Site icon ETHIO12.COM

“ሃያ አንዱ ማኅበራዊ ሕግጋት ●●●

በዶ/ር ምህረት ደበበ

1. ይሰለቹሃል አስሬ አትደውል፤ ሰዎች ጋር ከሁለቴ በላይ አይደወልም። ተሰልቺ ትሆናለህ!

2. ‘ሼም ነው’ የሚከፍለው ሌላ ሰው ነው ብለህ ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ምግብና መጠጥ አትዘዝ!

3. አይባልም “… እንዴ እስካሁን አላገባሕም? ለምንድነው እስካሁን ያልወለድሽው? እንዴት ዲግሪሽን እስካሁን ሳትይዢና ሳትይዝ ወዘተ…” አይባልም።

4. ክፈል አብሮህ ላለው ሰው ታክሲ ላይም ሆነ የትም ቦታ አግባብ ነው ብለህ ስታምን ቀድመህ ክፈል። ገና ለገና ይከፍላል ብለህ ከሱ ስትጠብቅ ደምህን እያሯሯጥክ ትሰቃያለህ።

5. ነውር ነው ሰው እየበላም ይሁን በማንኛውም ሰዓት ከሰዎች ጋር ካለህ ጥርስህን አትጎርጉር፣ አፍንጫህንና ሌሎች ያልተገቡ ቦታዎችንም አትነካካ።

6. አታቋርጥ ግዴለህም አብሮህ ያለው ሰው አውርቶ ይጨርስ። ጥልቅ እያልክ አታቋርጥ።ከባሕልም ከስልጣኔም ውጪ ነው።

7. አታብሽቅ ሆን ብለህ የማናደድ ባሕሪ ካለህ ተው። ሰዎች ለመባል የማይወዱትን ተው።ሰዎች ብዙ የማይናገሩትና የተሸከሙት የራሳቸው ብሽቀት ስላለባቸው ለተሻለውና ለሚበረቱበት ሕይወታቸው አድናቆት ስጥ።

8. አመሥግን ለተደረገልህ ማንኛውም ቅንጣት ነገር አመሥግን።

9. ያለስስት አድንቅ ሰዎችን በይፋ አድንቃቸው፣ መልካም ያልሆነ ነገራቸውን ግን በግል አውራቸው።

10. ክፉ አስተያየትህን ቆጥብ ያልሆነ ነገር ብታይ እንኳን አፍህ በበጎ ቃላት ይቀይረው። ወፍሮ ያየኸውን ሰው ኤጭ ተዝረጠረጥክ ከማለት ተቆጠብ።

11. ካልሆኑ ጥያቄዎች ታቀብ ሰዎች የሕክምና ቀጠሮ ሄደው መምጣታቸውን ነግረውህ ይሆናል። የውጤቱን

ምንነት ለማወቅ ግን በጥልቀት አትጠይቅ። በነገሩህ ልክ መልካሙን ተመኝላቸው። በቻልከው መጠን በመረጃና በጥቆማ አግዛቸው እንጂ ድንበር አትዝለል።

12. ስነ-ስርዓት ሰዎች ከስልካቸው ላይ ፎቶ እንድታይ ቢሰጡህ ከፈቀዱልህ ውጪ ሌላ ፎቶ ካላየሁ ብለህ ስልክ አትፈትሽ። ሁሉም ሰው ታልፎ እንዲገባበት የማይፈልገው የራሱ አጥር አለው።

13. ክብር ለሁሉም ከላይ ጫፍ ላለ የሥራ ኃላፊና ከታች ዝቅ ባለ ስራ ላይ ለሚገኘው ሰው እኩል ክብር ስጥ። እንደውም ከላይ ካለው ይልቅ ታች ላለው ሰው የሰጠኸው ክብር ብዙ እውቅና አለው። ለንቀትህ ግን የማንንም አድናቆትና ጭብጨባ አታገኝም።

14. ስልክህን አስቀምጥ ሰዎች በቀጥታ ላንተ እያወሩ ስልክህን የምትነካካ ከሆነ ቀሽምነት ነው። ከሰው

ሰራሹ ይልቅ ራሱ ሰው ትልቅ ዋጋ አለው።

15. አድብ ሰዎች ካልጠየቁህና ካልፈቀዱልህ በስተቀር በራሳቸው ሕይወትና ሥራ ጣልቃ አትግባባቸው።

16. ተቆጠብ ከረጅም ጊዜ በኋላ ያገኘሃቸውን ሰዎች አስጨናቂ ጥያቄ አትጠይቃቸው። ሰዎች ቆይታቸውን እንዲሁም ዕድሜና ደሞዛቸውን ጨምሮ የመናገርና ያለመናገር ብቸኛ ባለመብት ራሳቸው እንደሆኑ እወቅ።

17. መነጽርህን አውልቅ ከሰዎች ጋር በዓይንህ አውራ። ከማንም ጋር በመንገድ ላይ ተገናኝተህ ስታወራ መነጽርህን ከዓይንህ ማንሳት እንዳለብህ አስታውስ። ክብርም ነው!

18. አትሳሳት በድኅነት አስተሳሰብ ሆነህ ስለሀብታሞች ምንነትና ማንነት አታውራ፤ ልጅ ሳይኖርህ ስለልጅና ልጅ ስላላቸው ሰዎች ባሕሪ አትፍረድ።

19. ለስልክ መልዕክት ምላሽ መስጠት በስልክህ የጽሑፍ መልዕክት ሲደርስህ አንብበህ ዝም ማለት ነውር ነው።ተገቢውን ምላሽ በበጎነት ቃል መመለስን ልማድህ አድርገው።

20. ዕቃ መልስ የወሰድከውን ማንኛውም ቁስ ባለቤቱ ሳይጠይቅህ በፊት ቶሎ መልስ።

21. አማራጭ ሐሳቦች ሁሌም አሉ የያዝከውን ሐሳብ ሳትፈራ አውጣው። አንተም ሐሳብህም ትጎለብታላችሁ።

Exit mobile version