Site icon ETHIO12.COM

ቤት ሸጦ መኪና በመግዛት ራይድ የሚሰራ ሰው ለራሱ ስራ እንደፈጠረ ቢሰማው! ምክንያታዊ ነው?

አንድ ልጅ እያደረሰኝ ሲያወራኝ “ተመርቄ ቤተሰቦቼ ላይ ከምቀመጥ ብዬ! ቤተሰቦቼ የገዙልኝን እድሳት የሚቀረው ሁለት መኝታ ኮንደሚኒየም ቤት (የዛሬ ዓመት ከምናምን የገዙት 600ሺ ነበር ብሏል) ሸጨው መኪና በመግዛት ለራሴ የስራ እድል ፈጥሬ እየሰራሁ ነው!” አለኝ፡፡

በኢኮኖሚክስ አስተምሮት ውስጥ የቢሆን ስሌት (Assumption) ታዋቂ ነው! ስለዚህ ቢሆን ወይም let assume እያልኩ ነው የማቀርብላችሁ ስለዚህ አመክንዮው ላይ እንወያይበት (ሊሆንም ላይሆንም መቻል አለ ማለቴ ነው!)። ሃሳቡ የትችት ሳይሆን የውይይት መነሻ ብቻ ነው!

ቤቱን ስንት ሸጥከው? ስለው “2 ሚሊየን ብር!” መኪና ስንት ገዛህ ስለው “1.6 ሚሊየን ብር! የቀረውን ብር አንዳንድ ነገሮች ገዝቼበት የተረፈውን በባንክ አስቀመጥኩ” አለኝ፡፡

በመኪናው በቀን ስንት ትሰራለህ ብዬ ጠየኩት? “ወጪዬን ችዬ 1,500 ብር አለኝ!” እና ከቤት እራስህን ችለህ ወጣህ? ስለው “ቤተሰብ ላይ ነው አሁንም ያለሁት” አለኝ!

ስራ እንዴት ነው? አልኩት! “ከጠዋት እስከ ማታ ዘራፊ እንዳያጋጥም እየተመኘን እየታገልን ነው” አለኝ! እስከ አሁን በአካውንትህ ስንት አስቀመጥክ? ስለው “ማጠፋፋት አይቀርም….ብር” አለኝ።

Let assume!

አሁን የሰርቪስ እና ሌሎች ወጪዎች እንደሌሉ ብናስብ (ቤተሰቦቹ እየመገቡት! ከቤት ባያባርሩት ብንል!) ይህ ሰው በወር 45ሺ ብር ቢያስቀምጥ በዓመት 540ሺ ብር ይኖረዋል! በቀላል ስሌት የመኪናው ዋጋ በሶስት ዓመት ውስጥ ምንም ባይጨምር (1.6 ሚሊየን ብር እንደሆነ ቢቆይ) የመኪናውን ወጪ ለመሸፈን ሶስት ዓመት ያስፈልጋል፡፡

ምሳሌ 1፡- በቀን 1,500 ብር አስገብቶ በሶስት ዓመት ውስጥ በመኪናው የሰራውን 1.6 ሚሊየን ብር ይዞ ሲጠቀምባት የነበረችውን መኪናውን ከሶስት ዓመት በኋላ 1.5 ሚሊየን ብር ቢሸጣት ብንል ይህ ሰው ያካበተው ሃብት 3.1 ሚሊየን ብር ይሆናል! ዘንድሮ 2 ሚሊየን የሸጠውን ቤት ከሶስት ዓመት በኋላ 3.1 ሚሊየን ብር መልሶ ሊገዛው ይችላል?

ቤቱ ከሶስት ዓመት በኋላ 10 ሚሊየን ብር ሊደርስ ይችላል (አዲስ አበባ ውስጥ የቤት/ቦታ ዋጋ እራሱን እጥፍ ለማድረግ ዓመት እየፈጀበት አይደለም!) ቤቱን እንደዘጋ ለሶስት ዓመት ቢያስቀምጠው 10 ሚሊየን ብር ያገኝ ነበር (10 ሚሊየን ብር #አንፃራዊ መኪናም ቤትም ሊገዛለት ይችላል!)፡፡

ምሳሌ 2፡- የተወሰነ ተበድሮም ይሁን ቤተሰብ አስቸግሮ ቤቱን አድሶ በወር 10ሺ ብር አከራይቶ ቢሆን በዓመት 120ሺ ብር አለው (የቤት ኪራይ ዋጋ በዓመት በ30 ከመቶ እያደገ ቢሄድ እና የቤቱ ዋጋ በዓመት 100-150% ቢያድግ) በሶስት ዓመት በኋላ ቤት ኪራዩ በወር 20ሺ (በዓመት 240ሺ ብር) የቤቱ የሽያጭ ዋጋ 10 ሚሊየን ብር ሊደርስ ይችላል፡፡

ስራ መፍጠር ማለት የሚውሉበት ምክንያት ማዘጋጀት ማለት አይደለም! እቤት ያለምንም አይነት ስራ መቀመጥ ከብዙ ጉዳዮች አንጻር መጥፎ እንደሆነ እረዳለሁ! ነገር ግን ትርፍ እና ኪሳራ ከመጪው ጊዜ ሁኔታ ጋር መሰላት አለበት! ሶስት ዓመት መኪና ገዝቶ እየሰሩ እንደሆነ ከሚሰማቸው ሶስት ዓመት የወደዱትን ተጨማሪ ትምህርት እየተማሩ ዛሬ ላይ 2 ሚሊየን ብር የሚሸጥ ቤታቸው 10 ሚሊየን ብር እስኪደርስ የዋጋውን መጨመር መጠበቅ አይሻልም?

አንዳንድ ወላጆች ስራ እንዳይፈታ ለልጄ መሬቴን/ቤቴን ሸጬ መኪና/ባጃጅ ገዝቼለት! ሱቅ ከፍቼለት፤ ወዘተ ይሉ እና ግን ልጆዎት ምን ለወጠ ሲባል መልስ ይጠፋል (መሬቴን ሸጬ አስመርቄው ወይም ሰርግ ደግሼለት የሚሉም አሉ!)፡፡

ስለዚህ አሁን ላይ ወላጆችም ሆኑ ወጣቶች በገቢ፤ በወጪ እና በአዋዋላቸው ላይ በሚያደርጉት ውሳኔ ከሁለቴ በላይ በማሰብ የቀደሙ፤ የአሁን እና የመጪው ጊዜ ሁኔታዎችን ከግምት የከተተ ውሳኔ ለመወሰን ቢሞክሩ መጥፎ አይደለም!

Via Wobshet Belay yimer

Exit mobile version