Site icon ETHIO12.COM

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መታወቂያን በማዘጋጀት እያስፈራራ ሲዘርፍ ነበር በተባለ ተጠርጣሪ ላይ ክስ እንዲመሰረት ተወሰነ

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተቋም መታወቂያን አስመስሎ በማዘጋጀት ሰዎችን እያስፈራራ ገንዘብ ሲቀበል ነበር በተባለ ተጠርጣሪ ላይ ክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።

የክስ መመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ሕግ የፈቀደው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሲሆን÷ተጠርጣሪው ነስሩ ሳሌ ጀማል ይባላል።

ግለሰቡ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሰራተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት ደህንነት ነኝ በማለት ግለሰቦችን በወንጀል እንደሚፈለጉ በመግለፅና መታወቂያውን በማሳየት ከግለሰቦች እስከ 200 ሺህ ብር ጀምሮ ሲቀበል እንደነበር ተመላክቷል፡፡

በዚህም ሀሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት የሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ሲከናወንበት መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ በዛሬው ቀጠሮ የምርመራ ስራ ማጠናቀቁንና መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን ለተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስታውቋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክተር ዐቃቤ ሕግ ችሎት ቀርቦ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ መረከቡን ገልጿል። መዝገቡን ተመልክቶም ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው የ15 ቀን ክስ መመስረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ተጠርጣሪው በበኩሉ ÷ ከዚህ በፊት ለፖሊስ ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ መፈቀዱን ጠቅሶ በድጋሚ ለክስ መመስረቻ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ አይገባም በማለት የዋስትና መብቱ እንዲፈቀድለት ጠይቋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ችሎቱ ዐቃቤ ሕግ መዝገቡን ተመልክቶ ክስ ለመመስረት ጊዜ እንደሚያስፈልገው በማመን የተጠርጣሪውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዐቃቤ ሕግ የ15 ቀን ክስ የመመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል። ውጤቱን ለመጠባበቅም ለመስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ ፋና


Exit mobile version