Site icon ETHIO12.COM

“ኢ-ፍትሃዊ ዓለም ውስጥ መኖራችን ያበሳጫል” አቶ አባተ ኪሾ

ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በህዝብ እንዲሁም በመንግስትና ህዝብ መካከል የቁርሾ ስሜቶች ተንጸባርቀው መቆየታቸው የሚታወስ ነው፤ ይህን የቁርሾ ስሜት ለማስወገድ እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ማውረድ ተገቢ ነው በሚል ተነሳሽነት ከዓመታት በፊት የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መውጣቱን ተከትሎ ስራዎች መጀመራቸው እሙን ነው:: ይህንኑ የእርቀ ሰላም ጉዳይ ያለበት ደረጃና ከሰሞኑን ስለተካሄደው የምርጫ ጉዳይን በተመለከተ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን የስራ አስፈጻሚ አባል እንዲሁም የቀድሞ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ከነበሩት ከአቶ አባተ ኪሾ ጋር አዲስ ዘመን ቆይታ አድርጎ የሚከተለውን አሰናድቷል:: መልካም ንባብ::

አዲስ ዘመን፡–ሰሞኑን መንግስት ከምርጫው ስኬታማነት ጋር ተያይዞ ለተለያዩ ባለድርሻዎች ምስጋና ሲያቀረብ ነበር፤

 ብዙዎች በተለይም ምዕራባውያኑ ምርጫው በሰላም እንደማይጠናቀቅ ከወዲሁ የተለያየ ግምት ሲያስቀምጡ ነበር፤

 ይሁንና ምርጫው በሰላም ተጠናቋል፤ በሰላም ለመጠናቀቁ በዋናነት ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?

አቶ አባተ፡ በቆይታዬ ብዙ ምርጫዎችን ለማየት ችያለሁ፤ በደርግ ጊዜም ምርጫ ነበር:: ኢህአዴግ ከመጣም በኋላ እንዲሁ ምርጫ ሲካሄድ ነበር:: ይህ ዘንድሮ የተካሄደው ደግሞ ስድስተኛው ምርጫ ነው:: ኢህአዴግ ከአንድ እስከ ሶስት ያካሄደውን ምርጫ አይቻለሁ:: አራትና አምስተኛው ላይ ግን አልነበርኩም:: የሆነው ሆኖ ቀደም ሲል የተካሄዱት ምርጫዎች በጣም ሰፊ ጉድለት የሚንጸባረቅባቸው ነበር:: ምርጫዎቹ አሳታፊ ያልነበሩ ናቸው:: ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም ፕሮግራማቸውን ወደ ህዝብ በአግባቡ ለማቅረብ ይቸገሩ ነበር:: ሲደረጉ የነበሩት ምርጫዎች ከደም ጋር የተጨማለቁ ነበሩ ማለት ይቻላል::

በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ ያካሄድነው ምርጫ በጣም በርካታ ተፎካካዎችን ያሳተፈ ነበር፤ እንዲያውም መጀመሪያ አካባቢ 90 ያህል ፓርቲዎች ነበሩ፤ በኋላ ላይ ግን ወደ አርባ አካባቢ ቢሆንም በዚህ ቁጥር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለመወዳደር ሲሳተፉ የመጀመሪያ ነው ማለት ይቻላል:: መሳተፋቸው ብቻ ሳይሆን ቀደም ብለወ በምርጫ ፕሮግራም ላይ ህግ በማውጣትና በጋራ በመወያየት ብዙ ርቀት ሄደዋል:: ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ታሪክ እምብዛም የሚታወቅ አይደለም:: ፖለቲከኞች በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየትና ተቀራርበው መነጋገር የቻሉበት ሁኔታ ማየት ችለናል:: ከዚህም ባሻገር እንደ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አይነት ፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያቀራርብ አንድ ድርጅት በእርቀ ሰላም ላይ የሚሰሩ አይነት ተነሳሽነቱ ያላቸው ተሰባስበው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያቀራርብ በምርጫ ዋዜማ የተጀመሩ ነገሮችን በአካል ተገኝተን አይተናል::

