Site icon ETHIO12.COM

የ12 ዓመት ታዳጊ የቤት ሰራተኛቸውን ገድለው በድብቅ ሊቀብሩ ሲሉ የተያዙ ባለትዳሮች በ25 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ

በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ማንጎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የ12 ዓመት ታዳጊ የቤት ሰራተኛቸውን ገድለው በድብቅ ሊቀብሩ ሲሉ የተያዙ ባለትዳሮች በ25 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን ፍትሕ ሚኒስቴር አሰታወቀ።

በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ምርመራውን በመምራት  ክስ መስርቶ ክርክር በማድረግ አጥፊዎቹ እንዲቀጡ ማደረጉ ተገልጿል።

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፤ 1ኛ ልጃለም ጌታቸው ታዬ እና 2ኛ ቆንጂት ሙለታ በቀለ የተባሉት ባለትዳር ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ማንጎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አከባቢ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከታህሳስ 17/2014 እስከ ጥር 17/2014  ባለ ጊዜ ሟች አስቴር ነገሰ የተባለች የ12 ዓመት ታዳጊን ተከሳሾቹ በተደጋጋሚ በተለያየ ጊዜ በፍልጥ እንጨት፣ በእርግጫ፤ በሞባልይ ቻርጀር ገመድ ጀርባዋን፣ ወገቧን እና እግሯን ደጋግመው በመደብደብ፤  ከገደሏት በኋላ የሟችን አስከሬን በሳጥን በማድረግ በድብቅ ለመቅበር ሲሰናዱ ተይዘዋል።

ጉዳዩ በምርመራ ሲጣራ በሟች ላይ በርካታ የቆዳ መጋጋጥ እና የመበለዝ፣ ከአንገትዋ የፊተኛው ክፍል አንስቶ ወደ ቀኝ እና ግራ ትከሻዋ የተሰራጨ” የመበለዝ፣ በደረትዋ የላይኛው ፊተኛና ጎን 1/3 ክፍል የመበለዝ፣ በቀኝና በግራ መቀመጫዋ ጭን የላይኛው ኋለኛ ክፍል እና በጀርባዋ የታችኛው ክፍል ላይ በርካታ የቆየ የቆዳ መጋጥ፣ በራስ ቅልዋ ፊተኛ መካከለኛ ክፍል የመበለዝ፣ በእጅ እና እግሮቿ ላይ ወደ ውስጥ ደም የመፍሰስ፣ የመሰራጨትና የመበለዝ ጉዳት ምክንያት ህይወቷ ማለፉ በማስረጃ በመረጋገጡ  ዐቃቤ ሕግ በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዉ ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ተከሳሾችም “ድርጊቱን አልፈፀምንም ጥፋተኛም አይደለንም”  ብለው የተከራከሩ ሲሆን፣  ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ አስደግፎ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በበቂ ሁኔታ ያረጋገጠ በመሆኑ እና ተከሳሾችም ይህን የዐቃቤ ሕግ ክስ እና የቀረበባቸውን ማስረጃ እንዲያሰተባብሉ በተሰጠ ብይን መሰረት 2 የመከላከያ ምስክር አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም የቀረበባቸውን ክስ እና ማስረጃ ያላስተባበሉ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ህግ በቀረበባቸው ክስ እና ማስረጃ መሰረት ጥፋተኛ ናቸዉ ብሏል።

በዚህም መሰረት ክርክሩን የመራው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም በቅጣት አወሳሰን መመሪያ 02/2006 መሰረት የወንጀል  ደረጃውን  2 እርከን 39 ስር በማድረግ መነሻ ቅጣት በመያዝ፣ ሁለቱም ተከሳሾች ሪከርድ የሌለባቸው በመሆኑና የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው 2 የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው በእርከን 37 ስር ተከሳሾችን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን እያንዳንዳቸው በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ እና እንዲሁም ተከሳሾች ለ5 ዓመት ከመብቶቻቸው እንዲሻሩ ሲል መወሰኑን አዲስ ማለዳ ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘችው መረጃ አመላክቷል፡፡

Exit mobile version