Site icon ETHIO12.COM

ክፉው ቀን ሳይመጣ ጆሮ ያለው ይስማ – ባለፉት ሰባት ቀናት 14 ሺህ 437 ግለሰቦች በኮቪድ19 ተይዘዋል 149 ሞተዋል

ባለፉት ሰባት ቀናት ከመጋቢት 17 እስከ መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 14 ሺህ 437 ግለሰቦች በኮቪድ19 መያዛቸው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቀ፡፡

የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው 100 ግለሰቦች ውስጥ 25ቱ ቫይረሱ እንደተገኘባቸውም ኢንስቲቲዩቱ ገልጿል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም 149 ግለሰቦች ህይወታቸውን አጥተዋልም ነው ያለው፡፡

በትናንትናው እለት ለ8 ሺህ 294 ግለሰቦች የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ 2 ሺህ 372 ሰዎች ኮቪድ-19 ሲገኝባቸው ይህም ከ100 ሰዎች 29ኙ ላይ ቫይረሱ እንደተገኘ ያሳያል ነው ያለው፡፡ አሁን ላይም የቫይረሱ ስርጭት በመላ ሃገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ነው ኢንስቲቲዩቱ የገለጸው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ህብረተሰቡም ሆነ መንግስታዊ አካላት የወጡ መመሪያዎችን በመተግበርና በሃላፊነት ስሜት በመንቀሳቀስ የቫይረሱን ስርጭት እንዲከላከሉም ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ መንግስት በኤግዚም ባንክ በኩል ባደረገው የ30 ሚሊየን ዶላር የረጅም ጊዜ ቀላል የብድር ስምምነት የተገዙ የህክምና መሳሪያዎችን መረከቡን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳስታወቁት የህክምና መሳሪያዎቹ የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲያግዙ የኢትዮጵያ መንግስት ከኮሪያ መንግስት በኤግዚም ባንክ በኩል ባደረገው የ30 ሚሊየን ዶላር የረጅም ጊዜ ቀላል የብድር ስምምነት የተገዙ ናቸው፡፡የህክምና መሳሪያዎቹም የኮቪድ19 መመርመሪያ መሳሪያ፣ የመተንፈሻ ድጋፍ ሰጪ
መሳሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የጽኑ ህሙማን ህክምና መስጫ ቁሳቁሶች ናቸው ተብሏል፡፡ለዚህም ሚኒስትሯ የኮሪያ መንግስት የኮቪድ ወረሽኝን በመዋጋት ሂደት ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን እያደረገ ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ via FBC


Exit mobile version