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ጥንቃቄዎች ሊደረጉ ይገባል ተብሏል።

ኢቢሲ ዜና


Exit mobile version