Site icon ETHIO12.COM

አቶ አንዱአለም አራጌ የሚኮንነው የትኛውን ፕ/ር ብርሀኑ ነው?

ኢዜማ ሲመሰርት “ፕ/ር ብርህኑ ነጋ አንተ መሪ መሆን አለብህ ብለው ሀሳብ እና ጥያቄ ሲያቀርቡልኝ፤ አይ እኔ ከምሆን አንተ ብዙ ተመክሮ ያለህ ስለሆንክ ካንተ ስር ሆኜ መማር ስለምፈልግ መሪነቱን አንተ ብትወስድ ይሻላል፤ ብየዋለው” አቶ አንዱአለም አራጌ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ሀሳብ ባልሰጥ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፤ ምክንያቱም ይሄ ጉዳይ ይበልጥ የባለጉዳዮቹ እና የፓርቲው አባላቶች ስለሆነ፤ ነገርግን በአጋጣሚ ትናንት በሰጠውት አስተያየት ላይ ተነስተው በርካታ ጥያቄዎች ስለቀረበለኝ እስኪ አንዱን አንስቼ ሀሳቤን ላካፍላችሁ፡፡

እንደሚታወቀው አቶ አንዱአለም አራጌ ፕ/ር ብርሀኑን ለመኮንን እና ስም ለማጥፋት በርካታ ጉዳዮችን ቢያነሳም በተለይ “እስከ አሁን ባለው የፕ/ር ብርሀኑ አመራር ውስጥ መሪን የመፍጠር ባህል የላቸውም፤ በግንቦት 7ትም አሁንም በኢዜማም ከስር ተተኪ መሪዎችን የማፍራት ባህል የላቸውም” በሚል ወቀሳውን ያቀረበውን እንየው፡፡

እንደሚታወቀው የፕ/ር ብርሀኑ በፓለቲካው ዙሪያ ያለ ታሪክ በአጨሩ እንደሚያሳየን ከሆነ ፕ/ር ብርሀኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተማሪ በነበሩበት ወቅት በርካታ ወጣት ተማሪዎች ከልክ ያለፈ ይወዷቸው ነበር፡፡ ፕ/ሩ የሚያገኙትን ደሞዝ ለችግረኛ ተማሪዎች ከመስጠት አልፈው፤ ፕ/ሩ በጣም ያስወደዳቸው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ ከወጣት ተማሪዎች በጣም ተቀራርበው እየሰሩ ትምህርት ይሰጡ እንደነበር እና ተማሪዎች የሚገጥማቸውን በትምርህትም ይሁን በሌላ ማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ቀርበው በመስራት ተማሪዎችን ይረዱ እና በርካታ ወጣት ተማሪዎች ከእውቀት ባሻገር በስነ ልቦና ጠንካራ ሆነው እንዲወጡ መሪ በመሆን ታሪክ መለወጥ እንደሚችሉ ያበረታቱ እና ያደርጉ እንደነበር ዛሬ ድረስ የሚመስክሩላቸው የቀድሞ ተማሪዎች አሉ፡፡

ሌላው አቶ አንዱአለም ራሱ መጀመሪያ ከፕ/ሩ ጋር የተዋወቀው በኢኮኖሚ ማህበር ውስጥ ሲሆን በዚህ ማህበር ውስጥ ፕ/ሩ ከልክ በላይ እውቅና የቸራቸው በመርህ ላይ ቆመው መንቀሳቀሳቸው ብቻ ሳይሆን በርካታ ወጣቶች ወደ ሀላፊነት እንዲመጡ በማድረግ እና ወጣቶችን መስራት እና ሀገር መቀየር እንደሚችሉ የሚያበረታታ እንደነበረ አብረዋቸው የሰሩ የነበሩ በርካታ ወጣቶች አሁንም ድረስ ይመሰከራሉ፡፡

ሌላው በቅንጅት ግዜ ኢንጂነር ሀይሉን ጨምሮ በድርጅቱ የነበሩት በርካታ የእድሜ ባለጸጋ የነበሩት ግለሰቦች በእድሜያቸው ብቻ ስልጣንን መያዝ አለብን የሚል አባዜ እየተጠናወታቸው ወጣቶች ወደ ሀላፊነት እንዳይመጡ ሲያደርጉ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ በርካታ ወጣቶች በሀላፊነት እንዲሰሩ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ አቶ ሙሉነህ እዮኤል እንዲሁም አቶ ልደቱ አያሌውን እና አሁን ስማቸውን የሚያጠፋውን አቶ አንዱአለም አራጌን ጨምሮ ወደ ሀላፊነት መተው እንዲሰሩ ከፍተኛ ጥረት ያደረገ እንደሆነ ስለድርጅቱ ሀቅን መመስከር የሚፈልጉ የቀደሞ አባላቶች የሚያውቁት ጥሬ ሀቅ ነው፡፡

በግንቦት 7 ውስጥም ቢሆን ፕ/ር ብርህኑ ከበርካታ ወጣቶች ጋር አብሮ መስራት መውደዱ ብቻ ሳይሆን ወጣቶችን በየግዜው በድርጅቱ ውስጥ ሀላፊነትን እንዲወስዱ ይሰራ የነበረና በርካታ ተተኪ የሆኑ ወጣቶችን እንዳፈራ ድርጅቱን ከናካቴው ምንም የማያውቀው አቶ አንዱአለም ሳይሆን አሁን ድረስ በህይወት ያሉ በርካታ የድርጅቱ አባላቶች የሚያውቁት ሀቅ ነው፡፡ ገና ድርጅቱ ሲቋቋም አመራር ውስጥ በርካታ ውጣቶች ያካተተ ሲሆን ከዚህም ውስጥ አንዱ ከድርጅቱ አለ አግባብ ገንዘብ በማባከን የወጡት እና በኋላም የባልደራስ አውሮፓ ተወካይ ሆነው የሰሩትና ባልደራስንም ጥለው የወጡት አሁን ነዋሪነታቸው በአውሮፓ ሆላንድ አምስተደርዳም የሁኑት አቶ መስፍን አማን ናቸው፡፡

ኢዜማንም ይሁን ገና ከመመስረቱ በርካታ ወጣቶችን በየወረዳው ብቻ ሳይሆን ለከፍትኛ የስልጣን ሀላፊነትንም ጭምር እንዲሰሩ ከፍተኛ ግፊት ማድረግ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ውጥስ ካሉ የድርጅቱ ወጣት አባላቶች ጋር በቅርበት ይሰሩ እንደነበር አሁንም ድረስ ይሄንን ሊመሰክሩ የሚችሉ የድርጅቱ አባላቶች አሉ፡፡

በዚህ ላይ ራሱ አቶ አንዱአለም አራጌ ድርጅቱ ሲመሰረት “ፕ/ር ብርህኑ ነጋ አንተ መሪ መሆን አለብህ ብለው ሀሳብ እና ጥያቄ ሲያቀርቡልኝ፤ አይ እኔ ከምሆን አንተ ብዙ ተመክሮ ያለህ ስለሆንክ ካንተ ስር ሆኜ መማር ስለምፈልግ መሪነቱን አንተ ብትወስድ ይሻላል፤ ብየዋለው” በሚል በአንደበቱ መስክሮለት የነበረው ሀቅ ነው፡፡

ታዲያ አቶ አንዱአለም አራጌ መሪ የመፍጠር ባህል የላቸውም ብለው የነገረን እና ስም ያጠፋው የትኛውን ፕ/ር ብርሀኑ ነጋን ነው?

By Desu Assefa Abdi – pinion

Exit mobile version