Site icon ETHIO12.COM

የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጂቢ ኒውስ በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በጋዜጠኛነት ተቀጠሩ

ጆንሰን በቴሌቪዥን ጣቢያው የፕሮግራም አቅራቢ፣ አዘጋጅና ተንታኝ ይሆናሉ። በቀጣይ ዓመት የአሜሪካና የዩኬ ምርጫ በመዘገብ “ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ” ተብሏል። “የእንግሊዝን ኃይል የሚያሳይ መሰናዶ” ያቀርባሉም ብሏል ጂኒ ኒውስ። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዩች ምልከታቸውን ለማጋራት ቃል ገብተዋል።

በዴይሊ ሜይል ላይም አምደኛ የሆኑት ቦሪስ ጆንሰን ሥራቸውን በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ይጀምራሉ። ቦሪስ ጆንሰን በኤክስ ገጻቸው ላይ “ጂቢ ኒውስን እንደምቀላቀል ስነግራችሁ በደስታ ነው” ብለው ቪድዮ አጋርተዋል።

“በሩሲያ፣ ቻይና፣ ዩክሬንና ሌሎችም ጉዳዮች እውነተኛ ዕይታዬን አቀርባለሁ” ብለዋል። “እንግሊዝ በዓለም ስላላት ዕምቅ አቅምና ፈተናዎቻችንም እናገራለሁ” ሲሉ አክለዋል። ቦሪስ ከሥልጣን እንዲወርዱ ከፍተኛ ጫና መፈጠሩን ተከትሎ ነው አምና የወረዱት። በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ያሳዩት አመራር አሁንም ምርመራ እየተደረገበት ነው።

በዩኬ የቀድሞ መሪዎች ሥልጣን በለቀቁ በሁለት ዓመታት ስለሚይዙት ሥራ የሚያማክሩት አገራዊ ኮሚቴ አለ። ይህ ኮሚቴ ቦሪስ ጆንሰን ጂቢ ኒውስ መግባታቸው ከመንግሥት መርህ ጋር የሚጻረር ስላልሆነ ፈቅዷል። ሥልጣን ላይ ሳሉ ያገኟቸውን መረጃዎች ያለአግባብ እንዳይጠቀሙ መርሆች ተቀምጠዋል። በተጨማሪም ጂቢ ኒውስን ወክለው መንግሥት ላይ ጫና እንዳያደርጉም ጥንቃቄ ይደረጋል።

ይህ የሚሆነው ሥልጣን ከለቀቁበት ጊዜ በኋላ ላሉት ሁለት ዓመታት ነው። ቦሪስ ከሥልጣን በለቀቁ በአምስት ወራት ውስጥ በተለያዩ መሰናዶዎች ንግግር በማድረግና የግል የሕይወት ታሪካቸውን ለመጻፍ በመስማማት አራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ፓውንድ አግኝተዋል። ጂቢ ኒውስ ከዚህ በፊት ታዋቂው ኮሜድያን ጆን ክሊስን ቀጥሯል። ጣቢያው ቦሪስ ጆንሰንን ከቀጠረ በኋላ የተመልካቾቹ ቁጥር ከፍ እንደሚል ይጠበቃል።


Exit mobile version