ETHIO12.COM

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን አጋላጭ ምክንያቶች

 የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሽንት ስርዓት አካላትን ማለትም (ኩላሊትን፣ የሽንት ፊኛን እና የላይኛውን እና የታችኛውን የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦዎች) የሚያጠቃ የኢንፌክሽን አይነት ነው።

ብዙዎቹ ኢንፌክሽኖች የታችኛውን የሽንት ቧንቧዎች እና የሽንት ፊኛን የሚያጠቁ ሲሆን÷ኢንፌክሽኖች ከሽንት ፊኛ አልፈው ወደ ኩላሊት ከተሻገሩ አሳሳቢ የጤና እክል ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ለመሆኑ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን አጋላጭ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሚከሰተው ባክቴሪያ ወደ ሽንት ቧንቧ ገብቶ በሚራባበት ወቅት ነው።

የሽንት ስርዓት በተፈጥሮ ባክቴሪያዎችን እንዲያስወግድ የተሰራ ቢሆንም አንዳንዴ ተፈጥሮአዊው መከላከያ መንገድ አሰራሩን በማሽነፍ ባክቴሪያዎች ወደ ሰውነት ገብተው በሽታ ሊያመጡ ይችላሉ።

ሌላው በተፈጥሮ ከብልት አቀማመጥ የተነሳ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የተጋለጡ ሲሆኑ የግብረ ስጋ ግንኙነት ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሴቶችን በተለይ የበለጠ ተጋላጭ ሊያደርግ እንደሚችል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሴቶች በተለይ ባላቸው የሰውነት አቀማመጥ ምክንያት በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት፣ በማህፀን ውስጥ በሚቀመጡ አንዳንድ የወሊድ መከላከያዎች እንዲሁም የሴቶች ማረጥ ጊዜ የበለጠ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ከፍተኛ ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ነው የተባለው።

ከነዚህም በተጨማሪ ጤናማ ያልሆነ የሽንት ቧንቧ ኖሯቸው የሚወለዱ ህጻናት፣ የሽንት ቧንቧ መደፈን፣ በኩላሊት ጠጠር ምክንያት፣ የበሽታ መከላከያ ስርዓት መጎዳት፣ አርቴፊሻል የሽንት ቱቦ (ካቴተር) የሚጠቀሙ ህመምተኞች፣ ሽንት ፊኛ፣ ፕሮስቴት ወይም የኩላሊት ቀዶ ጥገና ያደረጉ ሰዎች ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የበለጠ ተጋላጭ ናቸው፡፡

በቂ ውሃ መጠጣት ፣ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ የሽንት ቧንቧ አካባቢን ማጽዳት፣ እንዲሁም ውሃ በመጠጣት ባክቴሪያው እንዲወገድ ማድረግ፣ የሴቶች የተለያዩ  የብልት ማጽጃዎች እንደ ዴወደራንት እና  ፓውደር አለመጠቀም፣ የወሊድ መከላከያ መንገዶችን መቀየር ካለብዎ ከሐኪምዎ ጋር መማከር (በተለይ ተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ  ኢንፌክሽን የሚያጠቃዎት ከሆነ) የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን ለመከላከል ይረዳል፡፡፡


Exit mobile version