Site icon ETHIO12.COM

በኦሮሚያል “የማንወሻሸው ነገር …” ብ.ጄ ሃይሉ ጎንፋ

 “በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለውን ጠላት ፈልገን ካከሰምን በጫካ ያለው ሸኔ ከመስመር ይወጣል” -ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ ጎንፋ የፓርላማ አባልና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የደህንነት አማካሪ

ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ ጎንፋ ተወልደው ያደጉት ምዕራብ ሸዋ እጪኒ በተባለው አካባቢ ነው። ትምህርታቸውን በጉደርና በአምቦ የተማሩ ሲሆን፣ መከላከያ ገብተው አገራቸውን በተለያየ መስክ አገልግለዋል። መከላከያ ከገቡ በኋላ የተለያየ ስልጠና ወስደዋል። ከአገር ውጪም በራሽያ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ፣ ሰላም ማስከበር ላይ የተሳተፉ ናቸው፤ አገራቸውንም 21 ዓመት ያህል አገልግለዋል። እያዩ የነበረው ሁኔታ አጥጋቢና ስኬታማ ባለመሆኑ ወደትግል መሄድን አማራጭ አድርገዋል። ትግሉንም የተቀላቀሉት ከባድሜ ጦርነት በኋላ በ1998 ዓ.ም ነው። ከለውጡ በኋላ ግን ተመልሰው ወደአገራቸው በመግባት ሰላማዊ ትግሉን መቀላቀል ችለዋል። በአሁኑ ሰዓት መንግስትን እያገለገሉ ሲሆን፣ የፓርላማ አባልና የኦሮሚያ ክልል የፕሬዚዳንቱ የደህንነት አማካሪ ናቸው። በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በኦሮሚያ ቋንቋ የሚታተመው የበሪሳ ጋዜጣ ከብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ ጋር በአገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።

አዲስ ዘመን፡- በትግል ላይ ቆይተው ለውጡን ተከትለው ወደ አገር ቤት ከገቡ ቆይተዋል፤ በወቅቱ ማንን ነበር ሲታገሉ የነበሩት? የት ነበር ስትታገሉስ የነበረው?

ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ፡- በአገሪቱ ያለው የፌዴራሊዝም ስርዓት ነው ይባል እንጂ ስርዓቱ ሲያገለግል የነበረው ከብዙኃኑ ይልቅ ጥቂቶችን ብቻ ነበር። ይህ አግባብ አይደለም በሚል ትግል ውስጥ ቆይተናል። ምክንያቱም የኦሮሞ ሕዝብ በነበረው ስርዓት ከሚባለው በላይ ሲገፋ እና ሲጨቆን እንዲሁም ሲታሰር ቆይቷል። ከአገር እንዲሰደድም ተደርጓል። ከዚህም የተነሳ ነው ወደጫካ በመግባት ትግል ማካሄድ የጀመርነው። በዚህም የኦሮሞ ነጻ አውጪ ድርጅትን ተቀላቀልን። ለውጡ የመጣው በዚህ መሃል ነው። በመሆኑም ከለውጡ በኋላ ጠብመንጃ የሚያስነሳ ጉዳይ ስላልነበረ ወደ አገር የገባነው ትግላችንን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ በመስማማት ነው። በለውጡ የመጣ ትልቅ ነገር አለ፤ ይሁንና ሁሉም ተሳክቷል ባይባልም የቀረ ነገር መኖሩ የማይካድ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ ጠብመንጃ ማንሳት የሚያስችል ትግል አለ ብለው ያስባሉ?

ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ፡- ሲጠየቅ የነበረው የኦሮሞ ጥያቄ ሶስት ነበር። የመጀመሪያው የማንነት ጥያቄ ነበር። ማንነት ሲባል ኦሮሙማ ማለት ነው። ሁለተኛ ጥያቄ ደግሞ የአገር ባለቤትነት ነበር። እንዲህ ሲባል ትርጉሙ ብዙ ነው፤ ለምሳሌ በውስጡ የነጻነት ጥያቄ አለው። በአገሩ ባለቤት የመሆን ጥያቄንም የሚያካትት ነበር። ሶስተኛው ደግሞ እንደኦሮሞ የፌዴራል ስርዓት ውስጥ በሚያደርገው አስተዋጽኦ ምላሹም እንደእዛው መሆን አለበት የሚል በመሆኑ ትግሉ ረጅም ጊዜ ሊወስድ ችሏል።

