Site icon ETHIO12.COM

በዩክሬን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወደ ፖላንድ እየተጓዙ ነው

ጦርነት በተቀሰቀባት ዩክሬን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወደ ፖላንድ ጉዞ መጀመራቸውን በጀርመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለቢቢሲ አስታወቀ።

ኤምባሲው ኢትዮጵያውን ተማሪዎች ወደ ፓላንድ እንዲሻገሩ ከፖላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግባባት ላይ መደረሱን ተከትሎ ጉዞ የጀመሩ መሆኑንም በኤምባሲው ምክትል የሚሲዮን መሪ የሆኑት አምባሳደር ተፈሪ ታደሰ ተናግረዋል።

የሩሲያ ኃይሎች ወደ ዋና መዲናዋ ኪዬቭ ምገባታቸው እየተነገረ ካለችው ዩክሬን ወደ ፖላንድ ለመውጣት በሚደረገው ሙከራ ከፍተኛ የሆነ የትራፊክና የመኪና መጨናነቅ ስላለ መንገድ ላይ መሆናቸውን ነው አምባሳደሩ ጉዞ ከጀመሩ ተማሪዎች ተወካይ የተረዱት።

ጦርነቱ እየተጋጋለና ከ130 ሰዎች በላይ በተገደሉባት ዩክሬን ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ማንኛውም የመንገደኛ በረራዎች በመቋረጣቸውም ያለው አማራጭ በመኪና መጓዝ መሆኑን ገልጸው፣ ሆኖም ተማሪዎቹ በሰላም እየተጓዙ መሆኑንም አምባሳደሩ ተረድተዋል።

በተለይም ወደ ፖላንድ ድንበር አካባቢ የሚገኙት ተማሪዎች እንቅስቃሴ የጀመሩ ሲሆን ሆኖም አንዳንድ በተዘጉ ስፍራዎች ላይ ያሉ ተማሪዎች መረጋጋት እስከሚፈጠር ድረስ የተወሰነ ጊዜ ሊቆዩ እንደሚችሉም አክለው ገልጸዋል።

አጠቃላይ በተደራጀ መልኩ መረጃቸውን ማግኘት አዳጋች በመሆኑ በዩክሬን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ቁጥር በትክክል ማግኘት እንዳልቻሉ የገለጹት አምባሳደሩ፣ እስካሁን ባለውም ከ40 አስከ 50 የሚሆኑት ተማሪዎች ፖላንድ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ከተማሪዎች ተወካዮች በተሰጣቸው መረጃ መሰረት ወደ አርባ የሚሆኑ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን ሌሎች ተጨማሪ ተማሪዎች ከመጡ በድረገፃቸው አማካኝነት መረጃዎችን ወደ ፖላንድ ለማሳለጥ ኤምባሲያቸው ዝግጁ መሆኑንም ያስረዳሉ።

ተማሪዎቹ ፖላንድ ከደረሱም በኋላ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ የገለጹት አምባሳደር ተፈሪ ከፖላንድ መንግሥት ጋር የተደረገውም ስምምነት ይህንኑ ነው የሚመክረው።

ተማሪዎቹ ፖላንድ ከገቡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ጉዞም ቲኬታቸውን ራሳቸው እንደሚገዙና ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ዝግጁ እንደሆኑም አምባሳደሩ ከተወካዮቻቸው መረዳት ችለዋል።

በአሁኑ ወቅት ዩክሬን ውስጥ ስላሉበት ሁኔታ ቢቢሲ ያናገራት በኪዬቭ ያለችው ተማሪ እሌኒ አብሮም እንደገለጸችው፣ ሁሉም ወዴት እንደሚሄዱ ግራ መጋባታቸውንና በጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን ጠቁማ፤ የተወሰኑት ወደ ፖላንድ ድንበር መጓዛቸውን ተናግራለች።

አምባሳደሩም ተማሪዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጭንቀት ላይ እንደነበሩ ገልጸዋል።

“ጦርነቱ ያልተጠበቀና በዚህ ወቅት ይፈጠራል ያልተባለም ከመሆኑ አንፃር ቅድመ ዝግጅት አላደረጉም። መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ጭንቀት ነበር። ከኤምባሲው ጋር ከተገናኙ በኋላ በየጊዜው እየተከታተልን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እየመከርን ነው ያለነው” ብለዋል።

መጀመሪያ ላይ የተማሪዎቹ ስጋት የነበረው የፖላንድ መንግሥት ወደ አገሪቱ እንዲሻገሩ አይፈቀድም የሚል የነበረ ቢሆንም፣ በጀርመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፖላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ሁኔታዎችን ካመቻቸ በኋላ በተወሰነ መልኩ መረጋጋት እንዳለ አምባሳደር ተፈሪ ገልጸዋል።

“እንደ ማንኛውም በጦርነት ውስጥ እንደሚኖር ሰው ያልተጠበቀ ስለነበር የድንጋጤ ስሜት መፈጠሩ የሚጠበቅ ነው” ብለዋል።

በዩክሬን ከተማሪዎች ውጪ በሥራ ወይም ኑሯቸውን በዩክሬን ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ይኖሩ ይሆን ወይ? በሚል ቢቢሲ አምባሳደሩን ጥያቄ ያቀረበላቸው ሲሆን እሳቸውም “እኛ ባለንም መረጃ በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ተማሪዎች ናቸው። ከእነሱም ጋር ግንኙነት አለን” ብለዋል።

ተማሪዎቹን በሰላም ወደ አገራቸው ለመመለስ ኤምባሲው ቡድን አቋቁሞ በትኩረት እየተከታተለ እንደሚገኝ የገለጹት አምባሳደሩ ተፈሪ ታደሰ፣ ተማሪዎችም ሆነ የተማሪ ቤተሰቦች በኤምባሲው ፌስቡክ ገፅ በተቀመጠው እንዲሁም በስልክ ማንኛውንም ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለትምህርት ዩክሬን የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን፣ ከፍተኛው ቁጥር የሞሮኮ ተማሪዎች ሲሆኑ (8,000)፣ ናይጄሪያ (4,000) እና ግብፅ (3,500) ሲሆኑ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ዩክሬን ውስጥ እንደሚገኙ ቢቢሲ አረጋግጧል።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ባለው ጊዜ አስካሁን አገራት ተማሪዎቻቸውን ማስወጣት አልቻሉም። በጀርመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፖላንድ መንግሥት ጋር በመተባበር ተማሪዎቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በቅርበት እየተከታተለ ነው።

ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በጀርመን በርሊን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዩክሬን ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ደኅንነት ለመከታተል በስልክና በኢሜል ሪፖርት እንዲያደርጉለት ጠይቋል። ዘገባው የቢቢሲ ነው

Exit mobile version