Site icon ETHIO12.COM

“የሞተው ባልሽ ገዳዩ ወንድምሽ፣ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ”

Youngsters walk next to an abandoned tank belonging to Tigrayan forces south of the town of Mehoni, Ethiopia, on December 11, 2020. The town of Mehoni, located in Southern Tigray, experienced shelling resulting in civilian deaths and injured people. (Photo by EDUARDO SOTERAS / AFP)

የሞተው ባልሽ ገዳዩ ወንድምሽ (ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ) የሚለው የቆየ ተረት ልብን የሚያደማ ኩነትን ማሳያ ነው። እቺ መከረኛ ሚስት ባልዋ በእናቷ ልጅ ወንድሟ ተገደለ። ሟች ባል፣ ገዳይ ወንድም …

ኢህአፓ “ሃይማኖት ነው” በሚል ሲገልጸው በነበረው ትግል በቀይና ነጭ ሽብር ስም እናቶች የወላድ መካን ሆነዋል። ጧሪ ያጡና ባዶ ቤት ሃዘን አንጀታቸው አርምጦት የሞቱ ቤቱ ይቁጠራቸው። ከዛም ከዚህም ወገን ልጆች ወላጅ ፣ቤተሰብ አልባ ሆነዋል። “ነጭና ቀይ” ተብሎ የተሰየመው መተላለቅ አብዮቱ “ያለምንም ደም …” ተብሎ ተጀምሮ በደም ተጨማለቀና አለፈ። መንግስት ብቻ ሳይሆን “ታጋይ ታጋይ ነው፣ ፋኖ ተሰማራ…” ያሉት ሁሉም የደም መንገድ መርጠው ህዝብን ጥቁር ማቅ አለበሱት። የድም ታሪካቸውን ተሽክመው ነጎዱ!!

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ” የዘመናት ብሶት የወለደው” ብሎ አራት ኪሎ ከገባ በሁዋላ የዘር ምሶሶ ተክሎ ህዝብ ያማያውቀውን መለያየት እንደ ችግኝ አፈላብን። ለይቶ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን “ነፍጠኛ” ብሎ ለበላተኞች አሳልፎ ሰጠ። ይባስ ብሎ “አኖሌ” ብሎ በፈጠራ ታሪክ ሰርቶ ሃውልት አቆመ። ጥላቻንና ክፋትን የወንበሩ ማስጠበቂያ አድርጎ ትውልድን አከሸፈ። በዘር መደራጀትና መቧደንን ልዩ የንግድ ዘርፍ አድርጎ አስተዋወቀና አገሪቱን በኢንዱስትሪ ሳይሆን ጊዜ ጠብቀው በሚጫረሱ የዘር ድርጅቶች አጥለቀለቀ። ከዛም “ይጫረሳሉ” የተባሉ የሃያ ሰባት ዓመት ብሶት አጀገናቸውና አንድ ሆነው አስፈነጠሩት።

ትህነግ ከዳር እስከዳር አገሪቱን ላይ የዘራው የክፋት፣ የጥላቻና የመተላለቅ ዘር አብቦ ፍሬ ሊሰጥ ሲል በተወገደው ትህነግ እግር ብልጽግና ገባ። ብልጽግና አገር ውስጥ ተተክሎ ፍሬው ሊበላ የደረሰው የትህነግ ዘር እንዳይበቃ ” እኔ ዴሞክራሲያዊ ነኝ” ብሎ ወደ አገር ቤት ምንጣፍ አንጥፎ ያስገባቸው ሳይውሉ ሳያድሩ ሊበላ የደረሰውን የትህነግ የዛፍ ፍሬ እያፈሱ “እንወክልሃለን” ለሚሉት ሁሉ አዳረሱ። ለመስማት የሚቀፍ ፕሮፓጋንዳ ያለማቋረጥ በማከታተል “ወዲያውኑ ወደ ቤተመንግስት” በሚል ብልጽግናን አናወዙት።

ከቁንጮው እንጂ ከስሩ ያልጸዳው የቀድመው መዋቅር የአዲስ ገቢዎቹ መፍንጫ ሆነና አገር ለመስማት በሚከብድ፣ ለማይት በሚዘገንን ጭካኔ ሃዘን ከየአቅጣጫው ተሰማ ጀመር። የወደቀ ተነስፍስፈው የሚያነሱ፣ የታረዘን የሚያለብሱ፣ የተጠማን የሚያጠጡ፣ የሚመጸውቱ ዜጎች በባህላቸው አይተው የማያውቁት ጉዳይ ይሆን ጀመር። ሰው በቪዲዮ እየተቀረጸ፣ በጭፈርና በእልልታ ሲገደል፣ መግደል አይበቃም ተብሎ አስከሬኑ ሲሰቀል፣ መሰቀሉ አይበቃም ተብሎ በድንጋይ ሲወገር … አየን።