ትግል ሲባል መሳሪያ ስላለን ወይም መሳሪያ ስላነሳን የሚደረግ ጉዳይ አይደለም። እታገልለታለሁ ለሚለው ሕዝብ በትክክል የዚያን ሕዝብ ጥያቄ አግባብነት ባለው አካሄድን ተከትዬ እየጠየቅሁ መሆኔን ማወቅ አለብኝ። ጠብመንጃ ማለት ግን በሰላማዊ መንገድ መታገል ያቃተኝን ነገር በጉልበት የማስኬደው ነገር ነው። አሁን ያለንበት ነገር ግን ጠብመንጃ የሚያስነሳ ነገር የለውም። ያለጠብመንጃ በርካታ ነገሮችን ማሳካት ይቻላል።

ባለፉት 27 ዓመታት ስንታገል የቆየነው ነገር እውነተኛ የሆነ ነገር ስለነበር ነው። በወቅቱ ከሚደርሰው ጭቆና ራስን ለማላቀቅ በመወሰኑ ነው። ለምሳሌ ኦሮሞን ሊጠቅም የሚችለውን ነገር ታግለን ድል አግኝተናል። ያገኘውን ድል ደግሞ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማጣጣም መቻል ነው። ከዚህ በኋላ በሰላማዊ መንገድ መደረግ ያለበት ነገር ጠላትን ከኦሮሞ ላይ ማሳነስና ወገን የሆነውን ማብዛት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በዚህ አገር ላይ ገዝፈን ለመታየት ራስን ማዘጋጀት ነው። እኛ ሰፊ ብሔር ነን። የትልቅ ብሔር ጥያቄ ማንሳት እንጂ እንደ ትንሽ መሆን የለብንም። እኛ ከዚህ በኋላ ማልቀስ የለብንም፤ ሌላውንም ሰው ማስለቀስ አይኖርብንም።

አሁን ሸኔ የሚያደርገው በኦሮሞ ላይ እንደመሳለቅ የሚቆጠር ነው። የኦሮሞ ሕዝብ የከፈለውን መስዋዕትነት አለማወቅ ነው። በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ባዕድ መሆን ነው። የሌላውን አካል ፍላጎት ማስፈጸም እንጂ የኦሮሞን ሕዝብ ፍላጎት መጠበቅ ማለት አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- እናንተ ወደትግል የገባችሁት በወቅቱ የነበረው የጊዜው ሁኔታ አስገድዷችሁ እንደነበር ጠቅሰዋል፤ አሁን ሸኔ በኦሮሞ ላይ ጠብመንጃ ማንሳቱን እንዴት ያዩታል?

ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ፡- ኦሮሞ ሁሉን ያውቃልና ለእርሱ እንዲህ ነው ብዬ የምናገረው ነገር የለኝም። የኦሮሞ ሕዝብ በብዙ መንገድ ተምሯል ብዬ አምናለሁ። በመከራ ውስጥ ያለፈ በመሆኑ ከዛ የወሰደው ተሞክሮ አለ ብዬም አስባለሁ። ከነበረው ተጽዕኖ የተነሳ ልጁን በብዙ መንገድ ገብሯል። ይህን የሚያውቁ ሁሉ በትግሉ ጊዜ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ከጀነራሎች ጀምሮ ሼሆች፣ ቄሶችን ጨምሮ ታዋቂ ሰዎችም ሳይቀሩ በትግሉ አስፈላጊነት ላይ ልዩነት አልነበራቸውም። ትግሉም ያስፈልገናል በሚል አግዘውና መርቀው የሚጠበቅባቸውን አድርገዋል። ለውጥ መምጣት የቻለውም በእነርሱ የድካም ውጤት ጭምር ነው።

አሁን ግን ትግሉ ሰላማዊ በመሆኑ ‹ወደ ጫካ ሒዱና እርስ በእርሳችሁ ተገዳደሉ› ብሎ የሚመርቅ አባገዳ የለም። ሼሁም ቢሆን ‹‹ወደወንዝ ወርዳችሁ እርስ በእርስ ተገዳደሉ› አይሉም። ‹ጫካ ወርዳችሁ ተገዳደሉ› የሚሉ የኦሮሞ ሊቆችም በጭራሽ የሉም።

