Site icon ETHIO12.COM

በጩቤ በማስፈራራት ወጣቷን አስገድዶ የደፈራት ግለሰብ በ15 አመት ፅኑ እስራት ተቀጣ


ተከሳሹ አማኑኤል ሞገስ ይባላል፡፡ ዕድሜዉ 27ዓመት ሲሆን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ነዋሪ ነዉ፡፡ አስከ 10ኛ ክፍል ተምሯል ሆኖም ቋሚ ገቢ የሚያገኝበት ስራ የለዉም-ያላገባና ትዳር የሌለዉ መሆኑንም ጨምሮ ለመርማሪ ፖሊስ በሰጠዉ ቃል አስረድቷል፡፡

የግል ተበዳይ እድሜዋ 22 ዓመት የሆነና ከትዉልድ አካባቢዋ ወደ አዲስ አበባ መጥታ ስራ በመፈለግ ላይ የነበረች ወጣት ስትሆን ድርጊቱ ከመፈጸሙ 2 ቀን ቀደም ብሎ ስራ ፈላጊ መሆኗን ያወቀችዉ ጓደኛዋ ደላላ ነዉና አናግሪዉ ስራ ያስገባሻል ብላ የተከሳሹን ወጣት ስልክ ሰጥታት ደዉላ ካገኘችዉ በኋላ ግንቦት 12 ቀን 2012 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 5፡00 ሠዓት መገናኛ አካባቢ ይገናኛሉ፡፡

በዚሁ መሰረትም ተከሳሹ የግል ተበዳይን ፋብሪካ እንደሚያስገባት አሳምኖ ከከተማ ዉጪ በእግር ይዟት በመጓዝ ላይ ሳለ የግል ተበዳይ ሁኔታዉን ተጠራጥራ ልዩ ቦታዉ አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ካለዉ የመቃብር ስፍራ ሲደርሱ ወደኋላ ልትመለስበት እንደሆነ በመገመቱ በኪሱ የያዘዉን ጩቤ አዉጥቶ በማስፈራራት አስገድዶ ይደፍራታል፡፡

ከድርጊቱም በኋላ ከአካባቢው ሊሰወር ሲል ባሰማችዉ የድረሱልኝ ጩኸት በአካባቢዉ የነበሩ ሰዎች ቢደርሱላትም ተከሳሽ ያመለጠ መሆኑን የግል ተበዳይዋ በእለቱ ወደ ላምበረት ፖሊስ ጣቢያ ደርሳ የደረሰባትን በደል ሁሉ ባስረዳችዉ መሰረት የላምበረት አካባቢ ፖሊስ ባደረገዉ ክትትል ተከሳሽ በቁጥጥር ስር ሊዉል ችሏል፡፡

ከሳሽ ዐቃቤ ህግም ከፖሊስ ጋር በመሆን ምርመራውን በመምራት እና በምርመራ ሂደቱ በመሳተፍ ማስረጃዎችን በሚገባ ሰብስቦ ሲያበቃ ተከሰሹ ላይ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 620/1/ ስር የተደነገገዉን በመተላለፍ በፈጸመዉ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ መስርቶበት ጉዳዩ በክርክር ሂደት ላይ ቆይቷል፡፡

ተከሳሽ አማኑኤል ሞገስ በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ ወንጀል ችሎት ታህሳስ 4 ቀን 2013 ዓ.ም ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን ተጠይቆ የወንጀል ድርጊቱን እንዳልፈጸመና ጥፋተኛም እንዳልሆነ ክዶ ቢከራከርም ዐቃቤ ህግ ድርጊቱን ያስረዱልኛል ብሎ ያቀረባቸውን ማስረጃዎች የሰማው ፍርድ ቤት የቀረቡለትን የሰዉ ምስክሮች እና የግል ተበዳይን የጉዳት መጠን የሚገልጸዉን የህክምና ማስረጃዎችን መርምሮ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም ተከሳሽ መከላከያ ማስረጃ ማቅረብ ሳይችል በመቅረቱ በተከሰሰበት ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበታል፡፡

በዚህም መሰረትም የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሽን በ15 (አስራ አምስት ) ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡

ውድ የገጻችን ተከታዮች የልባችን መሻት ለማግኘት በምናደርገው ጥረት ውስጥ ላልጠበቅነው እንግልት እና አደጋ እንዳንጋለጥ ስለሚያግዙን ሰዎች ማንነት እና ባህሪ፣ ስላንበት ሁኔታ እና አካባቢያችንን በሚገባ መቃኘት እና አብዝቶ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ከደጋግ ሰዎች መካከል በሰዎች ስቃይ እና ጉዳት ሀሴት የሚያደርጉ ህገ-ወጦች አሉና ጠንቀቅ ማለቱ አይከፋም የእለቱ መልዕክታችን ነው፡፡

Attorney general Fb

Exit mobile version