ለመግደል አቅደው፣ ገድለውና ሰቅለው እያሽካኩ ቪዲዮ የሚቀረጹ የ”ዘሩ” ፍሬዎች በተከፈላቸው መጠን እየከነፉ ቪዲዮ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲረጩ፣ ሻሞ ሲሉ የገባውም ያልገባውም ህዝብን ቁጣ ውስጥ እንዲከት ታስቦ የሚሰራውን አሰቃቂ ድራማ እየተቀባበለ ምሬትን አነገሰ። መዋቅር ውስጥ ሆነው የተጠለፉም የዚሁ ተባባሪ ሆነው በገፊና ጎታች ሴራ ህዝብ እንዲቆጣ አብዝተው ገፉት።

“በይቅርታና በፍቅር፣ በመድመር …” ተብሎ የተጀመርወና ” ኢትዮጵያ” በሚል የተቀጣጠለው አዲሱ የለውጥ ጎዳና በገባቸውና እንዳይገባቸው ሆነው በተቀረጹ ዜጎች፣ በሴራ በተካኑ እፉኝቶች፣ አገር ከረጋ ዘብጥያ እንደሚወርዱ ስጋት በገባቸው ባለብሮች፣ የዘር ፖለቲካ የንግድ ድርጅት ለመክፈት በተዘጋጁ ትርፍ ፈላጊዎች፣ ትህነግ ወደ አራት ኪሎ ለመመለስ በሚሾፍረው ባቡር በተሳፈሩ … ወዘተ እነ ግብጽን ጨምሮ ቀለማችንን ባይወዱ የውጭ አካላት የተገዙ አንድ ላይ ተዳምረው ለውጡን ገና ከንቡጡ አካለቡት። ከየአቅጣጫው ሴራ እየጠመቁና ብር እየረጩ የሚያስፈጽሙትን ዘግናኝ እልቂት፣ መፈናቀል፣ ስደት እንደ አካፑልኮ ፊልም በተከታታይ እያሰራጩ እንቡጡን ለውጥ አርገበገቡት። ገና ሲጀመር ጥርስ የተነከሰባቸው አብይ አህመድ “እርኛውን ምታ በጎቹ ይበተናሉ” በሚለው መርህ ስማቸው በደቦ ከውስጥና ከውጭ እንዲጠለሸ ሆነ። ” መከላከያን በደቂቃዎች ውስጥ አወላለቅነው” ባሉና በተዛበቱ መመራት ይሻላል እስኪባል ድረስ ፕሮፓጋንዳው የበላይ ሆነ።

አማራንና አፋርን ወሮ ለመዘርዘር የሚያታክት ወንጀል ፈጽሞ ሲያበቃ መጨረሻ ላይ በአማላጅ ” ለሰላም እጄን እሰጣለሁ” ያለው ትህነግ፣ “ወደ ትግራይ ሂድ” ብሎ ማን እንደገፋው እስካሁን በይፋ ባይገለጽም ” ስልታዊ እርምጃ” እንደሆነ ዛሬ ካናዳ የሚኖረው የሩሲያው የቀድሞ ሰላይ ያጋራው ድርሰት ምስክር ነው። ምንም ሆነ ምን ዛሬ ላይ የትህነግ ዕብሪት፣ ሰላማዊ ውይይትን የረገጠበት ዕብለቱ ምን ላይ እንደጣለውና ህዝቡ ለምን አይነት መከራ እንደተዳረገ ከምንም በላይ የትግራይ ህዝብ በውል አውቆታል። ዙሪያውን ጠላት ገዝቶላት በወጉ እንዳይታገዝና እንዳይረዳ አድርጎታል። ትህነግ ስልጣን ይዙ ሃብት ለማመንዠግ ሲል ምስኪኑን የትግራይ ህዝብ መያዣ አድርጎ እጅግ በሚዘገንና ልቡና ላለው ሁሉ የሚያም ደረጃ ላይ አድርሶታል። የጦርነቱ መዘዝና አሻራ ውሎ አድሮ ገና ብዙ ያሰማናል። ብዙ ጽሁፎች ይወጣሉ። የፈሰሰ አይታፈስ እንዲሉ ቢሆንም ሃዘኑ እንደ ሴትየዋ “ቅጥ አጣ” የተባለው አይነት ነው። ለሁሉም ነብስ ይማር!!

