የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ ከኮሮና ቫይረስ በፊት በዓመት ከተማዋን ከ40 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ይጎበኟት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ኮቪድ 19 እና የሰሜኑ ጦርነት የቱሪስት እንቅስቃሴውን በእጅጉ ማሽቆልቆሉን አንስተዋል፡፡ ከሰሜኑ ጦርነት ማግስት ተፈጥሮ በነበረው ሰላም የቱሪዝሙ እንቅስቃሴው መነቃቃት አሳይቶ ነበር፡፡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችም ከኮሮና ቫይረስ በፊት እንደነበረው በስፋት ባይመጡም በርከት እያሉ መጥተው ነበር ነው ያሉት፡፡
በክልሉ አሁን ያለው የጸጥታ ችግር ደግሞ ቱሪዝሙን እንደገና ጎድቶታል፡፡ የሆቴል ባለሃብቶች፣ አስጎብኚዎች፣ የቤተክርስቲያኗ አገልጋዮች ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው ያሉት፡፡ የከተማዋ ምጣኔ ሃብትም ደቅቋል ብለዋል፡፡ አምራጭ በማጣታቸው አስጎብኚዎችን ከተማ አሥተዳደሩ በሚያመቻቸው የቀን ሥራዎች ጭምር እንዲሠማሩ፣ እቅድ አቅደው እንዲመጡ እና ብድር እንዲመቻችላቸው እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ግን ብድር ለማግኘት አስቸጋሪ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ሆቴሎች በሰሜኑ ጦርነት የወደመባቸውን ሃብት ለማካካስ ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ እየተጠየቀ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ሥለዚህ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ለሰላም ዘብ መቆም አለበት ብለዋል፡፡ የሁሉም መሠረት የኾነውን ሰላምን ሳይዙ ቱሪዝምን ማሰብ አይቻልም ነው ያሉት፡፡ ሰላሙ ከተረጋገጠ ቱሪዝሙ ወደ ነበረበት የማይመለስበት ምክንያት አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ ለቱሪዝም የሚመቹ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነወ ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ አሁን ያለው የክልሉ ነበራዊ ሁኔታ በቱሪዝም ላይ ገቢያቸውን መሠረት ያደረጉ አካባቢዎችን ጎድቷል ነው ያሉት፡፡ ቱሪዝም የተረጋጋ ሰላምን፣ የተመቻቸ ሥፍራ ይፈልጋልና፡፡ ሰላምና ጎብኚዎችን የሚስብ ውበት ለቱሪዝም ወሳኝ ጉዳይ ነው፤ ሰላም ከሌለ ምንም የለም፡፡
ላሊበላ የምጣኔ ሃብት መሠረቷ ቱሪዝም ነው፣ ላሊበላ ውስጥ ከቱሪዝም የማይጠቀም የማኅበረሰብ ክፍል የለም ይላሉ፡፡ የሰላም እጦቱ ቱሪዝሙን ጎድቶታ፤ ቱሪዝሙ ሲጎዳ ተጠቃሚው ማኅበሰረብ አብሮ ተጎድቷል ነው ያሉት፡፡ በሰሜኑ ጦርነት በላሊበላ የሚገኙ ሆቴሎች ትርፋ ማጣታቸው ብቻ ሳይኾን ወድመዋል፣ ተዘርፈዋል ብለዋል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት የተጎዳውን በጥናት ተመስርቶ ለማቋቋም እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ሆቴሎች ከውጭ ከቀረጥ ነጻ እቃ እንዲያስገቡ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ አስጎብኚዎችም ተጠቃሚ የሚኾኑበትን አሠራር መዘርጋቱንም አንስተዋል፡፡ ከችግሩ ሙሉ ለሙሉ ለመውጣት ግን ሰላምን አረጋግጦ ወደ ቱሪዝም እንቅስቃሴው መመለሰ ነው ብለዋል፡፡
ለተቸገሩት ለመድረስ፣ ሰላምን ማንገሥ ግድ ይላል፡፡ እንግዳ የናፈቃትን እንግዳ ተቀባይ ከተማ እንደ ቀደመው ሁሉ እንግዶች እንዲርመሰመሱባት፣ በየጎዳናዎቿ እንዲመላለሱባት፣ ሁሉም ስለ ሰላም ይነሳ፤ ሁሉም ሰላምን ጋሻው ያደርግ ዘንድ ግድ ይለዋል፡፡
Via አሚኮ