ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አያሌ ኪሎ ሜትሮች አቆራርጣችሁ ለሁለት ቀናት በዚህ ታላቅ ጉባዔ ላይ የታደማችሁ የተከበራችሁና የተወደዳችሁ የጉባዔ አባለት፣ አንደኛ መደበኛ ጉባዔያችንን በአማረና በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ በመቻላችን እንኳንም ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ ያለን ለማለት እወዳለሁ፡፡

ኢዜማ ለሀገራችን እንግዳ የሆነዉን የዴሞክራሲ ባህል ናሙና በጓዳዉ ሲጠነስስ ጀምሮ የፓርቲያችን መፈረካከስ የሚሹ፣ ፓርቲያችንን የሚደግፉና የፓርቲያችን አባላት ሳይቀሩ ተመሳሳይ ድምፀት ያለዉ ሀሳብ ሲያስተላልፍ ሰምተናል፤ ኢዜማ ይፈረካከሳል የሚል። ይህ ታላቅ ጉባዔ በአካሄደዉ ጥብብ የተሞላ ዉይይት ኢዜማ ከመሰነጣጠቅ ይልቅ ተጠናክሮና ፈርጥሞ እንዲወጣ ለማድረግ በመቻሉ በድጋሚ እንኳን ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡

ዴሞክራሲን አምጣ ለመዉለድ ባልቻለችዉ ሀገራችን ማህፀን የተፈጠረዉ ኢዜማ በራሱ ጓዳ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ እዉነተኛዉንና መሠረታዊዉን የዴሞክራሲ ችግኝ በመትከል ታሪክ ሰርቷል፡፡ ይህ በኢዜማ ጓዳ ዉስጥ የተፈለዉ የዴሞራሲ ችግኝ ነገ አባጣ ጎርብጣዉን የሀገራችንን የፖለቲካ መልክዐ-ምድር በመሸፈን፣ ሀገራችንን ለዘመናት እያቆረቆዛት የመጣዉን ዘመን ጠገብ የፖለቲካ ስብራት ለመፈወስ የመሠረት ድንጋይ እንዳስቀምጥን አማናለሁ፡፡

የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዚህ ጉባዔ አባለት አንድ ከዚህ ወጣ ወደ አለ ጉዳይ ልዉስዳችሁ፡፡ ይህን ሰሞን የምርጫ ቅስቀሳ አድርጌ፤ ስመለስ ልጆቼ አንድ ቀልድ ይቀልዱብኝ ነበር፤ ልክ እዚህ መድረክ ላይ የተገኙ በማስመሰል የምርጫዉን ዉጤት በድራማ መልክ ያሳዩኝ ነበር እንዲህ እያሉ «እባካችሁ ከሦስት ተወዳዳሪዎች አራተኛ ለወጣዉ ለአንዱዓለም አራጌ ሞቅ ያለ ጭብጨባ አድርጉለት» በማለት ሲቀልዱብኝ ነዉ የሰነበቱት ዛሬ ሟርታቸዉ ሰምሮ በምርጫዉ በመሸነፌ ጥሩ አለንጋ ገዝቼ ወደ ቤት በመግባት ብስጭቴን እንደምወጣባቸዉ ቤቱ እንዲያዉቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ዛሬ እነርሱን አያድርገኝ!

ወደ ፍሬ ሀሳባችን ልመልሳችሁ፡፡ ኢዜማ ሲጠነስስ ሀሳብ ነበር፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ ድርጅታዊ ዉቅሩን አስቀምጠናል፡፡ ከዚህ አንደኛ መደበኛ ጉባዔያችን ቀጥሎ ደግሞ መሬት የቆነጣጣና፣ ሰንጥቆ መዉጣት የሚችል ድርጅት እንዲሆን ሥጋ የማልበስ ስራችንን እንቀጥላለን፡፡ግዙፉን መዋቅራችንን አስፈላጊ የሆኑ አካላዊና ርዕዮታዊ ትጥቆችን በጥንቃቄ ካስታጠቅነዉ ከፊታችን በሚመጡ አመታት ለኢትዮጵያችን ፖለቲካዊ ተዓምራቶችን መስራት የሚችል ድርጅት ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ አብዛኛዎቻችን በመርከብ ተጉዘን የምናዉቅ አይመስለንም ይሆናል፡፡ ነገር ግን መለስተኛ ከተማን የሚያክል መርከብ፣ በባህር ላይ ሲንሳፈፍ ብዙዎቻችን በቴሌቪዥን መስኮት አይተን ይሆናል አንቀርም፡፡ ብዙዎቻችን ይህንን ግዙፍ አካል አንድ ካፒቴን ሺህ ማይሎችን እንዴት ሊያንሳፍፈዉ እንደቻለ እያሰብን እንደመም ይሆናል፡፡ ነገር ግን መርከቡ ሁለንተናዊ ጤንነቱ ተጠብቆ እንዲንሳፈፍ የሚያስችሉትን አያሌ ቴክኒሻኖች እንዘነጋለን፡፡ በአንድ ቴክኒሻን ስህተት አንድ ኤሌክራቲካል ወይንም ሜካኒካል ክፍሉ ቢበላሽ ካፒቴኑ ምንም መፈየድ እንደማይችል የምናስተዉል ስንቶቻችን እንሆን?

