ETHIO12.COM

በዘረኝነትና በሃይማኖት ስም እልቂት የሚያነሳሱ በሽብር ወንጀል በህግ ሊጠየቁ ነው፤ ዘመዴ “ለዘመዶቹ” የድረሱልኝ ጥሪ አቀረበ

በተለይ ከአገር ውጭ ሆነው በዘረኝነትና በሃይማኖት ሽፋን ህዝብ እንዲጫረሰ እየሰሩ ነው በተባሉ ክፍሎች ላይ በዓለም ዓቀፍ ደረጃና በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ክስ እንደሚመሰረት ተሰማ። ከአንዳንድ አገራት ጋር የመዋቅር ንግግርና የጋራ ስራ መጀመሩ ታውቋል። ከዚሁ ጋር የተያያዘ ይሁን በሌላ ሳይገልጸ ዘመዴ “ለዘመዶቹ” መከሰሱን ገልጾ ገንዘብ እንዲያዋጡለት “ድረሱልኝ” ብሏል። ክሱ በሽብር ከሆነ ገንዘብ የሚሰጡትንም የሚያካትት በመሆኑ ስጋት የገባቸው አስተያየት ሰጥተዋል።

ዜናውን ይፋ ያደረጉልን ክፍሎች እንዳሉት ክስ ለመስረት ሰፊ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። መረጃ ተደራጅቷል። “ወዳጅ” ከተባሉ አገራት ጋር የጋራ ምክክር ተካሂዷል። ከአንዳንዶቹ አገራት ጋር በተመሳሳይ ወነጀለኞችን ለመለዋወጥ ስምምነት አለ።

በቅርቡ “ሃፍ ካስት” ተብለው ተፈርጀው፣ እንዲገደሉ ሳይሞቱ ዛቻ ቀርቦባቸው የነበሩትና በዚሁ መሰረት የተገደሉት የአቶ ግርማ የሺ ጥላ ሞት በዓለም ዓቀፍ ህግ መሰረት የዘረኛነት ቅስቀሳና ለእልቂት ማነሳሻ ወንጀል መሆኑን ያመለከቱት የዜናው ባለቤቶች ” የሚመሰረተው ክስ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በአውርፓም ጭምር እንደሆነ መረጃው አለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

በይሃማኖትም ሆነ በዘረኝነት የጥላቻ ቅስቀሳ ንጹሃን እንዲገደሉ መቀሰቀስ ዓለም ዓቀፍ ወንጀል በመሆኑ አገራቱ ክሱን ለመመስረት አሳብ ሲቀርብላቸው በቂ የሰነድና የምስል ማስረጃ ከሙሉ ትርጉሙ ጋር እንደቀረበላቸው ከዜናው ባለቤቶች ለመረዳት ተችሏል።

“በውል ከሚታወቁት የዕልቂት ስብከት አቀጣጣዮች ጀምሮ እስከ አገር ቤት ያለው ትስስር፣ የገንዘብ ዝውውርና የገንዘብ ዝውውሩ አከናዋዮች በውል በማስረጃ ተለይተዋል” ሲሉ ያስታወቁት የመረጃው ባለቤቶች፣ ለሽብር ስራ ገንዘብ የሚያዋጡ ወይም እንዲዋጣ የሚያስተባበሩትን ጨምሮ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።

“እነማን ናቸው” በሚል የተጠቀሰው አይነት ክስ የሚመሰረትባቸውን እንዲገልጹ የተጠየቁት እነዚሁ ክፍሎች ” ለጊዜው ዝርዝር መናገር ያስቸግራል። ግን ብዙም ሚስጢር አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ይሁን በሌላ ጀርመን አገር የሚኖረው ዘመድኩን በቀለ (ዘመዴ) ” የጀርመን ፌደራል ፖሊስ ተከሰሃል። ስለዚህ ቃልህን ልንቀበል በሚቀጥለው ሳምንት ለጥያቄ እንፈልግሃለን ነው ያለኝ” ሲል ለተከታዮቹ መረጃ አድርሷል። አያይዞም ጠበቃ ቀጥሮ ለመከራከር ይችል ዘንድ ” እኔ ነኝ ያለ ጠበቃ አቁሜ ነውና የምሟገተው እያንዳንድሽ አዳሜና ሔዋኔ ሳትወጂ በግድሽ ከአጠገቤ ትቆሚያለሽ አትቆሚም…? አለቀ። አዳሜ ቃላችሁን ስጡ። ቁጭ አሁኑኑ ” ሲል የገንዘብ ድጋፍ ጠይቋል።

ዘመድኩን ከሳምንት በፊት እረፍት እንደሚወጣና መጻፍ ለተወሰነ ጊዜ እንደሚያቆም አስታውቆ ነበር። እረፍት እንደሚያስፈልገው ሲያትት “…ዘመዴ ሆዬ… ወዬ… ይሄ ሳምንት የተባረከ የእረፍት ጊዜ ይሁንልህ ብዬ እኔው ራሴው ለእኔው ለራሴው የእረፍት ፈቃድ ሰጠሁ። ሃይ እህዕ ይሞታል እንዴ አባቴ…? አዎ ዘመዴ ትንሽ እረፍ አልኩት ራሱ ዘመዴን። እንዲያው ለምናልባቹ የግድ የሚል አጣዳፊ ጭቅጭቅ፣ ሙግት፣ ክፍትአፍነቴን የሚፈልግ ጉዳይ ድንገት ቢመጣና ብንፈልግህ ቶሎ ደርሰህ ትመለስ ይሆናል እንጂ ለጊዜው ግን ትንሽ እረፍ ብዬ ዘመዴን እኔው ራሴ እረፍት ሰጠሁት እላችኋለሁ። ደግ አደረግኩ አይደል…?” ብሎ ነበር።

የጀርመን የመረጃ ደህንነት ተቋምና ፖሊስ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት ለመስራት ስምምነት ማድረጋቸውን አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት የፊርማ ስነስርዓት ላይ ማረጋገጣቸውን የመንግስት መገናኛዎች በቅርቡ መዘገባቸው ይታወሳል።

Exit mobile version