መግቢያ
ሽግግር ፍትህ ጉልህ የመብት ጥሰቶች በተፈፀመባቸው ሀገራት ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ተበዳዮችን ለመካስ ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል፡፡ በሀገራችንም የሽግግር ፍትህ አስፈላጊነት ታምኖበት ፖሊሲ ሲዘጋጅ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ፖሊሲ ተጠናቆ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀ ሲሆን ይህ አጭር ፅሁፍ ፖሊሲው በያዛቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ይሆናል፡፡
የፖሲው ይዘት አወቃቀር
የፖሊሲው በመግቢያ በሀገራችን በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱ እና የቀጠሉ ተደራራቢ እና ሰፊ የተጎጂና የአጥፊ ወሰን ያላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ያልጠሩ ትርክቶች እና በደሎችን ለመፍታት የተደረጉ የተለያዩ ሙከራዎችን የሚያብራራ እንዲሁም አሁን ለምን ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ እንዳስፈለገ የተብራራበት ነው። ፖሊሲው ሶስት ዋና ዋና ክፍሎችን የያዘ ሲሆን የመጀመሪያው ክፍል ጠቅላላ የፖሊሲ ጉዳዮች የተገጸበት ሲሆን ሁለተኛው ክፍል የፖሊሲ ጉዳዮችና አቅጣጫዎች የተተነተነበት ነው። የመጨረሻው ክፍል የመንግስት እና የባለድርሻ አካላት ሚና እና የክትትል እና ድጋፍ ሥርዓት ተብራትተውበታል።
የፖሊሲው ዝርዝር ይዘት
በፖሊሲው ክፍል አንድ ሥር የፖሊሲው ዓላማ በግልጽ የተብራራ ሲሆን ይኸውም የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውድ መሰረት ያደረገ፣ የተቀናጀ እና የተናበበ የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚመራበት እና የሚተገበርበትን ሥርዓት በመዘርጋት ዘላቂ ሰላም፣ ዕርቅ፣ የህግ የበላይነት፣ ፍትሕ እና ዲሞክራሲ የሚረጋገጥበትን መደላድል መፍጠር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል። ፖሊሲው የሚመራበት መርሆዎችም በጥልቀትና በዝርዝር የተብራሩ ሲሆን ዋና ዋና መርሆዎቹም ሰብአዊ መብት ተኮር የትግበራ ሂደት፣ ከጥቃት ወይም ከጉዳት መጠበቅ፣ አገራዊ ባለቤትነት፣ አውድ ተኮር የአተገባበር ሥርዓት፣ ተጠያቂነት፣ ሁለንተናዊነት፣ አካታችነትና አሳታፊነት፣ ሥርዓተ-ጾታ ተኮር አተገባበር፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ የህበረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ እና ሀገር በቀል የግጭት አፈታት እሴቶችን ጥቅም ላይ ማዋል ናቸው።
በክፍል ሁለት ሥር የፖሊሲው ጉዳዮችና አቅጣጫዎች የሚል ዋና ርዕስ ያለው ሆኖ አምስቱ የሽግግር ፍትህ አምዶችን አስመልክቶ ፖሊሲው ተግባራዊ የሚሆንበትን አግባብ የተብራራበት ነው።
በዚሁ አግባብ የመጀመሪያው የሽግግር ፍትህ አምድ የሆነው የወንጀል ተጠያቂነት ሥር አራት ዋና ዋና ጉዳዮች የታዩ ሲሆን እነዚህም ምርመራ እና ክስ የሚወሰንባቸው ወንጀሎች፣ ምርመራ የሚከናወንባቸው እና ክስ የሚመሠረትባቸው አጥፊዎች፣ ወንጀል ምርመራ እና ክስ የሚከናወንበት ተቋማዊ ሥርዓት እና የፍርድ ሂደት የሚከናወንበት ተቋማዊ ሥርዓት ናቸው። .
