Site icon ETHIO12.COM

ጭንቀት

stress

አንዳንድ ሰዎች በየምክንያቱ ይጨናነቃሉ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አብዛኛዎቹ የምንጨነቅባቸው ነገሮች ቀድሞውኑ መሰረት የሌላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌነት የሚከተለውን የአንድ ጥናት ውጤት እንመልከት፡፡ የምንጨነቅባቸው ነገሮች . . .

– 40% በፍጹም ለማይደርስብን ነገር …

– 30% ምንም ልንለውጠው ስለማንችለው ስላለፈው ነገር …

– 12% ሰዎች ስለእኛ ስለሚናገሩብን ፍርድ፣ ወሬና ሃሜት …

– 10% ስለጤንነታችን (ስለተጨነቅን የሚብስ) …

– 8% ስለእውነተኛ ልናስብበት ስለሚገባ ሁኔታ …

በፍጹም ለማይደርስብን ነገር …

ያለን አማራጭ ምክንያታዊነትን ማዳበር ነው፡፡ ሁኔታው ሊደርስብንና ላይደርስብን የሚችልበትን የእድል መጠን አመዛዝነን ያለመድረሱ ሁኔታ ካመዘነ፣ መጨናነቅን የማቆምን ሂደት መጀመርና እየተዉ መሄድ የግድ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን እንዲሁ ምክንያት ፈልገው የመጨነቅ “ሱስ” አለባቸው፡፡ ይህ ዝንባሌ የሚመጣው ለረጅም ጊዜ በአጣብቂኝ ሁኔታ ከማሳለፍና ስሜታችን የጭንቀት ሰለባ ሆኖ ከመክረሙም የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ፍጹም የማይደርስ ነገር ተለይቶ ሊታወቅና ከስሜታችን የደም ዝውውር ውስጥ ሊወገድ ይገባዋል፡፡

ምንም ልንለውጠው ስለማንችለው ስላለፈው ነገር …

ያለን አማራጭ ፈጽሞ አንዴ የሆነ ነገር መሆኑንና ምንም ብናደርግ ልንለውጠው እንደማንችል በመቀበል አእምሮን በአዳዲ ነገሮች መሙላት ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልፈለግን ግን እስቲ አንዴ የሆነውንና ያለፈውን ነገር ለመለወጥ የአንድ ወር ጊዜ እንስጠውና የምንችለውን ያህል እንሞክርና ካልቻልን ነገሩን ለመተው ለራሳችን እድል እንስጠው፡፡

ሰዎች ስለእኛ ስለሚናገሩብን ፍርድ፣ ወሬና ሃሜት …

ያለን አማራጭ መቆጣጠር የማንችለውን የሰውን ባህሪይ ለመቆጣጠር ከመጦዝ ይልቅ መቆጣጠር የምንችለውን የራሳችንን በሆነ ባልሆነው የመጨነቅ ዝንባሌ ለመቆጣጠር መስራቱ ይመረጣል፡፡ ሰዎች ስለአንተና በአንተ ላይ የሚሉት ነገር አንተ ካልፈቀድክለት በስተቀር ምንም ሊያደርግህም እንደማይችል አትዘንጋ፡፡ ብትችል ወሬው አንተ ጋር የማይደርስበትን መንገድ ፍጠር፡፡ ካልቻልክ ደግሞ ወሬው ወደ ስሜትህ የማይደርስበትን ጥንካሬ አዳብር፡፡

ስለጤንነታችን (ስለተጨነቅን የሚብስ) …

ያለን አማራጭ ስለጤነታችን የሚያሳስበን ሁኔታ ካለ ያንን ለማስቀረት ወይም ለመቀልበስ የምንችለውን ያህል መሞከር ነው፡፡ ጭንቀታችን ግን “ምናልባት እታመም ይሆን” የሚል ከሆነ፣ ይህ የራስ በራስ ትንበያ እንደሚፈጸም አትጠራጠር፡፡ ጭንቀት በሽታን የመሳብ ባህሪይ አለውና፡፡

ስለእውነተኛ ልናስብበት ስለሚገባ ሁኔታ …

ያለን አማራጭ በቅድሚያ፣ ሁኔታው በትክክልም የሚያሳስብና በቅጡ ካልያዝነውም የሚስጨንቅ ጉዳይ ስለሆነ ማሰባችንና በመጠኑም ቢሆን መጨነቃችን ትክክለኛው መሆኑን አምኖ መቀበል አስፈላጊ ነው፡፡ ሲቀጥል ያሳሰበንን ሁኔታ በምን መልኩ ብንጋፈጠው ልናሸንፈው እንደምንችል በሚገባ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ አእምሮን በጭንቀት ከመሙላት ይልቅ ትክክለኛውን ምላሽ በማሰብ መሙላት በብዙ እጥፍ ይመረጣል፡፡ በጉዳዩም ላይ ሰውን ማማከሩም አንዱ መንገድ ነው፡፡

Dr. Eyob Mamo FB

Exit mobile version