በዋናናት ትግራይ ቢጠቀስም፣ ከአንድ ባህር የሚቀዳው የትርምስ ሴራ ኦሮሚያ ውስጥ በተለይ አማራ ላይ የደረሰው በደል ዝም ብለው የሚያልፉት አይደለም። ወለጋ፣ ሻሸመኔ፣ ዝዋይ በዋነነት የሚጠቀሱ የጭካኔና ተግባር መፈጸሙን ማንም አይክደውም። መልኩን የሚቀያይረው ዘርን መሰረት ያደረገ የጭካኔ ተግባር ብዙ ስምና ባለቤት ቢሰጠውም ጉዳይ የገፊና ጎታች ሴራ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

በዘርና በሃይማኖት መልኩን እየቀያየረ ኢትዮጵያን ሊበላ የተነሳው ሴራ የተቀነባበረ ሴራ ስለመሆኑ በርካታ ማሳያ ማቅረብ ይቻላል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ ይህን በ”ፍቅርና ቀናነት ብቻ” በሚል የተጀመረው ለውጥ ላለፉት አራት አመታት በተለያዩ የቀውስ በትሮች ለማስለል ቢሞከርም ህዝብ አገሩን ይወዳልና አልተሳካም። ሁሉንም ጉዳይ ወደ አንድ አቅጣጫ በመግፋት፣ በራሱ በመንግስት ውስጥ ባሉ የሰው ብሎችና ሴረኛ የማህበራዊ ሚዲያ ፊት አውራሪዎች ቅስቀሳ ሁለት አይነት ዜጎች መፈጠራቸው አሳሳቢ ይሆናል።

1- ምሬት ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉና በምሬት ብዛት ቁጣ የሞላባቸው፣ ከቁጣቸው ብዛት ወደየትም አቅጣጫ ለመገፋት የተመቻቹ ” የትግሉ ደጋፊ” በሚባል የሚጠቀሱ

2- የሌሎችን ምሬት ለማብዛት ሲባል የሚረጨው ቅስቀሳ ” ማን ሞኝ አለ ቆሞ የሚጠብቅ” በሚል እንደ አቅማቸው ራሳቸውን ለመከላከል ዝግጅት የሚያደርጉና አጋጣሚ ጠብቀው ሲሳሳ ፍላጎታቸውን ለማርካት ነቅተው የተኙ

“አገራችንን እንወዳለን” የሚሉ እነዚህን ሁለት ወይም ሶስት ሃይሎች ግምት ውስጥ አስገብተው የነገሮችን አካሄድ ቢመረምሩ የአሁን ግብግብ መዳረሻ የማን አጀንዳ እንደሆነ ማየት ይችላሉ። እንዳያውቁና እንዳይመራመሩ የዘረኘት አድንቋሪ ፍሬ ሲያሻምዱ የኖሩት ሳይሆኑ ለህሊናቸው የቀረቡ የመንግስትን ተዘርዝሮ የማያልቅ በሽታ፣ የተጀመረው መልካም ነገር ሳይናድ እንዴት እንደሚገታ ውጥን ሊወጥኑለት ይገባል። በግርግርና በቁጣ ስሜት የብልጽግናን መንግስት ማዝመም እንደ ትህነግና ደርግ ቀላል እንደማይሆን አውቆ “ስጋት አይገባኝም እኔም ልግባበት” የሚል አጋር የሚያሰባስብ የሰከነ ትግልና የደረጀ ጨዋ አገራዊ፣ ያልተጠለፈ መዋቅር ግድ ይላል።

ዛሬ በኢትዮጵያ ሁሉም አልቃሽ፣ ተበዳይ፣ ሃዘነተኛ፣ ፍትህን ጠያቂ፣ የፍትህ ረሃብተኛ ወዘተ ነው። ሆኗል። እየሆነ ነው። ወደፊትም በዚሁ ይቀጥላል። የሚቆም አይመስልም። መክሰስ፣ መወንጀል፣ መፈረጅ፣ በደቦ መፍረድ፣ ማሸማቀቅ፣ ማስፈራራት፣ ተናቦ ማራከስ ወዘተ አንዱ ከሌላው የሚቀባበለው ወግና ባህል ሆኗል።

