Site icon ETHIO12.COM

የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል!

ሀገራችን ያለፉትን አመታት በከፍተኛ የሰላም እጦት ችግር ውስጥ ማሳለፏ እሙን ነው።አሁንም ቢሆን በአንፃራዊነት ካልተገለፀ በቀር ሰላሟ ሙሉ ነው ለማለት እምብዛም አያስደፍርም።ይሁን እና ከትላንቱ ዛሬ ይሻላል።

የመከላኪያ ሰራዊት ሰላም ለማረጋገጥ በአነስተኛ የሰራዊት ቁጥር እና አደረጃጀት ብዙ ዋጋ ከፍሏል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ሁኖም ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም በመተለም እራሱን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርበትን አያሌ በጎ ተግባራትንም በመከወን ላይ ይገኛል።

‘ዘመናዊ የመከላኪያ ተቋም ገንብተዋል’ የምንላቸውን ሀገሮችን የግንባታ ሂደታቸውን ለተመለከተ የብዙዎቹ ከእዚህ ጋር ፈፅሞ የተለየ መሆኑን ይረዳል።

ሰራዊታቸውን ለማሰልጠን እና ለማስታጠቅ የነበሯቸውን የሰላም ጊዜዎች ተጠቅመውበታል። ‘ወታደር በሰላም ጊዜ ይደራጃል በጦርነት ጊዜ ይዋጋል!’የሚለው አባባልም ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል።ይሁን እና እኛ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ለዚህ አልታደልንም።

በዚህ ቁጭት የተብሰለሰሉ ‘ዛሬም አረፈደም! እድሉም አቅሙም አለን’ ብለው የተነሱ ለእውናዊነቱ ሌት ተቀን ያለ እረፍት በመስራት ላይ ይገኛሉ።

ከምናየው ሀቅ ተነስተን ‘ሀገራችን ከዚህ ቀደም ፈፅሞ ኖሯትም ሆነ አስባው የማታውቀው በክብሯ በልኳ የተሰፋ ግዙፍ ዘመናዊ ሰራዊት ባለቤት እየሆነች እንደሆነ በልበ ሙሉነት ለመናገር እንደፍራለን።

በሰልፉ እና በወታደራዊ ትሪቶቹ ልብ የሚያርድ! በግርማ ሞገሱ የሚያስፈራ! ጠላቶቹ ወደ ጦርነት ከመግባታቸው በፊት ደጋግመው እንዲያስቡ እንደ ልብ ወዳጅ የሚመክር!

ከዚህ አልፈው ወደ ጦርነት ለሚገቡ በአጠረ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ለእነሱም ሆነ ለሌላው የሚሆን የእድሜ ልክ ትምህርት የሚያስጨብጥ!ግዙፍ ዘመናዊ የጦር ሰራዊት ባለ ቤት እየሆነች ነው ብለን ብንል ማጋነን አይሆንብንም።

ይህ ተግባር ውትድርና የነፍሳችን ጥሪ ሆኖ ለተቀበልን! በሰራዊት ቤት ውስጥ አልፎ ሀጅ ላልሆንን ለእኛ ብዙ ትርጉሙ አለው።

የሌላ ሀገሮችን የዘመነ የመከላኪያ ተቋም እያየን በቅናት ለበገንን!ኢትዮጵያችንም እንደ እነሱ አይነት ዘመን ተሻጋሪ ተቋም እንዲኖራት በምኞት ለምንታመም ወታደሮች ደስታው ከ እስከ ተብሎ የሚገለፅ አይደለም።

የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል!

Zerihun Nuri Abote

Exit mobile version