ይህ አካሄድ በጣም ሰላማዊ የሆነና ይቺን አገር በጋራ ወደፊት ለማሻገር ርዕይ የሰነቁ አካላት ተግባብተው ሲያወሩ የነበረበትን ሁኔታ ማስተዋል ችለናል:: ይህ ጉዳይ በህዝቡ ውስጥም ተመሳሳይ መንፈስ መፍጠር ችሏል ባይ ነኝ:: ይህ ማለት ተሸናፊው ለአሸናፊው እውቅናም ጭምር የሚሰጥበት፣ ተሸናፊም በአንድ ጀምበር የሚገነባ ስርዓት ስለሌለ በቀጣይ ጉድለቴ ምንድን ነው በሚል ራሱን በአግባቡ ፈትሾ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን የዚህቺን አገር የዴሞክራሲ ጥማት ለማሟላት ቃል ኪዳን የገባበትና የዴሞክራሲ መሰረት የጣለበት ወቅት ነው ባይ ነኝ:: በእርግጥ ቃል ኪዳኑን በተመለከተ አሁን የሁሉም አካባቢ የምርጫ ውጤት ባልተገለጸበት ወቅት እና እኔም ዝርዝር መረጃ ባይኖረኝም በአብዛኛው ግን የነበረው ሂደት ከተወሰኑ ጉድለቶች ባሻገር ልክ ነው::

እንዳልኩሽ ሁሉም ነገር በአንድ ጀምበር አይገነባም፤ አሁን ያለውን ነገር ማስተዋል ከተቻለ በህግ የመጠየቅ ድፍረቱ ካለ እስከዛ የመሄጃው መንገድ ምቹ ነው ማለት ይቻላል:: ምክንያቱም ይህን ጉዳይ በገቡት ቃል ኪዳናቸው ሲያረጋግጡ ሰምተናል:: እንዲሁም ቀደም ብሎ ደግሞ ህዝቡ በራሱ ፍላጎት በተመዘገበ ልክ ምንም እንኳ ጥቂት የማይባሉ አካባቢዎች ምርጫውን ወደ ጳጉሜን ላይ እንዲመርጡ ቢደረግም በሰኔ 14 የተሳተፈው አካል ግን የእኔ ድምጽ ትልቅ ዋጋ አላት በሚል እስከማታ ድረስ ተሰልፎ ድምጽን መስጠት ችሏል፤ እኔ ራሴም በመራጭነት መሳተፍ ችያለሁና ሁሉም ድምጼ ዋጋ አላት ወደሚልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ማለት ይቻላል::

እውነት ለመናገር ያለፉትም የራሳቸውን ትምህርት ሰጥተው አልፈዋል:: ይህ በመሆኑ ደግሞ ወደ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሂደት ሊያሸጋግረን የሚችል ምርጫ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል:: ዴሞክራሲ ገና እንጭጭ በሆነበት አገር ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አገር በጣም ዴሞክራሲን እያጣጣምን ነን በሚሉ አገራትም ጭምር በምርጫ ወቅት ትልቅ ችግር ሲፈጠር አስተውለናል:: በዚህ ጉዳይ በቅርቡ እንኳ በአሜሪካ የተፈጠረውን ችግር ማስተዋል ይቻላል::

እንዳልሽው የውጭ አገር ሚዲያዎች ምርጫው በሰላም ይሸጋገራል ብለው አላሰቡም ነበር:: በነገራችን ላይ እነዚህ አገራትም ሆኑ በእነርሱ የሚመሩ ሚዲያዎቻቸው ኢትዮጵያን አያውቋትም:: ኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ ያላትና የረጅም እድሜም ባለቤት የሆነች አገር ናት:: እንደ አገር እድሜዋ ሲሰላ የሶስት ሺህ እድሜ ያላት:: በአሁኑ ሰዓት ጫና ለማሳደር የሚንደረደሩ አገራት የቅርብ ጊዜ ናቸው:: በእነሱ እድሜ ልክ እንኳ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያኑን አለማወቃቸው እንደ መንግስት የራሳቸውን ስርዓት ይዘው የመጡ  ህዝቦች መሆናቸውን ያልተገነዘቡ መሆናቸውን ነው የሚያመለክተው::

የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ምርጫውን የሚያካሄደው ለአሜሪካ ወይም ለአምዕራባውያኑ ሳይሆን ለራሱ ነው:: መሪዋም ቢሆን የራሱ ህዝብ ሲወስንለት ብቻ እንጂ ሌላው አካል እንዲወስንለት የማይጠብቅ ስለመሆኑ ትምህርት ሰጥቶ የተጠናቀቀ ምርጫ ነው የነበረው::

ኢትዮጵያ በሰኔ 14 ቀን 2013 ምርጫ እንደምታካሄድ ቀን ቆጥራ ወደተግባራዊነቱ ስትገባ መጥተው ምርጫውን ለመታዘብ ፈቃደኛ መሆን ሳይችሉ የቀሩ የውጭ አገር ታዛቢዎች ምርጫው በሰላም መጠናቀቁን ሲያስተውሉ አንድ ቃል መናገር አልቻሉም:: የለመዱትን ያልተገባ ድርጊት ፈልገው ሲያጡ ለምርጫው የሚያወጡት ምክንያት ባለመኖሩ ባለመታዘባቸው እስከመቆጨት ብሎም እስከደማድነቅ ነው የደረሱት::

እኔ በዚህ ምርጫ የትኛውም ፓርቲ አሸነፈም ተሸነፈም እምብዛም ችግር የለብኝም:: ነገር ግን የምርጫውን ሂደት ስናስተውል የትኛውም ሰው ማንም ሳያስገድደው የራሱን ድምጽ ወጥቶ ሰጥቷል:: በቀጣይ ምርጫ ቦርድ የቀረቡትን ቅራኔዎች በአግባቡ አስተውሎ የፍትህ አካሉም አግባብነት ያለውን ፍርድ እያስቀመጠ መሄድ ይጠበቅባቸዋል:: በተለይ ህዝብን ሊያሳምን የሚችል ውሳኔ መስጠት የሚገባ ይመስለኛል::

ይህን ደግሞ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ማሳየት ችለዋል፤ ለምሳሌ በእርስ ቤት ውስጥ ካሉ የተወሱ የፓርቲ አባላት ጭምር በምርጫው እንዲወዳደሩ በመደረጉ ዳኝነቱ እውነቱ ወዳደላውና ህዝቡ ወደሚፈልገው ግብ እየሄደ ነው የሚያስብል ደረጃ ላይ መገኘቱን አመላካች ነው:: ይህ በኢትዮጵያ የዳኝነት ስርዓት የታየ ጥሩ ምልክት ነው:: ይህ ጅማሬ ብቻ ነው:: ነገር ግን ስር መስደድ አለበት:: ትልቁ ብልሽት የነበረው የዳኝነቱ ጉዳይ ነጻ አለመሆን ነው:: ፍትህ ያጣ ህዝብ ሁልጊዜ ማንን መምረጥ እንዳለበት አያውቅም፤ ከመረጠም ድምጼ ይከበርልኛል ብሎም አያምንም::

ስለዚህ በዚህ መንገድ ምርጫን ማስኬድ እና ዳኝነቱም ፍትህ ለጎደለው ብሎ ሽንጡን ገትሮ በመቆም ለፍትህ ያለው ተነሳሽነት ማሳየት ተስፋ ሰጪ እንዲሆን አድርጎናል:: የውጪዎችም ቢሆኑ እኛ ምርጫውን መጥተው እንዲታዘቡ የመጋበዛችን ምስጢር የእነሱን እውቅና እና የእነሱን ይሁንታ የመፈለግ ጉዳይ አይደለም:: ከየትኛውም አገር ለመታዘብ ይምጣ እኛ የምናካሄደው ምርጫ ለአገራችን ህዝብና ለኢትዮጵያ ለራሷ ነው የሚል እምነት የተፈጠረበት ጊዜ ላይ ደርሰናል:: መቼም አገራችን ባለፉት ጊዜ ውስጥ በፈተና ውስጥ ነበረች:: በፈተና ውስጥ መሆናችን ደግሞ አሸንፈን እንድንሻገር የሚያደርገን ኃይል የሚያስታጥቀን ይመስለኛል:: በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ትልቅ ተስፋም ውጤትም እያየን ነው::

አዲስ ዘመን፡– ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫውን በማስመልከት የሚዲያ አካላትን ባመሰገኑበት 

መድረክ ላይ በቀጣዩ ፓርላማ የሚታደም ከአንድ አይነት ይልቅ የተዥጎረጎረ ፓርቲ ቢሆን ደስተኛ ነኝ ብለው ነበር፤ 

እርስዎ ይህን አባባላቸውን እንደምን ያዩታል?