አዋቂዎች በፍርሃቻና በደቦ ዱላ ተሽብበዋል። ያውቃሉ የሚባሉ መልካም ዜጎች የደቦ ውርጅብኝ ፈርተው ዝም ማለታቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሰነበቴ ቤት፣ ከጠጅ ቤት፣ ከጠላ ቤት፣ ከጫት ቤት፣ ከየስርቻው ዳንኪራ ሰፈር … ያለ አንዳች ሃፍረት “እናውቃለን” በሚሉ እንዲነዳ አድርጎታል። ሚዛን የሚደፉና አመክንዮ የሞላባቸውን መረጃዎችና ንግግሮች መስማት ውግዝ ሆኖ ሃሰት፣ ዘለፋ፣ ሃሜት፣ ክብረነክ፣ የጅምላ ፍረጃና ማጠልሸት፣ ህዝብን ቁጣ ውስጥ የሚጥሉና ተስፋን የሚበሉ መረጃዎችን መስማት ቀዳሚ እውቀት እንዲሆን ሆኗል።

ሞተ፣ ተረሸነ፣ ተደፋ፣ ተቃጠለ፣ ወደመ … የሚሉ መረጃዎች ከዩቲዩብ የገቢ ምንጭነታቸው አልፈው እንዲህ ያሉ መረጃዎችን መለጠፍና ህዝብን ተስፋ ማስቆረጥ ጀማሪ አዲስ ሳይል ” ጀግና ” የሚያሰኝ ሆነ። ጭራሽ ቅጥፈትን ያለአንዳች ሃፍረት ማራባት ክብር የሚያሰጥ ተግባር፣ የሚያሸልምና በገሃድ “ጎ ፈንድ ሚ” የሚያሰከፍት ልዩ ምልክት ተደረገ።

ይህን ጽሁፍ ያዘጋጀሁት ለውጥ የምመኝ ዜጋ ነኝ። ከጥቂቶች በቀር አሁን ስልጣን ላይ ካለው መንግስት አያስፈጉም ባይ ነኝ። ጥንካሬ ያላቸው በዓለም ፊት ከፍ ብለን እንድንታይ የሚያደርገን ስራ የሰሩ ቀና አመራሮች መኖራቸውን ግልጽ ቢሆንም፣ ከትህነግ የወረሰውን ጨምሮ በርካታ ችግሮች ያለበት መንግስት መሆኑ ለአፍታም ሊታበል አይችልም። እናም ለውጥ ያስፈልጋል።

ዛሬ ላይ “አሮሙማ አማራን እይወጋ ነው” በሚል እኔን ጨምሮ ኦሮሞ አማራን እየወጋ እንደሆነ የሚነገረው ቅስቀሳ አግባብ አይመስለኝም። ዛሬ እኮ ኦሮሚያ ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ የአማራ ልጆች “አማራ” የሚለውን ስያሜ እስከመርሳት ደርሰው ኦሮሚያ እየኖሩ ነው። አምራ ክልልም የሚኖሩ ኦሮሞዎች አሉ። ታዲያ ኦሮሞ አማራ ላይ በህዝብ ደረጃ ጦርነት ካወጀ ለምን በክልሉ ውስጥ አብሮ በፍቅር እንደቀድሞ ይኖራል? ይህን ስል ወለጋን ጨምሮ በኦሮሚያ አማራ አልተፈናቀለም ወይም አልሞተም ለማለት ሳይሆን፣ ማንም ያድርገው ማን ጥፋቱ ኦሮሞን አይወክልም ለማለት ነው። ለምሳሌ ከአባይ በረሃ በአንገር ጉቲን እስከ ምስራቅ ወለጋ በርካታ ኦሮሞዎች ተዘርፈዋል። በተደጋጋሚ ወረራ ተፈጽሞባቸዋል። ተገድለዋል። ይህን ዜና ማንም ዜና አላደርገውም። ለእውነት ቆመናል የሚሉ ካሉ በአባይ በረሃ በአንገር ጉቲን እስከ ምስራቅ ወለጋ በሻምቡ፣ በሙገርና ወንጪ ስኳር አቅጣጫ ማን ምን እንዳደረገ የምርመራ ሪፖርት ስሩ። ሂዱና ገበሬውን አነጋግሩት።

