Site icon ETHIO12.COM

ዝንጀሮዎች ለኒው ደልሂ የቡድን 20 ጉባዔ ስጋት ሆነዋል

የህንድ ዋና ከተማ ኒው ደልሂ ከ10 ቀናት በኋላ የቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባን ለማስተናገድ ጉባዔው በዝንጀሮዎች እንዳይረበሽ እየተዘጋጀች ነው።

ከተማዋ እንግዶቿን ለመቀበል እያደረገችው ባለው ሽር ጉድ ውስጥ ለአንድ ጉዳይ የተለየ ትኩረት ሰጥታለች፤ ዝንጀሮዎችን ከመሰብሰቢያ አዳራሽ የማራቅ ዘመቻ። በከተማዋ የተለያዩ አቅጣጫዎች አስፈሪ የዝንጀሮ ምስሎች እና ቅርጾችን እያስቀመጠች ሲሆን፥ የእንስሳት ድምጽን የሚያስመስሉ የሰለጠኑ ሰዎችንም ለማሰማራት አቅዳለች ተብሏል።

በኒው ደልሂ ከ20 ሺህ በላይ ዝንጀሮዎች እንዳሉና በየዓመቱ በአማካይ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በዝንጀሮዎች እንደሚነከሱ የታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ዘገባ ያሳያል። “ላንገርስ” የሚሰኙት ጥቁር ፊትና ረጅም ጭራ ያላቸው ዝንጀሮዎች ባህሪያቸው ቁጡ እና ሃይለኛ ናቸው።

በባለሙያዎች ቁጥጥር ካልተደረገባቸውም ጉዳት እንደሚያደርሱ የህንድ የዱር እንስሳት ጥበቃ ተቋም ይገልጻል። እናም ኒው ደልሂ ከፈረንጆቹ መስከረም 8 እስከ 9/ 2023 የምታስተናግደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ በዝንጀሮዎች እንዳይታወክ ከ30 በላይ የሰለጠኑ ባለሙያዎች በየሆቴልና ስብሰባ አዳራሹ ተመድበው ይሰራሉ ተብሏል።

የዝንጀሮዎቹን ድምጽ የሚያስመስሉት ባለሙያዎች ዝንጀሮዎቹ እንግዶቹን እንዳይረብሹ እንደሚያደርጉ ተገልጿል። ዝንጀሮዎቹ ምግብ ፍለጋ ወደ ስብሰባ አዳራሾች እና ሆቴሎች እንዳያንዣብቡም ከተማዋ በየሥፍራው የምግብ ማቅረቢያ እያዘጋጀች ነው ተብሏል።

ኒው ደልሂ በፈረንጆቹ 2014 የላንገርስ ድምጽ የሚያስመስሉና ወደ ፓርላማ እና ሌሎች ቢሮዎች እንዳይገቡ የሚያስፈራሩ 40 ባለሙያዎችን ቀጥራ ነበር። በ2010 የኮመንዌልዝ ጨዋታዎች በከተማዋ ሲደረግም አትሌቶች በእነዚህ ዝንጀሮዎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው 38 የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ማሰማራቷን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2015

Exit mobile version