አቶ አባተ፡ እኔ እንደሚመስለኝ በዝግጅቱ ላይ በጣም ብዙ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች አሉ እንጂ በጣም ሰፊ ስራ የሚቀራቸው ይመስለኛል:: ውጤት በጸሎት አይገኝም፤ ውጤት በስራ እንጂ በምኞት አይመጣም:: እንደሚታወቀው ቀደም ሲልም አይነት አተያይ ያለው አካል ነውና ያለው ፓርላማን በጉጉት ሊከታተለው የሚችለው አካል ብዙም የለም:: እንዲህ ስል ልክ እንደ አንዳንድ አገሮች ፓርላማ ውስጥ አምባጓሮ ይፈጠር ማለቴ አይደለም:: በፓርላማ ውስጥ የሐሳብ ልዩነት ሊኖር ይገባል፤ አንደኛው ዘንድ የጎደለ ነገር በሌላው ሐሳብ አመንጪነት ሊሞላ ይችላል:: በዚህም አካሄድ አገርን የመገንባት እድል ይሰፋልና ሁላችንም ተጠቃሚዎች እንሆናለን::

አሁንም በቀጣይ የምንሰማው ውጤት የአንዱ ብቻ ጫፍ ላይ የሚወጣ ከሆነ ውጤቱን መቀበል አንድ ጉዳይ ሆኖ በተለይ ተፎካካሪዎች ቀጣይ መስራት ያለባቸው የቤት ስራ ላይ ማተኮር የሚጠበቅባቸው:: ፓርቲዎች በቁጥር ከመብዛት ይልቅ የሀሳብ ተመሳስሎ ወዳለው በመግባባት አንድነት መፍጠር ጥሩ ነው:: ህዝብ የሚመርጠው አስተሳሰብን ነው:: በአገራችን ያለው የፓርቲ ቁጥር ብዛት የዚያን ያህል መለጠጥ ያለበት ነው ብዬ አላምንም፤ እስከ 40 ያህል የደረሰው ፓርቲ ግፋ ቢል ወደ ሶስት መፈረጅ የተገባው ነበር:: ልክ ባልኩሽ መልኩ ተደራጅተው ቢሆን ኖሮ ወደፓርላማ የመግባቱ ሁኔታ አሁን ካለው ይልቅ እድሉ የጎላ ይሆናል::

ፓርቲዎች ሲበዙ የሚያገኙት ውጤት ደግሞ በተቃራኒው በጣም አነስተኛ ነው የሚሆነው:: በመሆኑም ፓርቲዎች በሚያቀራርባቸው ጉዳይ ላይ ተቀራርበው  ለመስራት ፍቃደኞች የማይሆኑ ከሆነ በዚህ መልኩ በሚደረገው ጉዞ ከምኞት ያለፈ የፓርላማ ስብጥርና ውበት ልናይ አያስችለንም:: በእርግጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምኞት መልካም ነው:: ከዚህ ምኞት ተፎካካሪዎች በዚህ ዓመት ምን ትምህርት አገኘን ብለው ማስተዋል ያለባቸው ይመስለኛል:: አሁንም ልዩነትን እያሰፋን ነው ወይ መሄድ ያለብን ወይም ተቀራርበን በመስራት ብልጽግናን መፎካከር አለብን የሚለውን ማጤን ያለባቸው ይመስለኛል::