ይህን ያነሳሁት ለኦሮሞ ለመሟገት ሳይሆን የሁሉም ጡዘት ማብቂያው አምራና ኦሮሞን ህዝብ ለህዝብ ወደለየለት ጦርነት ማስገባት ነው። ኦሮሞና አማራ ወደለየለት ጦርነት ከገቡ ኢትዮጵያ ምኗ ይተርፋል? እንደ ዜጋስ ምን እናገኛለን? ወንድም ወንድሙን እየገደለና ዘር ለይቶ በደቦ ከተጫረሰ መዋለድ ምን ሊሆን ነው? አብሮ መብላትና መጠጣትስ፣ ከሁሉም በላይ አገር አልባ አንሆንም? አገርና መንግስት አልባ የሆኑት ምን አገኙ? ሶማሊያ፣ የመን፣ ሊቢያን ያየ፣ አሁን ደግሞ እንደ ጧፍ እየነደደች ያለችውን ሱዳንን የሚመለከት ህዝብ እንዴት ጥበብን ሳተ? እንዴት በምናምንቴዎች ለመነዳት መረጠ? የሚል ጥያቄ እንዳነሳ ያስገድደኛል።

የዛሬዋ ኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ተቃዋሚዎች በጥንቃቄ ካልያዟት፣ በጥበብ ሊቀባበሏት ካልወሰኑ፣ ከምንም በላይ አብሮ በኖረ ህዝብ መቆመራቸውን አቁመው ወደ ጨዋ የፖለቲካ ፍልሚያ ካልተሸጋገሩ ” የሞተው ባልሽ ገዳዩ ወንድምሽ፣ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” እንደተባለው ከመሆን አንድንም።

የዛሬዋ ኢትዮጵያ በብዙ የዘረኛነት ነጋዴዎችና ችግር ጠማቂዎች ሴራ ሰለባ የሆኑ ፣ኑሮና ፕሮፓጋንዳ ተጋግዘው ቁጣ የዘሩባቸው፣ በማህበራዊ ሚድያ በሚረጭ ትርክት ተስፋ የቆረጡና በንጋዴዎች ደባ የተማረሩ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች ያሉባት አገር በመሆኗ ካልሰከንን ጣጣው የበዛ መሆኑንን ለማሳየት ያህል የጫርኩት ነው። የትጥቅ ትግል ንግድ እንደሆነ ከኔ መንደር ወደ ጫካ የሄዱና አሁን ተመልሰው እርሻ የጀመሩ መስክረውልኛል። አሁን ላይ ክፍያ ቆሞባቸዋል። የሚከፍሏቸው የነበሩት አሮባቸዋል። ሌላውም ሰፈር በተመሳሳይ ስላለመሆኑ እርግተኛ መሆን አይቻልም። ሰማይና ምድርን በተዓምራቱ ያጸና አምላክ ይርዳን።

ሳበቃ ይህ እላለሁ። ጽሁፉን ከኦሮሞነቴ ጋር አታያይዙት። ለውጥ እፍለጋለሁ። ግን ለውጥ እንዲመጣ የተመረጠው መንገድ እንደማይጠቅም በጻፍክትና በበርክታ ለጊዜው በልገለጽኩት ምክንያቶች በማርጋገጤ ስጋቴን በቀናነት ተረዱልኝ። የጋምቤላውን፣ የሶማሌውን፣ የኦሮሚያውን፣ የአማራ ክልል ውጊያን ገጣጥሙትና ምጽዋ ላይ ሚስጥሩን ፈልጉት። ስለምጽዋ በሚቀጥለው እጽፋለሁ። የምጽዋ ውሃ አይጠጣም። በምጽዋ ውሃ ቡኮም አይቦካም። እንጀራም አይሆንም። ነገሩ እንዲህ ነው። ምጽዋ ተቦክቶ የተጋገረ ዳቦና እንጀራ የለም። ያው “ቂጫ”!! ኤርትራ 22 ዓመታት እርከን ሲሰራ የነበረ ወንድሜ ብዙ አጫውቶኛል። አያይዛቸው ለራሳቸውን አይበጅም። እድሜ ይሰጠንና እናየዋለን።፡እስከዛው የአገሬ ልጆች ወደ ቀልባችን እንመለስ። በደም ጎርፍ መዋኘት ይብቃ!!

አቶምሳ አበበ ከሆለታ


Exit mobile version