ጫካ ወርዳችሁ ተጣሉ የሚለው በርቀት ያለ የአገር ጠል ነው። ከዚህ ድርጊታቸው በእነርሱ ተንጠላጥሎ የፖለቲካ ትርፍ የሚያገኘው ኃይል ነው ያንን የሚያዛቸው። ኦሮሞ ኦሮሞን መግደሉ የሚደንቅ ነው፤ እንዲህ አይነቱ ድርጊት ከዚህ ቀደም በመካከላችን የሌለ ነው። እርግጥ ሁላችንም አንድ አይነት አመለካከት እና አስተሳሰብ የግድ ይኖረናል ማለት አይደለም። በመሰረታዊ ነገር ላይ ግን አንድ ልንሆን ይገባል። በዚያን ወቅት ጫካ አስገብቶ ሲያታግለን የኖረው የአገር ባለቤትነት፣ ነጻነትና የማንነት ጥያቄ ስለነበረን ነው።

በአሁኑ ወቅት ግን ጫካ ያለው አካል (ሸኔ) ትልቅ ስህተት እየፈጸመ ነው። ኦሮሞን ለ150 ዓመት ያህል ወደኋላ የጎተተውን ጉዳይ በተለያየ የእውቀት ዘርፍ በመሰማራት ወደፊት ማምጣት ተገቢ ነው እንጂ በዚህ ዘመን ጠብመንጃ አያስፈልገንም፤ ጠብመንጃ የሚመልሰን ወደኋላ ነው። በምንም አይነት ሁኔታ እንዲህ አይነት ኦሮሞን ራሱን መልሶ የሚያጠፋ ትግል አይተን አናውቅም።

እህል የሚያቃጥል ትግል፣ የጤና ተቋማትን የሚያጋይ ትግል፣ አምቡላንስን የሚያቃጥል ትግል፣ መንገድን የሚከለክል ትግል አይተን አናውቅም። እንዲህ አይነቱ ድርጊት የነጻነት ትግል ሳይሆን የባርነት ድርጊት ነው። ይህ ነውር ነው። የኦሮሞን ሞራልም የሚሰብር ድርጊት ነው። ይህ ከሆነማ ለዚያን ያህል ዓመታት ስንታገል የቆየነው ለምንድን ነው ያሰኘኛል። የኦሮሞን ንብረት የምናቃጥል፣ የምናወድም እና ንብረቱን የምናሳጣ ከሆነ ስለምን ደከምን ያስብላል። ቋንቋችንን ደባልቆ እርስ በእርስ እንዳንስማማ የሚያደርገን የጠላት ተልዕኮ ነውና ከዚህ ድርጊትና አስተሳሰብ ልንወጣ ይገባል። በእርግጥ ብዙዎች ይህ መንገድ አግባብነት የሌለው መሆኑን ተገንዝበዋል፤ ያልተገነዘቡ አሁንም ቢሆን ከዚህ ውስጥ መውጣት አለባቸው እላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በኦሮሚያ የተለያየ አካባቢዎች ተዘዋውረው መጎብኘትዎ ይታወቃል፤ ኦሮሞን ከሰላም አንጻር ያለበትን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?

ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ፡- ኦሮሚያ በትግል ውስጥ ናት። ትግሉም የማንነትን ጉዳይ ማስጠበቅ፣ በእውቀት መላቅና ከሌሎች ጋር አብሮነትን በመፍጠር ረገድ የሚደረግ ነው። የአገር ባለቤትነትን አስተማማኝ የማድረግ ትግልና ራስን ማስተዳደር ነው። ይህን አይነት መልካም የሆነ ትግል ምልዑነት እንዲኖረው ለማድረግ የሚደረግ ሩጫ ነው። ይህን ሰላማዊ ትግል ከእጅ ለማስጣል የሚያደርጉ አካላት ግን አሉ።