ከወንጀል ምርመራና ክስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ሂደት ጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ከባድ ወንጀሎችን መለየት የሚያስችል ግልፅ መለያ መስፈርት በመዘርጋት ጉልህ በሆኑ ወንጀሎች ላይ ትኩረት ያደረገ የክስ ሂደት ይከናወናል። በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ሂደት የወንጀል ምርመራ የሚካሄድባቸው እና ክስ የሚመሰረትባቸው አጥፊዎችን በተመለከተ በጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ከፍተኛ ደረጃ የወንጀል ተሳትፎ ያላቸው አጥፊዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰት ድርጊት የተሳተፉ ነገር ግን ከፍተኛ ደረጃ የወንጀል ተሳትፎ የሌላቸው አጥፊዎችን እንደየአግባብነቱ ሌሎች የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን በመጠቀም ጉዳያቸው የሚታይበትና መፍትሔ የሚሰጥበት ሥርዓት እንደሚዘረጋ ተብራርቷል።
የክስ ስራ የሚከናወንበት ተቋማዊ ሥርዓትን በተመለከተ አሁን ካለው የወንጀል ምርመራ እና ዐቃቤ ሕግ ተቋም ውጪ በሆነ፣ ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ራሱን ችሎ በሚቋቋም እና የሕዝብ አመኔታ በሚኖረው አዲስ የልዩ ዐቃቤ ሕግ ተቋም አማካኝነት የሚከናወን እንደሆነ በፖሊሲው ላይ ተቀምጧል። የፍርድ ሂደት የሚከናወንበት ተቋማዊ ሥርዓትን በተመለከተ በነባሩ ፍርድ ቤት ውስጥ የሽግግር ፍትህ ጉዳዮችን ብቻ የሚመለከት ልዩ ችሎት እንደሚቋቋም ተቀምጧል።
በሽግግር ፍትህ ሥርዓት ሁለተኛው አምድ እውነትን ማፈላለግ፣ ይፋ ማውጣት እና የዕርቅ ተግባር ሲሆን በፖሊሲው እውነት የማፈላለግ፣ ይፋ የማውጣት እና የዕርቅ ስራ በሁሉም ጉልህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ በማተኮር የጥሰቶችን መሠረታዊ ምክንያቶች፣ ተከታታይነት፣ ስልታዊነት፣ መጠነ-ሰፊነት፣ ዓይነት እና የጉዳት መጠን በመለየት ተግባራዊ እንደሚደረግ የተብራራ ሲሆን እውነትን የማፈላለግ፣ ይፋ የማውጣት እና የዕርቅ ተግባራት ከተጽዕኖ እና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ በሚቋቋም አዲስ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን አማካኝነት እንደሚከናወን ተቀምጧል።
በቅድመ−ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ምህረት ሶስተኛው አምድ ሲሆን ለምህረት ብቁ የሚያደርጉ ቅድመ ሁኔታዎችን በተመለከተ የሽግግር ፍትህን በሚያሳልጥ፣ የሕግ የበላይነት እና ተጠያቂነትን በማያስቀር መልኩ በቅድመ−ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ ምህረት በአግባቡ ተዘርዝረው እና ለምህረት ብቁ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ተብራርተው በፖሊሲው ውስጥ ተመላክቷል። የምህረት ተግባር የሚከናወንበት ተቋማዊ ሥርዓት ከእውነት ማፈላለግ፡ ማውጣትና ከዕርቅ ተግባራት ጋር በተሰናሰለ እና ተመጋጋቢ በሆነ መንገድ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኑ ምህረት የመስጠቱን ተግባር በተደራቢነት እንደሚያከነውን ፖሊሲው አስቀምጧል።
ተግባራዊ የሚደረጉ የማካካሻ ዓይነቶች እና ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮችን በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ አቅምን እና ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተግባራዊ የሚደረጉ የማካካሻ አይነቶች በዋናነት መልሶ ማቋቋም፣ የማገገሚያ እርምጃዎች፣ ፈውስ፣ የመታሰቢያ እና ማስታወሻ ክንዋኔዎች፣ የጥሰቶችን ሙሉ ሀቅ ማፈላለግ፡ ይፋ ማውጣት እና እውቅና መስጠት እንዲሁም ለተፈጸሙት በደሎች በመንግስት ደረጃ ይፋዊ ይቅርታ መጠየቅ ወዘተ ናቸው። የማካካሻ ሥራን ምህረት ከመስጠት እና ከእውነት ማፈላለግ፡ ይፋ ማውጣትና ዕርቅ ተግባር ጋር በተሰናሰለ መንገድ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽኑ የማካካሻ ስራዎችን የሚያከናውን መሆኑን በፖሊሲው ላይ ተብራርቷል።
