ETHIO12.COM

በሐሰተኛ የሽያጭ ደረሰኝ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ሽያጭ የፈጸመው ተጠርጣሪ ተያዘ

ሐሰተኛ የሽያጭ ደረሰኝ አዘጋጅቶ ለተለያዩ ነጋዴዎችና ድርጅቶች ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ በመሸጥ በከፍተኛ የማጭበረበር ወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በፊንፊኔ ከተማ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ።

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ሊውል የቻለው አድራሻው የማይታወቅ ሰለሞን ሙሉ ከውን በተባለ ግለሰብ ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት በዚሁ መታወቂያ የንግድ ፍቃድ በማውጣት የማሽነሪዎችና የመሣሪያዎች ኪራይና ሽያጭ የንግድ ዘርፍ ላይ ተመዝግቦ ምንም ዓይነት የንግድ ልውውጥ ሳያደርግና የሸጠው እቃ ሳይኖር ሐሰተኛ የሽያጭ ደረሰኝ ለተለያዩ ነጋዴዎችና ድርጅቶች በ30 ቢሊዮን 152 ሚሊዮን 434 ሺህ 002 ብር ከ03 ሣንቲም በመሸጥ መሆኑ ታውቋል።

ግለሰቡ የማጭበርበር ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ለበርካታ ጊዜያት ተደብቆ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከፊንፊኔ ከተማ ገቢዎች ጋር በመተባበር ባደረገው ጠንካራ ክትትል በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን አስታውቋል ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጾ ኅብረተሰቡም ወደ ኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ቢሮ በአካል ቀርቦ ተጨማሪ መረጃ በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጥሪ ማቅረቡን በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ዜናው የፌደራል ፖሊስ ነው


Exit mobile version