ኦሮሞ ሰፊ ሕዝብ ነው። ኦሮሞ ጉልበታም ነው፤ ጉልበታም የሚያደርገው አንዱ ብዛቱ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ያለው የምጣኔ ሀብቱ ነው። ሶስተኛው ደግሞ መልካምድራዊ አቀማመጡ ነው። እነዚህ ሁሉ ስላሉት ጠላቶች በርክተውበት ቆይቷል። አሁን በዚህ ትግል ውስጥ ያለች ኦሮሚያን የጠላት ተላላኪ የሆኑ ደግሞ ትግሏን ለማስቀየስ ሲባዝኑ ይስተዋላሉ። እርስ በእርስ ለማጣላት የሚፈልገውን አካል ግን ስርዓት እንዲኖረው ማድረግ ተገቢ ነው። ይህም ስርዓት የማስያዙ ጉዳይ በቅርቡ ምላሽ ያገኛል የሚል እምነት አለኝ። በዚህ ሁሉ መሃል ግን ጫና ሊኖር ይችላል፤ ልማትንም በሰላማዊ መንገድ ለማሳለጥ ይከብድ ይሆናል። አሁንም አንዱ ሌላውን ከቦታው ማሳደዱ አልቆመም። ይሁንና ይህ ጊዚያዊ ነው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያበቃ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በምዕራብ ኦሮሚያ እንዲሁም ሰሜን ሸዋ አንዳንድ አካባቢ የሸኔ ቡድን የሚዘዋወር እንደሆነ ይነገራል፤ ከዚህ ውስጥ ለመውጣት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ፡- በኦሮሚያ ከልል ምዕራብ ሸዋ እና አንዳንድ ቦታዎች ስናስተውል የሰላም ሁኔታው አስቸጋሪ ነው፤ ኦሮሞ ሰላም አግኝቶ አርሶ እንዳይበላ እየተደረገ ነው፤ የተማረ ሰው መብቱን ለመጠየቅ ይችላል። ነገር ግን ሰው እንዳይማር እንኳን ትምህርት ቤት ያቃጥላሉ። ቡድኑ ትምህርት ከነጻነት በኋላ ነው በሚል ብሒል ውስጥም በመግባቱ ይህ አግባብነት የሌለው ነው። ትናንት የነበሩ እንደ እነ ጄኔራል ታደሰ ብሩ አይነት ጀግኖቻችን ይሉን የነበረው ተማሩ፤ ተመራመሩ እንጂ ትምህርት ቤት አቃጥሉ አልነበረም። የተማረ ሰው ከባርነት ነጻ የሚወጣበትን መንገድ ያውቃል። ስለዚህ የሰላም መታጣትን የሚያመጣው አለማወቅ ነው።

ሰላም እንዲታጣ የሚደረገው አለማወቅ እንዲኖር በማድረግ ነው፤ ይህ እንዳይሆን መደረግ ያለበት በሶስት መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ፤ የመጀመሪያው የኦሮሞን ሰላም ማጣት ለሚፈልገው ለላኪው ባለመላላክ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ተሳስቶ በዛ ውስጥ የገባን አካል በማስተማር ነው። ሶስተኛው ደግሞ ተጸጽቶ እንዲመለስ በመምከር ነው። በእነዚህ ሶስቱ የማይመለስ ከሆነ ደግሞ እርሱ በመጣበት መንገድ ወታደራዊ ስልት መጠቀም ነው። ይህ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ታግሎ ሰላም ሲያጣ ማየት ያሳዝናል። እንዲህ እያደረገ ያለው የራሱ ልጅ በመሆኑ የሚመከረውን መክሮና ዘክሮ መመለስ ሲሆን፣ አልመከር ያለውን ደግሞ አሳልፎ መስጠት ይጠበቅበታል።

አዲስ ዘመን፡- የኦሮሚያ ክልል ሰላም እንዲሆንና አካባቢውም ሁሉ ሰላም ውሎ እንዲያድር ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?

ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ፡- ሰላም በመገዳደል አይመጣም፤ ሰላም የሚመጣው እርስ በእርስ በመረዳዳትና አንድነታችንን በማጠናከር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በማስተዋል መስራት ስንጀምር ነው። ለውጥ ማምጣት የሚችለው በጠብመንጃ አይደለም። በጠብመንጃማ ቀደም ሲል ብዙ ጊዜ ሰላም ለማምጣት ተሞክሯል። ሰላም ማምጣት የሚቻለው በመነጋገርና በመመካከር ነው። በአሁኑ ሰዓት ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሰላም እንዲመጣ ሲያደርግ የነበረው የኃይል ትግል ሰላማዊ ወደሆነው ትግል እንዲመጣ ማድረግ በመቻሉ ነው።

