Site icon ETHIO12.COM

በኢድአልፈጥር በዓል የጭስ ቦንብ በማፈንዳት ወንጀል የተጠረጠረው ፖሊስ ፍርድ ቤት ቀረበ

በአዲስአበባ በተከበረው በኢድአልፈጥር በዓል ላይ በመስቀል አደባባይ አካባቢ የአድማ ብተና የጭስ ቦንብ በማፈንዳት ወንጀል የተጠረጠረው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ስር ውሎ ፍርድ ቤት ቀረበ።

የፌደራል ፖሊስ አድማ ብተና ዘርፍ አባል የሆነው ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ ከትናንት በስቲያ ሰኞ በአ/አ በተከበረው የኢድአልፈጥር በዓል ላይ በመስቀል አደባባይ የሰማዓታት መታሰቢያ ሙዚየም አካባቢ ከፈነዳው የአድማ በታጭ የጭስ ቦንብ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ስር ውሎ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ ረፋድ ላይ ቀርቧል።

መርማሪ ፖሊስ ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ በኢዳል አፍጥር በዓል ዕለት በተመደበበት ወንጀል የመከላከል ምደባ ላይ እያለ የታጠቀውን አድማ በታኝ የጭስ ቦንብ በአግባቡ መታጠቅ ሲገባው በአግባቡ ባለመታጠቅ የጭስ ቦንቡ እንዲፈነዳና ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር አድርጓል ያለው መርማሪ በዚህ በተፈጠረ ሁከትና ብጥብጥ የመንግስትና የግለሰብ ንብረት ጉዳት መድረሱንም አብራርቷል።

በተጠረጠረበት ሁከትና ብጥብጥ ማስነሳት ወንጀል ለተጨማሪ ማስረጃ አሰባስቦ ለመቅረብ 14 ቀን እንዲሰጠው መርማሪው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ በበኩሉ በዕለቱ አስቀድሞ በተመደበበት ቦታ ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ጀምሮ በስራ ላይ እንደነበር እና በሰዓቱ በቦታው ላይ የነበሩ ሰዎች ቁጥር መጨመርና መጨናነቁን ተከትሎ ከታጠቀው ሶስት አድማ በታኝ የጭስ ቦንብ ውስጥ አንደኛው በማያውቀው ሁኔታ መሬት ላይ ወድቆበት በድንገት መፈንዳቱን ገልጿል።

ሆኖም ምንም አይነት ተንኮልም ሆነ ክፋት በውስጤ አልነበረም ወድቆ ሲፈነዳ እኔ እራሴ ደንግጬ ነበር ሲል እያለቀሰ ሁኔታውን ለችሎቱ አስረድቷል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪው ወላጆቹን በሞት ማጣቱን ገልጾ እህትና ወንድሙን በሱ እርዳታ እያስተማራቸው እንደሆነ እና ከለሊት 7:00 ጀምሮ ለጥበቃ ስራ ከመሰማራቴ ውጪ ሌላ ክፋት በውስጤ የለም ሲል ለችሎቱ አብራርቷል።

ጉዳዩን የተከታለው ፍርድ ቤቱ ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ 14 ቀን ፈቅዷል።

ለግንቦት 10 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል።

Via Tarik Adugna

Exit mobile version