የጉምሩክ የታክስ ኢንተለጀንስ ባለሙያ ጉቦ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ተያዘ

ሃሰተኛ ደረሰኝ አቅርበሃል በሚል ምክንያት ከአንድ ግብር ከፋይ ላይ 80 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበለ የገቢዎች ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የታክስ ኢንተለጀንስ ባለሙያ እጅ ከፍንጅ ተይዞ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪው ግለሰብ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ገቢዎች አነስተኛ ግብር ከፋይ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የታክስ ኢንተለጀንስ እና የኦፕሬሽን ባለሙያ ነው፡፡ በየካቲት ወር ውስጥ የግል ተበዳይን ፋይል አውጥቶ ስልክ በመደወል ሃሰተኛ ደረሰኝ ለመስሪያ ቤታችን አቅርበሃል በወንጀል ትጠየቃለህ ብሎ ወደ ቢሮ እንዲመጡ መጥራቱን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የግል ተበዳይ ወደ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ ቢሮ ከሄዱ በኋላ ከግለሰቡ ጋር ይገናኛሉ፡፡ ሃሰተኛ ደረሰኝ እንዳላስገቡ እና ይህንንም ማረጋገጥ እንደሚቻል ለባለሙያው ቢገልፁለትም ባለሙያው ግን ልትከሰስ ስለሆነ ጉዳይህን ከእኔ ጋር ተደራድረህ ብትፈታው ይሻልሃል ብሎ 140 ሺህ ብር ጉቦ ይጠይቃቸዋል፡፡ የግል ተበዳይም ከቤተሰብ ጋር ልማከር ብለው ከተለያዩ በኋላ ለ1 ወር ከ15 ቀናት ያህል ሳይገናኙ ይቆያሉ፡፡ ተጠርጣሪው ግን በድጋሚ ወደግል ተበዳይ ስልክ ይደውላል፡፡ ጭቅጭቁ የበዛባቸው የግል ተበዳይም ሁኔታውን ለገቢዎች የስራ ሃላፊዎች በማሳወቅ እና በጋራ በመሆን ጉዳዩን ለፖሊስ አመልክተዋል፡፡

ፖሊስም የቀረበለትን ጥቆማ ተቀብሎ ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪው ከግል ተበዳይ ላይ 80 ሺህ ብር ለመቀበል ተስማምቶ ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ/ም ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ፊናንስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ አንድ ባንክ ውስጥ ቀጥሯቸው ከተገናኙ በኋላ ገንዘብ ገቢ ማድረጊያ ፎርም በመሙላት 80ሺህ ብሩን ተቀብሎ ወደራሱ አካውንት ሊያስገባ ሲል እጅ ከፍንጅ ተይዞ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ሰዎችን በሃሰት ለመወንጀል በማሰብ እና በማስፈራራት እንዲሁም መብታቸውን በገንዘብ እንዲገዙ በማስገደድ የስነ ምግባር ጥሰት በሚፈፅሙ የስራ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች ላይ የሚደረገው ክትትል እና ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ መብታቸውን አውቀው ሙስናን በመጠየፍ ሙሰኞች በህግ እንዲጠየቁ የሚያደርጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቆማቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

አዲስ አበባ ፖሊስ

You may also like...

Leave a Reply