እውነት ለመናር ዝም ብለን ስያሜውን እየሰጠናቸው ነው እንጂ ፓርቲዎቹ ተፎካካሪዎች አይደሉም:: አስርና ሃያ መቀመጫ ላይ ተወዳድረው ተፎካካሪ ሊባሉ ነው እንዴ! ተፎካካሪ ሲባል ሜዳው እኩል እስከሆነ ድረስ ባለጋራውን መገዳደር የሚያስችለው አቅም ያለው መሆን አለበት:: በአሁኑ ሰዓት ተፎካካሪ ከመባል ይልቅ ለተወሰነ ጊዜ ታዳጊ የሚል ወይ ሌላ አቻ ስም ተሰጥቷቸው እስከ አምስት ዓመት ጊዜ ይቆዩና ራሳቸውን አሳድገው ተፎካካሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን ባህሪ ይዘው ቢመጡ ነው የሚሻለው:: ገዥው ፓርቲም በበኩሉ ሁሉንም ነገር አልጋ በአልጋ አድርጓል ማለት አይቻልም:: ለተፎካካሪ ፓርቲ ምን ያህል ምቹ ሜዳ አዘጋጅቻለሁ ብሎ ራሱን መጠየቅ ያስፈልጋል፤ በሌለ ሜዳ ለምን አልሮጣችሁም ሊል አይገባም::

አዲስ ዘመን እስካሁኑ የምርጫው ጊዜያዊ ውጤት ይነገር እንጂ ገና ጳጉሜን ውስጥ የሚደረግም ምርጫ

 በመኖሩ አሸናፊው ቁልጭ ብሎ አልተለየም፤ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ተሸናፊውም ሆነ አሸናፊው ውጤቱን እንዴት ነው መቀበል ያለበት ይላሉ?

አቶ አባተ፡ ተፎካካሪዎችም ይሁኑ ገዥው ፓርቲ በቀጣይ ከሁለት ወር በኋላ ለሚደረገው ምርጫም ቢሆን ችግሮችን ለይተው ለመፍታት መሞከር እና ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል:: በሂደት የተፈጠሩትን ችግሮች በሚቀርፍ መንገድም ስራ መስራት ያለባቸው ይመስለኛል:: ጎልተው የነበሩ ስህተቶች በውጤት ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሊሆኑም ይችላሉ:: ዞሮ ዞሮ ግን አሸናፊ ካለ ተሸናፊ አለ ማለት ነውና ተሸናፊውም ለአሸናፊው መልካም ምኞት ሊመኝ ይገባል::

ተሸነፈ ሲባል ግን ነገሮች አበቁ ማለት እንዳልሆነ መረዳት ተገቢ ነው:: አሸናፊው ስለተፎካከርከኝ አጠቃሃለሁ ወይም አስርሃለሁ በሚል ማሰብ የለበትም:: የተሸነፈው ደግሞ እድሌን ሞክሬያለሁ ከዚህ በኋላ በቃ ማለት የለበትም:: አገር የጋራ እንደመሆኗ አገርን የመገንባት ተልዕኮ በጋራ መውሰድ አለበት:: ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ አብሮ ለመስራትና በጣም ትልልቅ ፖሊሲዎች ላይ ድርሻ እንዲኖራቸው የማድረግ ሁኔታ ቢኖር መልካም ነው:: ተሸናፊውም ከአሸናፊው ጋር አብሮ የሚሰራበት ሁኔታ መፈጠር አለበት:: በሚጎድል ነገር ላይ መተጋገዝ ቢኖር መልካም ነው::

በተለይ በዚህች አገር ዙሪያ በብዙ መልኩ ጠላት አለና ይህን ጠላትም በጋራ ለመመከት ተሸናፊው ከአሸናፊው ጎን መራቅ የለበትም:: በሜዳው ፊትና ኋላ መሰለፍ ካልሆነ በስተቀር አገር የጋራ ነውና በጋራ መሰለፍ የሚለውን አስተሳሰብ መገንባት ያስፈልጋል፤ በዚህ አገባብ መሰለፉ የተሻለ ነው::

አዲስ ዘመን፡– ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ከቀናት በኋላ በሚያስብል ደረጃ ሁለተኛው ዙር ውሃ የመሙላቱ

