Site icon ETHIO12.COM

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ ህገ-ወጥ ግዥ በሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው

የቀድሞው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ በ15 ተከሳሾች ላይ ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ ህገ-ወጥ ግዥ በመፈፀም በሙስና ወንጀል እና በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ክስ ተመሰረተባቸው፡፡

በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ የቀድሞው የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ በ15 ተከሳሾች ላይ ከ348 ሚሊዮን ብር በላይ ህገ-ወጥ ግዥ በመፈፀም በሙስና ወንጀል እና በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ክስ መሰረተባቸው፡፡

ጉዳዩ የቀረበው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ነው።

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሾች 1ኛ ዶ/ር ጫላ ዋታ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የነበረ፣ 2ኛ ዶ/ር ታምሩ ጣሞሌ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት የነበረ፣ 3ኛ ዶ/ር ሮባ ደምቢ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና የተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት የነበሩ፣ 4ኛ ኢ/ር አብርሃም ባያብል የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ እና ተቋማዊ ልማት ም/ፕሬዝዳንት የነበረ፣ 5ኛ አቶ ሊበን ደሊሎ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የግዢ ዳይሬክተር፣ 6ኛ አቶ ቦሩ ህርጳዬ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስ ዳይሬክተር የነበረ፣ 7ኛ አቶ ለታ ድሪባ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የቢ.ኤች.ዩ አማካሪ ድርጅት ተወካይ፣ 8ኛ አቶ አብራሃም ቡሶዋ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ፕሮጄክት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ 9ኛ አቶ ተስፋሁን ሌጃቦ ተስፋሁን ሌጃቦ ጠቅላላ የግል ስራ ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ፣ 10ኛ አቶ አያሌው ካሳ ቦኩ ኢቲያንሳ ጠቅላላ የግል ስራ ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ፣ 11ኛ አቶ ጉተማ ቡሌ ጉተማ ቡሌ አዱላ ጠቅላላ የግ/ስ/ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ፣ 12ኛ አቶ አንጂሎ አርሾ አንጂሎ አርሾ ጠቅላላ የግል ስራ ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ፣ 13ኛ አቶ ለሚ ኤጄታ ቢዳሩ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ፣ 14ኛ አቶ አይመን አቡዱላሂ አረብ ኮንስትራክሽን ስራ አስኪያጅ፣ 15ኛ ወ/ሮ ፀሃይ ሀይሉ የመንግስት ስራ የሚሰሩ ሲሆኑ፤ በድምሩ በ15 ተከሳሾች ላይ የእያንዳንዳቸው የተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ በዐቃቤ ሕግ አራት ተደራራቢ ክሶች ተመስርቶባቸዋል፡፡

በ1ኛ ክስ ላይ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ባሉት ተከሳሾች ላይ ሲሆን ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉ ተከሳሾች ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር እና የማናጅመንት አባል በመሆን የተሰጣቸዉን ከፍተኛ የስራ ሃላፊነት በመጠቀም በሚሰሩበት ወቅት 7ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች እንደቀደም ተከተላቸው የBHU Consulting Engineers General Level ድርጅት ቢሮ አስተባባሪ እና የቦርድ አባል ሆነው ሲሰሩ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት እና በመንግስት ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ፤ የመንግስት የግዥ አዋጅ እና አፈጻጸም መመሪያን በመጣስ በ1ኛ ተከሳሽ ስም ለተመዘገበውና ህገ-ወጥ ከሆነው ቢ.ኤች.ዩ አማካሪ ድርጅት ጋር 13 ሚሊዮን 478 ሺ 150 ብር በቀጥታ ግዥ የውል ስምምነት እንዲፈፀም እና ክፍያዎችም እንዲፈፀሙ በማኔጅመንት አለአግባብ ውሳኔ በማስተላለፍ፤
ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉ ተከሳሾች በዩኒቨርሲቲው ቦርድ ያልጸደቀ የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 39/2012 የሚል በማውጣት እና በዚሁም ደንብ ድርጅቱ በማማከር የሚያገኘዉን ትርፍ ክፍፍልን በራሳቸው በመወሰን ከዩኒቨርሲቲው ሂሳብ ቁጥር በተለያዩ ቀናት በድምሩ 23 ሚሊዮን 135 ሺ 433.27 ብር ተቀንሶ በህገ-ወጥ መንገድ ባቋቋሙትና በቀጥታ ግዢ የግንባታ የማማከር ስራዎችን ውል እንዲዋዋል ባደረጉት ቢ.ኤች.ዩ አማካሪ ኢንጂነርስ ድርጅት ስም በከፈቱት ሂሳብ ቁጥር እንዲተላለፍ ካደረጉ በኋላ በ1ኛ እና 6ኛ ተከሳሽ ፊርማ፤ ለ1ኛ ተከሳሽ 2 ሚሊዮን 116 ሺ 16.65 ብር፣ ለ2ኛ ተከሳሽ 542 ሺ 705.82 ብር፣ ለ3ኛ ተከሳሽ 523 ሺ 47.60 ብር፣ ለ4ኛ ተከሳሽ 2 ሚሊዮን 82 ሺ 747.14 ብር፣ ለ5ኛ ተከሳሽ 99 ሺ 284.67 ብር ለ6ኛ ተከሳሽ 421 ሺ 78.67 ብር፣ ለ7ኛ ተከሳሽ 1 ሚሊዮን 467 ሺ 185.84 ብር፣ ለ8ኛ ተከሳሽ 324 ሺ 20.72 ብር፣ በተለያዩ ቀናት በስማቸው በተከፈተ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር አለአግባብ ገቢ የሆነላቸው እና አለአግባብ እንዲከፋፈል ያደረጉ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተከፋይ በመሆን በፈፀሙት ስልጣንን አለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

