ETHIO12.COM

የላሊበላ ሰላም የነዋሪዎቿ የልብ ትርታ – ከንቲባ ዲያቆን ተፋራ ሰይፉ

በአማራ ክልል የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው ከነበሩ ከተሞች መካከል ላሊበላ አንደኛዋ ናት፡፡ የድንቅ አብያተ ክርስቲያናት መገኛ፣ የቅዱሳን ነገሥታት አሻራዎች ያሉባት፣ የቱሪስቶች መዳረሻዋ ላሊበላ የጸጥታ ችግር ገጥሟት ነበር፡፡

የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ኑሯቸው በቱሪስት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኑሯቸው የሰመረ ይኾን ዘንድ ደግሞ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ መምጣት አለባቸው፡፡ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ እንዲመጡ ደግሞ ሰላም ሊኖር ግድ ይላል፡፡ ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ ከቀጥሎም በነበረው የወረራ ጦርነት ላሊበላ ከተማ የቱሪስት እንቅስቃሴዋ ተቀዛቅዞ፣ እንግዳ ተቀባይ ነዋሪዎቿ እንግዳ ናፍቀው ነበር፡፡

ጦርነቱ ከተጠናቀቀ ማግሥት በከተማዋ ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪስት እንቅስቃሴ መነቃቃት አሳይቶ ነበር፡፡ ከሰሞኑ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ደግሞ የቱሪስት እንስቃሴው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው ነው የተባለው፡፡ የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ለቀናት ከነበረችበት የጸጥታ ችግር ወጥታ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ መመለስ ጀምራለች፡፡

የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ዲያቆን ተፋራ ሰይፉ የላሊበላ ከተማ ዋና የቱሪስት መዳረሻ የኾነችና ሕዝቧም ጨዋና እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም እጦቱ ወደ ቀውስ እንዳያመራ በሃይማኖት አባቶችና በሀገር ሽማግሌዎች ውይይት ሲያደርጉ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ ጦርነት እንዳይካሄድ የመንግሥትና የግል ተቋማት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ሰፊ ውይይት እያደረጉ መምጣታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከሰሞኑ በነበረው የሰላም እጦት የሰው ሕይወት መጥፋቱን እና የአካል ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል፡፡ ከተማዋ አሁን ላይ ከግጭት ወጥታ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ መመለሷንም ገልጸዋል፡፡ ከግጭቱ ማግሥት የግል ተቋማትና የመንግሥት ተቋማት ተከፍተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ሆቴሎች ተከፍተው ሕዝቡም ሰላማዊ እንቅስቃሴውን እያደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በረራው ተቋርጦ የነበረው የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ ከትናንት ጀምሮ አገልግሎት እየሠጠ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ በረራ በመጀመሩ በከተማዋ የነበሩ እንግዶች ወደ መጡበት አካባቢ በሰላም እየተመለሱ መኾናቸውን እና ሌሎች እንግዶችም ወደ ከተማዋ እየገቡ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡ ላሊበላ አሁን ጥሩ ሰላም መኖሩንም አመላክተዋል፡፡

የሰላም እጦት አጠቃላይ የማኅበረሰብን እንቅስቃሴ ይገድባል ያሉት ከንቲባው ቱሪዝም ደግሞ ነጻ የሕዝብ እንስቃሴን የሚጠይቅና ከምንም በላይ ሰላም የሚያስፈልገው ዘርፍ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ጊዜ የነበረው የወረራ ጦርነት የላሊበላን የቱሪስት እንስቅስቃሴ በእጅጉ ጎድቶት እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ጦርነቱ ካቆመ በኋላ ቱሪዝሙ መነቃቃት ጀምሮ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ አሁን የተፈጠረው ችግር መነቃቃት ጀምሮ የነበረውን ቱሪዝም የለም ወደ ሚባል ደረጃ የሚያደርስ ስለኾነ ላሊበላ ላይ ሰላም ሊኖር ግድ እንደሚል ገልጸዋል፡፡ ላሊበላ በቀደመው የቱሪስት መዳረሻነቷ እንድትቀጥል ሁሉም ለሰላም ሊሠራ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ሰላም ሲናጋ በከተማዋ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች ተስፋ እየቆረጡ ከተማዋን እንደሚለቁም ተናግረዋል፡፡ የሰላም እጦት በቱሪዝም ብቻ ሳይኾን በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውም ትልቅ ተፅዕኖ እየፈጠረ መኾኑን ነው ያስታወቁት፡፡ ሰላም ለላሊበላ የልብ ትርታ ነውም ብለዋል፡፡ ሰላም እንዲረጋገጥ መንግሥት የመንግሥትነት ድርሻውን መሥራት እንደሚገባውና ሕዝቡም የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት ነው ያሉት፡፡ ሕዝብና መንግሥት ተቀራርበው መሥራት አለባቸውም ብለዋል፡፡ ሰላም ሲታጣ የሚኖር ትርፍ እንደሌለ በመግባባት ሰፋፊ ውይይቶችን በማድረግ ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ከሕዝብ ጋር በመወያየት ወደ ግጭት የወሰደውን ምክንያት በመለየት ደረጃ በደረጃ ችግሮችን መፍታት ከተቻለ ሰላምን መመለስ የማይቻልበት ምንም ምክንያት የለምም ብለዋል፡፡ ሁሉም የሰላም ሰባኪ መኾን እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡

አሚኮ


Exit mobile version