\ ሂደት ይኖራል ተብሎ ይገመታል፤ ይሁን እንጂ ምዕራባውያኑ፣ የአረብ ሊግም ሆነ አሜሪካ የግብጽን ትርክት

በመስማት የተለያዩ ጫናዎችን ሲያሳድሩ ይስተዋላልና ከዚህ አንጻር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ አባተ፡ ስለህዳሴ ሲነሳ በግሌ የማሰበው ነገር አለ፤ የራሳችንን ሀብት እስካሁን ባለመጠቀማችን ሲቆጨን መክረሙ አንሶ አሁንም አትጠቀሙ በሚል ለገዛ ንብረታችን ባለቤቱ ሌላ አካል ለመሆን ሲጥር እና ወደዓለም አደባባይ ጉዳዩን ይዞ በመሄድ ሲከራከር ሳይ በእጅጉ ያበሳጨኛል:: የውጪው ኃይል ደሃና ሀብታም አገር በሚል በፈረጀው አካሄድ ሁልጊዜ ኢ-ፍትሃዊ ዓለም ውስጥ መኖራችን የሚያበሳጭ ነገር ነው:: የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ ማን እንደሆነች ባላፈው ካካሄድነው ምርጫ የተረዱ ይመስለኛል:: በምርጫው ወቅት ብዙ ቀውስ ይፈጠራል በማለት ያለሙ አካላት ከምርጫው ሰላማዊነት በርካታ ነገር ሊማሩ ይችላሉ የሚል አተያይ አለኝ:: የአባይ ወንዝ በተፈጥሮ የተቸርነው ሀብታችን ነው:: ነገር ግን ይህን ውሃ በፍጹም መንካት የለባችሁም በሚል በቤታችን ገብተው እንዳሻው ለማድረግ ምንም አይነት ስልጣን የላቸውም:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰብዓዊ መብት ወይም እገዛ ብለው ምንም እንዳልተፈጠረ ሲጮኹ ደግሞ የሚያስገርም ነው::

አባይ የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ምድር ነው፤ እስካሁን ወደአገራቸው ሲፈስ የነበረውን ውሃ ካሳ ግብጾችን ማስከፈል ሁሉ ተገቢ ነበር:: ኢትዮጵያውያን ከመብራት እጦት የተነሳ የምንኖረው በጨለማ ውስጥ ሆኖ ሳለ አሁንም በጨለማው ውስጥ ይኑሩ ማለቱ አግባብ አይደለም::

እነርሱ ከዚህ ቀደምም እርስ በእርሳችን በማዋጋት ከልማቱ ውጭ ለማድረግ ነው ፍላጎታቸው:: በእቅድም ይዘው አንዱን ክልል ከሌላው ጋር ለማጋጨትና በዚህ መካከል የኢትዮጵያ አቅም ለማዳከም ነው ጥረታቸው:: ይህ አጀንዳ ዛሬም ይሰራል ብለው የሚያስቡ አካላት አሉ:: ይህ ግን ስህተት ነው:: ስለዚህ እኛ ኤሌክትሪክ የማምንጨትና አገራችንን ከጨለማ የማውጣት መብት አለን:: የማንንም ንብረት አልነካንም፤ ባለን የውሃ ሀብት መጠቀም ግን መብታችን ስለሆነ እያደረግን ያለነው ይህንኑ ነው:: እነግብጽ ሲያደርጉ የነበረው አካሄድ አ-ፍትሃዊ ነው:: እኛ ደግሞ ያንን መንገድ አንከተልም:: ኢ-ፍትሃዊነትን በፍትህ እየተካን ስራችንን እንቀጥላለን:: ጠላት በበረታ ቁጥር ህብረታችን ደግሞ እየጠነከረ ከበፊቱ ይልቅ አንድነታችን እየጨመረ ይመጣል:: በመሆኑም ሁለተኛው ዙር ውሃ ይሞላል፤ በዚህ ዓመትም የብርሃን ጭላንጭል በማየት የመጀመሪያውን የብርሃን የምስራች እናጣጥማለን ብዬ አስባለሁ:: ምርጫውን በስኬት እንዳጠናቀቅን ሁሉ ሁለተኛውንም ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እናከናውናለን::

አዲስ ዘመን፡– እርቀ ሰላምን በተመለከተ ብሄራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ከተቋቋመ ብዙ ጊዜ አስቆጥሯልና

 አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? አንዳንድ ስለሰላም ያገባኛል የሚሉ አካላት መታረቅ ያለበት መንግስትና ህዝብ ነው ይላሉ፤ ይህንንስ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ አባተ፡ እንደዚህ አይነት ኮሚሽን በዓለም እስከ 40 በሚደርሱ አገራት ተቋቁሟል:: ለምሳሌ ብሄራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ካቋቋሙ የአፍሪካ አገራት መካከል ብንወስድ እንደ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ እኛም የደቡብ አፍሪካንና የኬንያን ልምድ መቀመር ችለናል::