ተቋማዊ ማሻሻያን በተመለከተ የተቋማዊ ማሻሻያ ሥራ ትኩረት የሚያደርግባቸው ተቋማት በዋናነት በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ በተሳተፉ ሰዎች፣ የዜጎችን ሰብአዊ መብት በማክበር ወይም በማስከበር ረገድ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ፣ ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ በሚችሉ አገራዊ እና ክልላዊ የፍትሕ፣ የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ መብትን ከማስከበር አኳያ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ ተቋማት፣ እና ለሰብአዊ መብት ጥሰት አስቻይ ሁኔታን በፈጠሩ ህጎች፣ ፖሊሲዎች እና አሰራሮች ላይ ቅድሚያ በመስጠት የማሻሻያ እንደሚደረግባቸው በፖሊሰው ላይ በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን የተቋማዊ ማሻሻያ ስራው ውጤታማ፣ ቀልጣፋ፣ ተቀባይነት እና የህዝብ አመኔታ እንዲኖረው ለማድረግ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ብቃት ባለው ተቋም ማለትም በህግ እንዲቋቋም በማድረግ ሥራው እንደሚመራ ተብራርቷል።
የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ የሚደረግበትን የጊዜ ወሰን በተመለከተ የሽግግር ፍትሕ የጊዜ ወሰን ለወንጀል ተጠያቂነት ዓላማ ‘የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ−መንግስት ከፀደቀበት ከ1987 ጀምሮ’ ያለው የጊዜ ወሰን ተፈፃሚ የሚደረግ ሲሆን ‘ለእውነት ማፈላለግ፣ ዕርቅ ማስፈን እና ማካካሻ ስራዎች ዓላማ’ ጥሰቶች እና ቅራኔዎችን ከመሰረታቸው በማጥራት ለመመርመር፣ ስብራቶች እንዲሽሩ እና እንዲጠገኑ ለማድረግ እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እንዲቻል የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ የተፈፃሚነት ወሰን ‘መረጃ እና ማስረጃ እስከተገኘበት ጊዜ ድረስ’ ይሆናል በማለት ፖሊሲው ላይ ተብራርቷል።
በሽግግር ፍትሕ ትግበራ የክልሎች ሚና በተመለከተ ክልሎች በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ሚናዎች የሚኖራቸው ሲሆን የመጀመሪያው በአገር−አቀፍ ተቋማት የሚከናውኑ ስራዎችን በማገዝ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአገራዊ ፖሊሲው አጠቃላይ እሳቤዎች እና እሴቶች ላይ በመመስረት ውስን የሽግግር ፍትሕ ስራዎችን ራሳቸው በባለቤትነት የሚመሩበትን ሂደት የሚመለከት ነው፡፡
በሽግግር ፍትሕ ባህላዊ የፍትህ ሥርዓቶች ሚና በተመለከተ ባህላዊ የፍትህ ሥርዓቶች ያሉባቸውን ክፍተቶች እንዲስተካከሉ በማድረግ በሚተገበረው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውስጥ ከሌሎች የሽግግር ፍትሕ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እውነትን በማፈላለግ፣ ዕርቅ በማስፈን፣ በማካካሻ እና ምህረት በመስጠት ተግባራት እንዲሁም ማህበረሰባዊ ሰላምን ለማስፈን በሚደረጉ ስራዎች ማእቀፍ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው በፖሊሲው ላይ ተብራርቷል።
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው እና የትግበራ ሂደቱ የባለብዙ ዘርፍ ጉዳዩች ማለትም ልዩ ትኩረት ለሚሹ እና ለጉዳት ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ለሴቶች፣ ለህጻናት፣ ለወጣቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋውያን እና ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ ፍላጎት እና ጥቅም ትኩረት በሚሰጥ አግባብ እንደሚከናወን በፖሊሰው ላይ ላይ በጥልቅ ተብራርቷል።
በክፍል ሶስት ሥር የመንግስት እና የባለድርሻ አካላት ሚና እንዲሁም የክትትል እና ድጋፍ ሥርዓት የተመለከቱ ጉዳዮች የተብራሩበት ሲሆን ዋና ዋና ጉዳዮችም በፖሊሲው መሰረት የሽግግር ፍትሕ ስራዎችን ተግባራዊ የሚያደርጉ ተቋማት በርከት ያሉ የሆኑ በመሆናቸው እነዚህ ተቋማት እንዲቋቋሙ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት አንስቶ ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ እስኪጀምሩ ድረስ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት ተግባር እና ኃላፊነት በዝርዝር የተቀመጠበት ክፍል ነው። ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪም የባለድርሻ አካላት ሚና እና የፖሊሲው አፈጻጸም፣ ክትትል እና ድጋፍ ሥርዓት በሰፊው ተብራርቷል።
የፍትህ ሚኒስቴር