Site icon ETHIO12.COM

“በተካድኩ” ስሜት መከላከያ አማራ ክልልን ለቆ ሊወጣ ነው?

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አላስፈላጊ መስዋዕትነት ላለመክፈል በሚል የአማራ ክልልን ለአማራ ልዩሃይል እና ለሌሎች የፀጥታ ሃይሎች አስረክቦ ለመውጣት የሚያደርገውን ዝግጅት በፅኑ እቃወማለሁ። የዶ/ር አብይ አስተዳደር ይህን ውሳኔ ካሳለፈ ታሪካዊ ስህተት እንደፈፀመ እቆጥረዋለሁ። እውነት ነው መሬት ላይ አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ትንኮሳዎች እና በሶሻል ሚዲያው የሚደረጉ ግብረ-ገብነት የጎደላቸው ቀረርቶዎችና ዛቻዎች እንዲሁም የጥላቻ ዘመቻዎች አሉ። ነገር ግን ይህ የመላው አማራ ድምፅ አለመሆኑን ለመናገር ብዙ ማተት አያስፈልገውም።
የአማራ ሕዝብ ከግፈኞችና ከስርዓት አልበኞች ጋር ፈፅሞ ሕብረት የለውም። “በፍርድ ከሄደች በቅሎዬ ይልቅ፣ ያለ ፍርደ የሄደች ጭብጦዬ ትቆጨኛለች” ብሎ ስለፍትህ የሚራቀቅ ሕዝብ ነው። ለሕግ የበላይነት መስፈን እንጅ ለስርዓት አልበኝነት መንገስ የማይተባበር በስርዓት የኖረና የሚኖር ሕዝብ ነው። የሐገሩን ሕልውና የሚጠብቅለትን መከላከያ ሰራዊትን የሚወጋ ሳይሆን ደጀን ከመሆን አልፎ ቀድሞት ለመሞት የሚሻኮት ሕዝብ ነው። ይህን ኢትዮጵያ የሕልውና ጦርነት በገጠማት ወቅት በየ ጦር ግንባሩ ያስመሰከረው ነው። የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የአማራ ሕዝብ ስርዓት አልበኝነትን በፅኑ የሚታገል ታታሪና ሰርቶ አዳሪ ኩሩና ደግ ሕዝብ ነው። ስርዓት አልበኝነትን ለማንገስ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው፣በመከላከያ ላይ ትንኮሳ እየፈፀመ ያለው እና ጥቃት ለመክፈት በመንቀሳቀስ ላይ ያለው የአማራ ሕዝብ አይደለም። ይህን ራሱ መከላከያ ሰራዊቱ ምስክርነቱን የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
በጌታቸው አሰፋ ቡድን ስር በተለያዩ የአማራ ከተሞች የሚንቀሳቀሱ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መቃብር ጠባቂዎች የግብፅ ቅጥረኞች ለአሜሪካ መሩ ምዕራባውያን ጥቅም ከፊት የተሰለፉ የ”E” ነጭ ለባሾች የ”X” እና የ”ገ” ጉዳይ አስፈፃሚ አካላት መሆናቸው እንኳን ለመንግስት ለተራ ሰውም ግልፅ ነው። ስለሆነም መከላከያ

ሁሌም በየትኛውም ጊዜ ከጎኑ ለሚቆመው ለደጀኑ ለአማራ ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ሲል በጥፋት ሃይሎች በኩል የሚከፈል አላስፈላጊ መስዋዕትነት ሊኖር ቢችልም ሕዝቡን ያስቀድም። በወጣና በገባበት ሁሉ እየተከለ ምርኩዙ ለሚሆነው ሕዝብ ደህንነትና ሰላም ዘብ ይቁም። ቢርበው የሚያበላው ቢጠማው የሚያጠጣው ደግ ርህሩህ ሕዝብ ነው የአማራ ሕዝብ። ፈፅሞ የመከላከያን ክፋት ማየት የሚፈልግ ሕዝብ አይደለም። በመከላከያ ላይ እጁን ሊያነሳ ቀርቶ የሚያነሱትን የሚታገል ሕዝብ ነው። ይህ ደግና ጀግና ሕዝብ ለአማራ ልዩሃይል እና ለሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ብቻ ሰላሙንና ፀጥታውን ያስከብሩለት ብሎ ጥሎት ለመውጣት ማሰብ ለእኔ እንደ ክህደት የምቆጥረው ጉዳይ ነው።ለአማራ ክልል ሕዝብ ሰላምና ደህንነት አለመቆርቆር ነው።
በተለያዬ መንገድ “በአማራ ልዩሃይል እንመካለን መከላከያ አያስፈልገንም እንዲያውም እንወጋዋለን እንዋጋለን” የሚለው ድምፅ የመላው የአማራ ሕዝብ ድምፅ አይደለም።የእነዚህ ሃይሎች ዋና አላማ ታውቆ ያደረ ነው። በመሆኑም መከላከያ ከአማራ ክልል ለቆ ለመውጣት የሚያደርገውን መሰናዳት መልሶ እንዲያጤነው እንጠይቃለን። የአማራ ክልል ሕዝብ ከመከላከያ ጎን በመቆመበት ሁኔታ የአማራ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ እንደሚያስፈልገው አይነት ይዘት ባለው መንገድ ለቆ ለመውጣት ታስቧል የተባለውን ጭምጭምታ ተቀባይነት የሌለውና ኋላፊነት የጎደለው አድርገን እንወስደዋለን።የአማራ ክልል መንግሰት ይህን ጉዳይ ተግባራዊ እንዲሆን ይተባበራል ብለን አናስብም ይህን የሚያደርግ ከሆነ ግን ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ይሰራል።
የጥፋት መልዕክተኞች በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በየትም ክልል ያለ ጉዳይ ነው።
የአማራ ሕዝብ በየትኛውም ጊዜ ከጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ነበረ ወደፊትም ይሆናል!!!

Thomas jajaw telegram

Exit mobile version