Site icon ETHIO12.COM

የአርሂቡ ሪል ስቴት ግንባታ ታገድ፤ በስራ ላይ እያሉ በሞቱት ሶስት ሰራተኞች ሳቢያ በህግ ሊጠየቅ ነው

በአዲስ አበባ ባሳለፍነው ዓርብ በአርሂቡ ሪል ስቴት ሕንጻ ግንባታ ሥራ ላይ የነበሩ 3 ሠራተኞች ሕይወታቸው ማለፉን ተከትሎ የሕንጻው ግንባታ እንዲቆም መደረጉን የከተማዋ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡ የህግ ጥያቄም እንደሚነሳበት ተመልክቷል ፋና እንዳለው ባለስልጣኑ ጉዳዩን አጠንክሮ ይዞታል።

የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ዴሲሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ ባሳለፍነው ዓርብ በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በጅምር ግንባታ ላይ የሚገኝ ባለ 9 ወለል የአርሂቡ ሪል ስቴት ሕንጻ ግንባታ ሥራ ላይ የነበሩ 3 ሠራተኞች ሕይወት አልፏል፡፡

ሠራተኞቹ ሲሚንቶ ወደ ላይ የሚያወጡበት ጋሪ የተሸከመው የብረት ገመድ በመታጠፉ የብረት ገመዱን ለማስተካከል በእጃቸው ይዘው በሚያንቀሳቅሱበት ወቅት በአቅራቢያው ከነበረ የኤሌክትሪክ ገመድ ጋር በመገናኘቱ ከሕንጻው ወደ መሬት ወድቀው ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

ተጨማሪ አንድ ሰራተኛ ወደ ሕክምናተቋም መወሰዱን ያብራሩት አቶ ገዛኸኝ÷ሶስቱ ሠራተኞች ግን ወዲያውኑ ሕወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

የደረሰውን አደጋ ተከትሎም ሕንጻው የግንባታ እንቅስቃሴውን እንዲያቆም መደረጉን ነው ያስታወቁት፡፡

ከዚህ ባለፈም የሕንጻው ባለቤት፣ የአማካሪውንና የተቋራጩን የግንባታ ፈቃድ በመያዝ ከአደጋው ጋር በተያያዘ ማብራሪያ እንዲሰጡ መታዘዛቸውን ገልጸዋል።

በሕንጻ አዋጅና መመሪያ መሰረት ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመው÷ለጠፋው ሕይወትም በሕግ እንደሚጠየቁ አክለዋል ፡፡


Exit mobile version