ለኦሮሞ ሕዝብ አሁን ካለው መንግስት የተሻለ የሚመጣለት መንግስት የለም። ከዚህ ያነሰ እድል ይመጣ ይሆናል እንጂ ከዚህ በኋላ ከዚህ የበለጠ ምቹ ሁኔታ አይመጣም። በየሰርጣሰርጡ ያሉ ቡድኖች የኦሮሞን ሕዝብ ከዚህ በኋላ ወደታች ለመመለስ የሚጥሩ ካልሆነ በስተቀር ከዚህ በላይ እድል የለም ባይ ነኝ። ስለዚህ ይህን እድል በአግባቡ ለመጠቀም አንደኛ አንድነትን ማጠናከር መልካም ነው። እንዲህም ሲባል በመካከላችን መከባበር መኖር አለበት። ታላቆችን ማክበር ያስፈልጋል። አዋጩ ይህ ነው፤ የላላውን የአንድነት ገመድ ማጠናከር ተገቢ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሕዝቡ መንግስት መዋቅር ውስጥ ያለው አካል ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሒደት አራዝሟል ይላል፤ ይህን ሁኔታ ሕዝቡ ባገኘው መድረክ ላይ ሁሉ ያንጸባርቃል። እርስዎ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ፡- እውነት ነው፤ ሕዝቡ ይህን ጉዳይ ስለመናገሩ ሐሰትነት የለውም። አንድ የማንወሻሸው ነገር ቢኖር የመንግስት መዋቅር ከሌላው ጋር የተቀላቀለ ነው፤ ትናንት በጥፊ ሲመታን የነበረውም ሆነ ሲያስጨንቀን የነበረውም በአንድ ላይ ተሸክመን እየተጓዝን ነው ማለት ያስደፍራል። በመሆኑም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለው አካል በጫካ ካለው ሸኔ በላይ ስጋት ነው።

በመሆኑም በመንግስት መዋቅር ያለውን ችግር ማጥራት ተገቢ ነው። ምክንያቱም አንዴ በዚህኛው አንዴ ደግሞ በዚያኛው እያሉ በሁለት ቢላዋ እየበሉ መኖር ከዚህ በኋላ የሚቻል አይሆንም። በጫካ ካለው ጠላት ይልቅ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያለውን ጠላት ፈልገን ካከሰምን በጫካ ያለውም ከመስመር ይወጣል።

ስለሆነም ሕዝብ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰገ አካል አለ እያለ ያለው ነገር ትክክል ነው። ምክንያቱም የተለያየ አገልግሎት ፈልጎ ወደመንግስት ተቋማት ሲሄድ ጥቅማጥቅም የሚጠየቅ ከሆነ፣ አገልግሎት ማግኘት ፈልጎ በአግባቡ ሳይስተናገድ እና አገልግሎቱን ሳያገኝ ከቀረ መንግስት ሕዝብን የሚያገለግልና የሕዝብ መንግስት ነው ማለት ይከብዳል። ይህን ጉዳይ ከሕዝብ ጋር በመሆን ታግሎ ማስተካከል ያስፈልጋል። በመንግስት መዋቅር ውስጥ የዴሞክራሲ ችግር መኖሩ መቶ በመቶ የሚታመን ነው። እንደ አንድ በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ እንደሚሰራ እንዲሁም ትናንት ደግሞ ሲታገል እንደቆየ ሰው ይህን ጉዳይ አጥርቼ መያዝ አለብኝ ብዬ አስባለሁ።

በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሌቦች እና አጭበርባሪዎች እንዲሁም ያለችሎታቸው የገቡ ብዙዎች አሉ። እነዚህ አካላት ደግሞ ጠላት የሆነውን ቡድን በማገልገል ላይ ነው ወይ ያሉት? ከተባለ አዎ ነው መልሱ። ስለዚህ ምን ማድረግ አለብን? የሚባል ከሆነ ደግሞ እነዚህን አካላት ማጥራት ተገቢ ይሆናል፤ ከማን ጋር? የሚባል ከሆነ ደግሞ ከራሱ ከሕዝብ ጋር በመሆን የሚል ነው መልስ የሚሆነው። መንግስት ደግሞ በዚህ ላይ ቁርጠኝነቱ አለው።

ይህን ጉዳይ ለማወቅ የተለየ ጥናት የሚያስፈልገው አይደለም። ስርዓት አለ፤ በጀትም አለ፤ የመንግስትን መዋቅር እያስቸገረ ያለው ነገር አንዱ ሰነፍ መሆን ነው፤ እውቀቱ እያለው ከስንፍናው የተነሳ ማከናወን አለመቻል ነው። ሁለተኛው አስቸጋሪ ጉዳይ እውቀት ማጣት ነው። ያንን ነገር መስራት ይፈልጋል፤ ነገር ግን እውቀት ደግሞ ስለሌለው ስራውን ማከናወን ይሳነዋል ማለት ነው። ይህን መንግስት ተረድቷል። ዋናው ነገር መረዳቱ ነው። ከተረዳ ማጥራት ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።

ብርጋዴር ጀነራል ኃይሉ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Exit mobile version