Site icon ETHIO12.COM

“እንዲህ አይነት ግፈኞች እውነት በኢትዮጵያ ምድር ነው ወይ የበቀሉት ” ጋዜጠኛ ያሬድ

የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች የጭካኔ ጥግ ፍጹም ከሰዋዊ ባህሪ ያፈነገጠ መሆኑን አስመልክቶ “ህወሓትን መሰል ጨካኞች ከኢትዮጵያ ምድር መብቀላቸው አስገራሚ ነው” ሲል የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን በደል በጋይንት ግንባር ተገኝቶ የተመለከተው ትውልደ ኢትዮጵያዊው የካናዳ ዜጋ ጋዜጠኛ ያሬድ አድማሴ ይናገራል፡፡

በካሜራ ጋዜጠኝነት ሙያ ከ18 ዓመታት በላይ ልምድ እንዳለው የሚናገረው፤ ከከናዳ ተነስቶ ወደ ትውልድ አገሩ ኢትዮጵያ በመምጣት የአሸባሪውን ግፍ ለዓለም ማህበረሰብ ለማድረስ በተለይ በጋይንት ግንባር ተገኝቶ የሆነውን ሁሉ መመልከቱን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጿል፡፡ በአይኑ የተመለከተው የአሸባሪው በደል “እንዲህ አይነት ግፈኞች እውነት በኢትዮጵያ ምድር ነው ወይ የበቀሉት የሚል ጥያቄ አስነስቶብኛል” ይላል፡፡

የአሸባሪው ህወሓት ግፍ አዕምሮው ውስጥ መቅረቱን፣ የአርሶ አደሮች ፍርስራሽ ቤቶች ምስልም አይኑ ላይ መሆኑን የሚናገረው ጋዜጠኛ ያሬድ፤ የደረሰው በደል ኢትዮጵያዊያን ተብለው ከሚጠሩ ዜጎች ፈጽሞ የማይጠበቅ ይልቁንም የሆነው ነገር የሚዘገንን፣ ስሜታዊም የሚያደርግና በሰው ልጅ ይሰራል ተብሎ የማይታሰብና ከዚህ ቀደም በካርቱን ፊልም ላይ ሲታይ የነበረው አይነት ድርጊት መሆኑን አመላክቷል፡፡

በእምነት ተቋማት ላይ በካባድ ማሳሪያ የታገዘ ጥቃት፣ የጤና ተቋመትን ሙሉ ለሙሉ መዝረፍና ማውደም፣ ከተሞች ውስጥ በመመሸግ ነዋሪውን ቤት አልባ ማድረግ፣ እድሜያቸው ከ15ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን ወደ ጦርነት አውድማ ማምጣት፣ ነፍሰ ጡሮችን በማስገደድ መሳሪያ አሸክመው እንዲዋጉ ማድረግ፣ የንጹሐንን ሀብት ንብረት ማሸሽና ማውደም የመሳሰሉት አሸባሪው በጋይንት ግንባር ስለመፈጸሙ ማረጋገጡን ጋዜጠኛ ያሬድ አስታውሷል፡፡ ድርጊቱም እጅጉን አሳዛኝ ስለመሆኑ ነው የገለጸው፡፡

እንደ ጋዜጠኛ ያሬድ ማብራሪያ፤ አሸባሪው ሂሳብ የማወራረድ ዓላማውን ዘር ለማጥፋት ባደረገው ድርጊት ገልጿል፡፡ አርሶ ላበላው ሳይራራ የአርሶ አደርን ንብረት በሚያሳዝን ሁኔታ ዘርፏል፤ የቀረውንም አውድሟል፡፡ አሸባሪ ቡድኑ ይህን በደል ሲፈጽም፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ወንጀለኛ አመራሮቹን ዕድሜ ለማራዘም ነው፡፡

ጋዜጠኛ ያሬድ፤ ባለው ጊዜ ይሄንን ግፍ ማየቱንና ለዓለም በማድረስ በሙያው በማገለግል የሃገሩን ህልውና ለማስጠበቅ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ይቆጥረዋል፡፡ ከዚህም በላይ የአሸባሪውን በደል እየተከታተለ ለዓለም ማህበረሰብ ለማድረስ ቁርጠኛ ስለመሆኑም አስታውቋል፡፡ የአገር ነቀርሳ የሆነው አሸባሪው ቡድን ያደረሳቸው ግፍ በርካታ በመሆናቸውና እነዚህን ሁሉ ሰንዶ ለዓለም ህዝብ ለማሳየት ወደ ካናዳ የሚመለስበትን ጊዜ እንዳራዘመም ገልጿል፡፡ በደላቸውን የውጭው ማህበረሰብ እንዲያውቀው ለዘሀበሻ፣ ቶሮንቶ ለሚገኘው ብርሀን ቲቪ አንዲሁም ለኢሳት እና ሌሎች የውጭ ሚዲያዎች መረጃዎችን እንደሚያስተላለፍም ነው የተናገረው፡፡

ምንም እንኳን አብዛኞቹ የውጭ መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሚዛናዊነት ቢጎድላቸውም፤ እንደርሱ ያሉ ለኢትዮጵያ ጥቅም የቆሙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ዳያስፖራዎች አሸባሪው የሰራውን ግፍ በማጋለጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊወጡ እንደሚገባም ጥሪ አቅርቧል፡፡

አሸባሪው በሚዲያ ተዘግቦ የማያልቅ መጥፎ ታሪክ መስራቱን በመጥቀስ፤ ክፋቱም ለዓለም ህዝብ መቅረብ እንዳለበትና አሸባሪዎቹም በዓለም የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መጠየቅ እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የውጭ መገናኛ ብዙኃን አሸባሪው ወረራ ባካሄደባቸው አካባቢዎች ያደረሰውን በደል እንዲዘግቡ የሚመለከተው አካል እድሉ መመቻቸት አለበት ሲልም መክሯል፡፡

አዲሱ ገረመው

Exit mobile version