2ኛ ክስ ከ1ኛ እስከ 6ኛ፣ 8ኛ፣ 9ኛ፣ 10ኛ እና 11ኛ ባሉት ተከሳሽ ላይ ሲሆን ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉ ተከሳሾች የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ አመራርና ማኔጅመንት አባል በመሆን የመንግስት የግዥ አዋጅ እና አፈጻጸም መመሪያን በመተላለፍ በቀን ሰኔ 10/2012 ዓ.ም በያዙት ቃለ-ጉባኤ በቀጥታ ግዥ እንዲፈጸም ውሳኔ በማስተላለፍ በግዥ ህግ አግባብ ግልፅ ጨረታ ወጥቶ በውድድር መሰጠት ያለበትን ስራ ያለምንም ጨረታ በቀጥታ ግዥ በድምሩ 195 ሚሊዮን 52 ሺ 812.81 ብር ግዥ ያለአግባብ እንዲሰጥ በማድረግ በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆኑ፤ 8ኛ ተከሳሽ የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ፕሮጄክት ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ከስራ ተቋራጮቹ ጋር በጋራ ከሚያስተዳድረው ገንዘብ አለአግባብ ለ1ኛ ተከሳሽ ጥቅም ወጪ እንዲሆን በቼኮቹ ላይ የፈረመ እና 1ኛ ተከሳሽ ከስራ ተቋራጮቹ ባለቤት እና ተወካይ ከሆኑት 9ኛ፣ 10ኛ እና 11ኛ ተከሳሾች ጋር አለአግባብ ውል በመዋዋል እና የማይገባው ጥቅም በመውሰድ እንዲሁም ከ9ኛ እስከ 11ኛ ያሉ ተከሳሾችም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ካሉ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ያለምንም ጨረታ በቀጥታ ግዥ ውል በመዋዋል ያለአግባብ ጥቅም ያገኙ እና በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆኑ በዋናና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በስልጣን አለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

3ኛ ክስ ከ1ኛ እስከ 6ኛ፣12ኛ፣ 13ኛ እና 14ኛ ባሉት ተከሳሾች ላይ ሲሆን ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉ ተከሳሾች የመንግስት የግዥ አዋጅ እና አፈጻጸም መመሪያን በመጣስ ያለአግባብ 14 ተሸከርካሪዎችን እና ማሽነሪዎችን በቀጥታ ግዥ እንዲፈፀም በመወሰን መንግስት የሚያገኘውን ጥቅም በማሳጣትና ጉዳት በማድረስ እንዲሁም የግዥው ህገ-ወጥነት እንዳይታወቅ ዩኒቨርሲቲው ለመሰረተ ልማት ግንባታ በተፈቀደለት ካፒታል በጀት ውስጥ በማካተት በድምሩ 116 ሚሊዮን 389 ሺ 964.18 ብር ግዥ እንዲፈፀም ያደረጉ ሲሆን፤ 12ኛ፣ 13ኛ እና 14ኛ የተጠቀሱት ተከሳሾችም በህገ-ወጥ የተሸርካሪ ግዢ አለአግባብ ጥቅም ያገኙ በመሆናቸዉ በዋናና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በስልጣን አለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

4ኛ ክስ በ1ኛ እና በ15ኛ ባሉት ተከሳሾች ላይ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ የመንግስት የግዥ አዋጅ እና አፈጻጸም መመሪያን በመጣስ ያለምንም ጨረታ በክስ 1፣ 2 እና 3 ቀጥታ ግዥ እንዲከናውን በማድረግ፣ እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው እና ከድርጅቱ ሂሳብ ቁጥር ተቀናሽ ተደርጎ ወደ 1ኛ ተከሳሽ ህጋዊ ባለቤት ወደሆነችው 15ኛ ተከሳሽ 10 ሚሊዮን ብር ገቢ ያደረጉ ሲሆን 15ኛ ተከሳሽም ገቢ የተደረገላትን 10 ሚሊዮን ብር የመኖሪያ ቤት ህንፃ ግዥ ክፍያ እንዲውል መኖሪያ ቤቱን ወደ ሸጠው ግለሰብ በተለያዩ ባንኮች ያስተላለፈች በመሆኑ እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ 1 ሚሊዮን ብር ህጋዊ በማስመሰል ህጋዊ ባለቤቱ ለሆነችው 15ኛ ተከሳሽ ገቢ ያደረገ፣ እንዲሁም 500 ሺ ብር በጉዱ ጀነራል ትሬዲንግ ህጋዊ በማስመሰል ለአክሲዮን መግዣ እንዲውል ያስተላለፈ በመሆኑ፤ በአጠቃላይ 1ኛ እና 15ኛ ተከሳሾች ምንጫቸው የሙስና ወንጀል የሆነ ገንዘብ ህጋዊ በማስመሰል የተጠቀሙበት፣ ያዘዋወሩ፣ ያስተላለፉ፣ እንዲሁም በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘውን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስለው በማቅረብ በዋና እና በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙበት በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ፣ እና 7ኛ ተከሳሾች በችሎት ቀርበው ክሱ የተነበበላቸው ሲሆን በቀረቡት ተከሳሾች ላይ የክስ መቃወሚያ ለመስማት እና ፖሊስ ቀሪ 9 ተከሳሾችን እንዲያቀርብ ለግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾች ከፍርድ በፊት እንደ ንጹህ የመገመት ህገ-መንግስታዊ መብታቸው የተጠበቀ ነው።

Exit mobile version