ETHIO12.COM

አጭበርባሪው ኮሎኔል – በሐሰተኛ ማንነትና ሰነዶች ህብረተሰቡን ሲያጭበረብሩ የነበሩ ተያዙ

ልዩ ልዩ ሐሰተኛ ሰነዶችንና ዘዴዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡን ሲያጭበረብሩና ሲያታልሉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በመንግስት ባለስልጣናት ስም እየተጠቀሙ ”እነ እከሌን እናውቃለን፤ ጉዳያችሁን እንጨርስላችኋለን” እያሉ እያጭበረብሩና እያታለሉ ከህብረተሰቡ ከፍተኛ ገንዘብ የሚቀበሉ በመሆናቸው ፖሊስ ከነ-ኤግዚብቱ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ገልጿል።

ከዚህም ባለፈ ተጠርጣሪዎቹ ባለሃብት ሳይሆኑ ባለሃብትና ከፍተኛ ገንዘብ እንዳላቸው ለማስመሰል በርካታ የአሜሪካን ዶላር በሳምሶናይት ይዘው ፎቶግራፍ በመነሳት እራሳቸውን እያሳዩ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባል ሳይሆኑ አባልና ኮሎኔል ነን እያሉ እንዲሁም የብሔሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት የስራ ባልደረባ ሳይሆኑ ባልደረባና ደኅንነት ነን እያሉ በሐሰተኛ መታወቂያ ህብረተሰቡን ሲያጭበረብሩና ሲያታልሉ እንደ ቆዩ ፖሊስ አሰታውቋል።

ፖሊስ ምርመራውን በማስፋት ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ አውጥቶ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አካባቢ በሚገኘው የተጠርጣሪ ሞቱማ ደለሳ ቦሮቃ መኖሪያ ቤት ውስጥ ባደረገው ብርበራ ለወንጀል ተግባር ማስፈፀሚያ የሚገለገልበት 90 ሺህ ብር፣ አንድ ሽጉጥ ከ24 መሠል ጥይቶች እና ከ2 ካዝና ጋር እንዲሁም አይፎንና ሳምሰንግ ሞባይል፣ አንድ አፒድ ላፕቶፕ እና ሦስት ፍላሾች መያዙን ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።

ህብረተሰቡ በወንጀል መከላከል ውስጥ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ የበለጠ በማጠናከር በተመሳሳይ የወንጀል ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በማጋለጥ አሳልፎ ለፖሊስ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥሪውን ያቀርባል።

በመጨረሻም በእነዚህ ሰዎች ተታለልኩ ወይም ተጭበረበርኩ የሚል ማንኛው ሰው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ቢሮ ቀርቦ ሪፖርት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

ጥር 18 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢ ፕ ድ

Exit mobile version