ETHIO12.COM

በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ 342 የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

በአማራና አፋር ክልሎች አሸባሪው ህወሃት ወረራ በፈጸመበት ወቅት ጉዳት ያደረሰባቸው 342 የጤና ተቋማት ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በማስተሳሰር በተደረገላቸው ድጋፍ አገልገሎት መስጠት መጀመራቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የፌዴራል እና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሆስፒታሎችን ከተጎዱ የጤና ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ድጋፍ እንዲያደርጉ እያስተባበረ ይገኛል።

በዚህም የመድሃኒትና ሌሎች የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ በማድረጋቸው 38 ሆስፒታሎችና 304 ጤና ጣቢያዎች በአፋርና አማራ ክልሎች መደበኛ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን በሚኒስቴሩ የሜዲካል አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ህሊና ታደሰ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ቀሪዎቹን ወደ ነበሩበት አገልግሎት ለመመለስ ሚኒስቴሩ መሰል ተቋማትን በማስተሳሰር የተጀመረው ስራ እንዲቀጥል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በድጋፉ ከመንግስት በተጨማሪ የግል ጤና ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ አካላት እየተሳተፉ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ እየተደረገ ያለው በሶስት ምዕራፎች ተከፍሎ ሲሆን፤ በመጀመሪያው የነፍስ አድንና ድንገተኛ ህክምና፣ በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ መሰረታዊና መደበኛ የህክምና አገልግሎቶችን ማስጀመር እንደሆነ አስረድተዋል።

በሶስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ሁሉንም የተጎዱ የህክምና ተቋማትን ወደ ቀድሞ ቁመናቸው ሙሉ በሙሉ ከመመለስ ባለፈ ከዚህ ቀደም ያልነበራቸውን የጤና አገልግሎት ጭምር እንዲሰጡ ለማስቻል እንደሚሰራ ነው ዳይሬክተራ ያብራሩት።

በክልሎቹ አሸባሪው ቡድን ጉዳት ያደረሰባቸው የጤና ተቋማት በአፋጣኝ ወደ ሙሉ አገልግሎት ለመመለስ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ዶክተር ህሊና አስታውቀዋል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version