በአባቷ የቀብር ስነስርዓት ላይ ለጓደኛዉ የታገቢኛለሽ ወይ? ጥያቄ ያቀረበዉ ግለሰብ አነጋጋሪ ሆኗል

በአባቷ ቀብር ላይ ለጓደኛዉ ቀለበት ያሰረዉ ደቡብ አፍሪካዊ ከሀገሩ እንዲሁም ከሌሎች የዓለማችን ክፍል ነዋሪዎች ዘንድ ከባድ ትችትን እያስተናገደ ይገኛል፡፡

ስለጋብቻ ጥያቄዎች ስናስብ ሁሌም ቢሆን አብሮ የሚታሰበዉ ነገር ቦታ እና ግዜ ነዉ፤ እናም የቀብር ቦታዎች ይህ ጥያቄ የሚቀርብባቸዉ ቦታዎች እንዳልሆኑ ይታመናል፡፡ ነገር ግን ይህ ጉዳይ ይህን ደቡብ አፍሪካዊ በጋብቻ ጥያቄ ታሪክ ዉስጥ እጅግ አሳፋሪዉን የታገቢኛለሽ ጥያቄ ከመጠየቅ አላስቆመዉም፡፡

በአባቷ የቀብር ስነስርዓት ላይ ተንበርክኮ ታገቢኛለሽ ብሎ ሲጠይቃት የሚያሳየዉን አስደንጋጭ ቪድዮ የቀብር ስነስርዓቱ ላይ የተገኘች አንዲት ሴት ቀርጻ ወዲያዉ በቲክቶክ የማህበራዊ መገናኛ ላይ ከለቀቀች በኋላ፤ እጅግ በርካታ ሰዎች እንደተቀባበሉት እና ብዙ ተጠቃሚዎችም ትችቶችን እንደሰነዘሩበት ኦዲቲ ሴንትራል ነዉ የዘገበዉ፡፡

ቪድዮዉ ላይ የሚታየዉ የአባቷ አስከሬን ሳጥን ፊት ቁጭ ብላ በማልቀስ ላይ የምትገኘዉ ጓደኛዉን ተንበርክኮ የታገቢኛለሽ ጥያቄ ሲያቀርብ ነዉ፡፡
ማይክራፎን በመጠቀምም ንግግር ያደርግ እና የሌሎች ሹክሹክታ እና ተቃዉሞ አንዳች ሳያግደዉ ቀለበት አዉጥቶ በጣቷ ላይ ሲያጠልቅ ያሳያል፡፡

ጓደኛዉ በፍጹም ድንጋጤ ዉስጥ ሆና የምትታይ ሲሆን ምንም ዓይነት ምላሽ ባለመስጠቷም የጋብቻ ጥያቄዉን ትቀበል አትቀበል ምንም ግልጽ የሆነ ነገር የለም፡፡ በቦታዉ እየሆነ ያለዉን ነገር በስርዓቱ ለማጣጣም በትክክለኛዉ የስሜት ሁኔታ ላይ እንዳልነበረችም በግልጽ ይታይ ነበር፡፡
ብዙዎች በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸዉን እየሰጡ ሲሆን በሁለት ጎራ የተከፈሉ ሰዎች መኖራቸዉንም ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቦታል፡፡

ግማሹ ‹‹የሰራዉ ስራ ፍጹም ንቀት መሆኑን እና ሰዓቱም በፍጹም ተገቢ እንዳልነበር›› ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ ‹‹በአባቷ ሀዘን ልቧ የተሰበረዉ ጓደኛዉን በዚሀ በህይወቷ ባጋጠማት ከባድ ግዜ ላይ አብሯት መሆኑን ያሳየበት መንገድ ነዉ›› ሲሉ ድጋፋቸዉን እየገለጹለት ይገኛል፡፡

‹‹ምንም ያህል ትክክል ነዉ ብላችሁ ለማሳመን ብትጥሩም ብትሞክሩም ይህ ግን በፍጹም ስህተት ነዉ ››ስትል አንዲት ሴት ሀሳቧን ገልጻለች፡፡

‹‹ይህ ጉዳይ በየትኛዉም መንገድ ቢታይ ካደረገዉ ነገር ንቀት ብቻ ነዉ ገዝፎ ሊታይ የሚችለዉ›› ሲል ሌላ ሰዉ ሀሳቧን ደግፏል፡፡

ያደረገዉ ነገር ምንም ያህል ከባድ ቢሆንም እንኳን ከጎንህ ነን ብለዉ ድምጻቸዉን እያሰሙ ያሉ ሌሎች ሰዎችም አልጠፉም፡፡

‹‹ሰዎች ይህ ሰዉ እኮ በሞተዉ አባቷ ፊት ነዉ ላግባሽ ብሎ የጠየቃት፣ ይህን በማድረጉ ላይ ደግሞ ምንም ችግሩ አይታየኝም ፡፡ ከልባችሁ ሀይማኖተኛ ከሆናቹ ይህንን መረዳት ትችላላችሁ›› ሲል አንድ ደቡብ አፍሪካዊ ድጋፉን ገልጿል፡፡

‹‹እኔ በበኩሌ ምንም ጥፋት አይታየኝም ፡፡ የቤተሰቡን ዕንባ ለማበስ ነዉ እየሞከረ ያለዉ፡፡ ይህንንም ማድረጉ ደግሞ ጀግንነት ነዉ›› ሲል ሌላም ሰዉ ያደረገዉን ነገር እንደሚደግፈዉ ገልጿል፡፡

ምንጭ፡- ኦዲቲ ሴንትራል በእስከዳር ግርማ ethioFM 107.8

You may also like...

Leave a Reply