ኢዜማን የሚያክል ግዙፍ ድርጅትም ያስመዘገባቸዉን በጎ ዉጤቶች ሁሉ ያስመዘገበዉ ሁለንተናቸሁን ለትግሉ ሰጥታችሁ በየአከባቢያችን ኢዜማን ባቆማችሁ ያልተዘመራለቸሁ ጀግኖች ትልቀ ተጋድሎ ጭምር እንጅ በጥቂት አመራሮች ብቻ አልመሆኑን በአንክሮ እገነዘባለሁ፡፡ እናንተን ከመሰሉ ጀግኖች ፊት ስቆም ከአክብሮት በለላይ ከልቤም ዝቅ የምለዉ ለተጋድሎአችሁ ካለኝ ክብር የተነሳ ነዉ፡፡ የምርጫዉንም ዉጤት የምቀበለዉ ለእናንተ ከለኝ ትልቅ አክብሮትና ከፍ ያለ ትህትና ጋር ነዉ፡፡ ከአንድ ደሃ የገበሬ ቤተሰብ ብገኝም ሁልጊዜም የነፃነትና እኩልነት ጉዳይ ሕይወቴ የሚሾርበትምህዋር ነዉ፡፡ ዴሞክራሲ ስንል አሸንፎ መደሰት ብቻ ሳይሆን ሽንፈትን በፀጋ መቀበልንም ያካትታል፡፡ በሂደቱ ግን ከምንም በላይ ድርጅታችን አሸናፊ አድርገናል፡፡ በቅስቀሳ ወቅት ቃል እንደገባሁላችሁ ቃሌን እጠብቃለሁ፡፡ በማያሻማ ቋንቋ ፕ/ር ብርሃኑ ለሚቀጥሉት ሦስት አመታት እንዲመሯችሁ መርጣችኃቸዋል፡፡ ምርጫችሁን ተቀብያለሁ፡፡ ፕ/ር ብርሃኑ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ የመርጣችኃቸዉ የእናንተ ብቻ ሳይሆኑ የተፎኮካርኳቸዉ እኔና እኔን የመረጡ የጉባዔ አባላትም መሪ መሆናቸዉን ለመግለፅ እወዳለሀ! በዚህ አጋጣሚ ፕ/ር ብርሃኑን እንኳን ደስ ያለዎት እያልኩ፣ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸዉ ከልብ እመኛለሁ!!
የምርጫ ዘመቻ ብድኔን፣ በገንዘብና በምክር የረዳችሁኝ ዜጎች ሁሉ ከልብ እያመሰገንኩ ለሽንፈታችን ተጠያቂዉ እኔና እኔ ብቻ እንደሆኑኩ ለመግለፅ እወዳለሁ!

ዘመኑ የፈተና ነዉ፤ ዘመኑ የትግል ነዉ፡፡ በድል የሚወጣዉ ደግሞ በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመና አንድነቱን በብርቱ የሚያስጠብቅ ድርጅት ነዉ፡፡ ሁላችንም ከዚህ ሰዓት ጀምሮ እጅለእጅ በመያያዝ ትግላችንን እንድንቀጥል አደራ እላለሁ!

ፍትህ እንደ ቀጥር ፀሐይ፣ ፍቅር እንደ ኃይለኛ ጅረት፣ ወንድማማችነት እንደ አበባ ጉንጉን በኢትዮጵያ ላይ ለዘላለም ይንገስ!!

አንዱዓለም አራጌ

Leave a Reply