እንዲህ አይነት ኮሚሽን ሲቋቋምና ወደ ተግባር ሲገባ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ህዝቦች ያለፈ ትርክት የሚያቃርናቸው ከሆነ እሱ አይነት ትርክት እንዲያቆሙ ለማድረግ የሚረዳ ነው:: እርቀ ሰላም ሲባል ያለፈውን ትተን በሽግግር ፍትህ አማካይነት ወደተሟላ ቁመና እና ርዕይ መሻገር ማለት ነው::

ህዝብ በቋንቋው፣ በኃይማኖቱና በባህሉ ክፍፍል ሳይደረግበት የጋራ አገሩን በጋራ እንዲገነባ ማስቻል ነው:: ያለፈውን ትርክት የሚረሱበት ወይም ባለፈው ትርክት ላይ የተመሰረተን ቂምና ቁርሾ የመፍታት ስራን የሚያከናውን ነው ማለት ነው::

ኮሚሽኑ የሚሰራው የሽግግር ፍትህ ነው፤ ነገር ግን በዚህ ሽግግር ወቅት ደግሞ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጠሙን:: አንድም ለእርቀ ሰላም እንቅፋት የሆነው ነገር በሂደት እያየናቸው የመጣነው የህዝቦች መፈናቀል፣ የእርስ በእርስ ግጭት፣ ጦርነቱ፣ የህዳሴ ግድቡ ላይ ያለው ጫና እና ሌላም በርካታ ጉዳዮች በዚህ በሽግግር ጊዜ ያጋጠሙን ፈተናዎች ናቸው::

እንዲያም ሆኖ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በኮሚቴዎች ተደራጅቶ በሁሉም ክልሎች መቼ ምን አይነት ችግር እንደተፈጠረ፣ የማህበረሰባችን አገር በቀል እውቀት ምንድን ነው፤ የት ቦታ ምን አይነት እውቀት አለ የሚል ጥናት አካሂዷል:: በአገር አቀፍ ደረጃም የትውልድ ተሻጋሪ ሰላምን የመፍጠር አጀንዳዎችን አገራዊ አድርጎ የተለያዩ ስብሰባዎችን አካሂዷል::

አብዛኛውን ጊዜ ችግርን የሚፈታው ብሄራዊ ውይይት ነው:: በመሆኑም ተቀራርበው እንዲወያዩና ለመወያየትም እንዲቀራረቡ የማድረግ ስራዎችም ሰርቷል:: ይህ በእርግጥ ዋና ስራው አይደለም:: ነገር ግን የዋና ስራው መንገድ መጥረጊያ ስራው ነው:: ህዝብን ከህዝብ ማወያየትና ህዝቡን ራሱ የመፍትሄ አካል አድርጎ ማንቀሳቀስ እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ አገራችንን በሚመለከቱ አጀንዳዎች ላይ በግልጽ እንዲወያዩ የማድረግ ስራ ነው እየተሰራ ያለው::

ከሰሞኑን ደግሞ ዓመታዊ ግምገማችንን ያካሄድን ሲሆን፣ በቀጣይ 2014 ላይ ወደ ህዝቡ እንደርሳለን:: አንድ ትልቅ አገራዊ የእርቅ ማዕድ እናዘጋጃለን፤ ይህም ሁሉንም ማህበረሰብ የሚያሳትፍ ይሆናል:: ይህ አይነቱ አካሄድ የአንድ ጊዜ ክስተት ብቻ አይደለም፤ እርቅ ተሻጋሪ ስርዓት ነው:: ደግሞም የጀመረው ኮሚቴ የሚጨርሰውም አይደለም፤ የሚቀጥል ነው:: በቀጣይም በሚሰራ ስራ ድልድይ ማበጀት ያስፈልጋል:: የዚህ ድልድይ አገልግሎትም አዲሱን ትውልድ እና ቀደም ያለውን ትውልድ በማገናኘት አሻጋሪ ማድረግ ነው::

