Site icon ETHIO12.COM

በዓባይ ግድብ ሰው ሠራሽ አሳ ማምረት ተጀመረ

በዓባይ ግድብ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ላይ አሳ ማስገር መጀመሩንና በቀን በአማካኝ አሥራ ሁለት ኩንታል የዓሣ ምርት እየተገኘ መሆኑን የቤንሻንጉል ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቤንሻንጉል ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሃሊፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ክልሉ በአንፃራዊነት ከሌሎች ክልሎች የተሻለ የዓሣ ምርት የሚገኝበት ነው። የክልሉ ነዋሪዎችም የዓሣ ምርቱን ለምግብነት ብቻ ሳይሆን ለገበያ በማዋል በገቢ ምንጭነት ይጠቀሙበታል።

የቤንሻንጉል ክልል የዓባይ ግድብ መገኛ መሆኑን ያወሱት ኃላፊው፤ አሁን ላይ ከህዳሴው ግድብ ሰው ሠራሽ ሐይቅ በቀን በአማካኝ አሥራ ሁለት ኩንታል የዓሣ ምርት በአማካኝ እየተገኘ ነው። ይህንንም በማጠናከር የዓሣ ምርቱን ለምግብነት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ በማዋል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለሀገር ማስገኘት ይቻላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ትላልቅ ወንዞች፣ ሐይቆችና ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫና ለመስኖ የተገነቡ ግዙፍ ግድቦች ባለቤት ናት። ይህንንም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት አቶ ባበክር፤ የክልሉ የዓሣ ሀብት ባለሀብቶች መጥተው በመመልከት በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የቤንሻንጉል ክልል ግብርና ቢሮ የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሀይሉ ይርጋ በበኩላቸው፤ በጥቂት የሞተር ጀልባዎች ከዓባይ ግድብ ሰው ሠራሽ ሐይቅ በቀን እስከ አሥራ ሁለት ኩንታል የዓሣ ምርት እየተገኘ ነው ብለዋል። ዓሣ ለማስገር የሚያገለግሉ ጀልባዎችን ቁጥር ማብዛት ከተቻለ እና ዘመናዊ ዓሣ የማስገር ሥራ የሚሠራ ከሆነ አሁን ላይ ከግድቡ እየተገኘ ያለውን ምርት በአስራ አምስት እጥፍ ማሳደግ እንደሚቻል ተረጋግጧል ብለዋል።

የዓባይ ግድብ ሰፊና ትልቅ ሰው ሰራሽ ሐይቅ በመሆኑ ዓሣ ለማስገር ዘመናዊ ጀልባ እና ማስገሪያ መረብ ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ በግድቡ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ላይ ሁለት ማህበራት ዓሣ የማስገር ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ። ነገር ግን ሰው ሰራሽ ሐይቁ በርካታ ጀልባዎችን ማስተናገድ የሚችል በመሆኑ በዘርፉ በዘመናዊ መንገድ ዓሣ ማስገር የሚፈልጉ የክልሉን ግብርና ቢሮ በማነጋገር ሥራ መጀመር ይችላሉ ሲሉ መናገራቸውን አዲስ ዘመን አስነብቧል።

ሳሙኤል ወንደሰን

Exit mobile version