የሚያስታርቀው ወጣቱንም ጭምር ነው፤ ቀደም ሲል በዩኒቨርስቲዎች ያሉ ተማሪዎች ላይ ኮሚሽኑ ሰፊ ስራ ሰርቷል:: በኢትዮጵያ ባሉ በ45ቱም ዩኒቨርስቲዎች ሁሉ በሚያስብል ደረጃ ወጣቱ ኃላፊነት እንዲወስድና ሰላምና እርቅ ለምን እንደራቀ ግንዛቤ በመውሰድ የየድርሻውን እንዲወጣ ማወያየት ተችሏል:: ወጣቱ እንዲወያይ የተፈለገበትም ምክንያት ሁልጊዜ እነሱን ሊጠቀም የሚችል አካል በመኖሩም ነው:: በመሆኑም ከጉዟቸው የሚያሰናክላቸውን የጠላትን አሰላለፍ ለይተው የጋራ መፍትሄ ማበጀት እንዲችሉም ጭምር ነው::

አዲስ ዘመን፡– በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ ችግሮችና ፈተናዎች ናቸው የኮሚሽኑን ስራ ያዘገዩት ብለዋል፤ 

ነገር ግን ይህ ችግር ኮሚሽኑን ይበልጥ አጣድፎ ወደስራ በማስገባት መፍትሄ እንዲያመጣ ማድረግ ሲገባው ዘግይቷልና የዘገየበት የተለየ ምክንያት ምን ይሆን?

አቶ አባተ፡ አንድ ነገር አለ፤ ለተቀማጭ ሰማዩ ቅርቡ ነው እንዲሉ፤ መሬት ላይ ያለው አካል ላይ ያለውን እሱንም ያንንም አውርድ ይላል፤ ላይ ያለው ግን የወጣበት መስላል መርገጫውን፤ የት ላይ መያዝ እንዳለበት በብልሃት መሄድ ስላለበት ማስተዋል ይጠበቅበታል:: ኮሚሽኑ መስራት የሚገባውን እየሰራ ነው ያለው::

ቀደም ብዬ እንዳልኩት የዚህች አገር ፈተናዎች ሁሉ በእርቀ ሰላም ኮሚሽን ላይ ነው የሚንጸባረቀው:: አንድ ቦታ ሄደሽ ነባሩን ችግር ለመፍታት ስትጀምሪ አዳዲስ ችግሮች ይፈጠራሉ:: በዚህ አይነት ወቅታዊ ግጭቶች ላይ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ምንም ማድረግ አይችልም:: ያ ግጭት ሰራዊት ገብቶ ተረጋግቶና መልክ ይዞ ካልሆነ ችግር ነው:: ለምሳሌ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ አጣዬ ወይም ሌላው አካባቢ የተነሳው አይነት ግጭት በተነሳበት ቦታ ኮሚሽኑ ገብቶ ከመስራቱ በፊት ቦታ አካባቢው ሊረጋጋ ይገባል:: እንደሚታወቀው ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመት ውስጥ ያልተተራመሰ ቦታ ብዙም የለም:: ስለዚህ ኮሚሽኑ ቦታው ከተረጋጋ በኋላ ነው ወደህዝቡ ገብቶ ስራውን መስራት የሚችለው:: በመሆኑም በዚህ መልክ አንዳች ተስፋ ሳንቆርጥ ነው መስራት ያለብን:: ምንም እንኳ ተግዳሮቱ በዝቶ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ ቢታይም መቼም ቢሆን ግን እኛ ተስፋ አንቆርጥም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ እንደሚታረቅ በጣም እርግጠኞች ነን::

አዲስ ዘመን፡– ለማስታረቅ እየተደረገ ያለው ህዝብን ከህዝብ ነው ወይስ መንግስትን ከህዝብ ነው?

አቶ አባተ፡ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው:: በእርግጥ ህዝብ ሁልጊዜ ተጣልቶ አያውቅም:: ወደህዝቡ ስትቀርቢና ስታዳምጪ አንዳንዴ ህዝቡ በመሪዎቹ በተፈጠረው ችግር ህዝብን ስንወቅስና በህዝብም ላይ ድንጋይ ስንወረውር ነው የቆየነው:: ምክንያቱም ህዝብ ከህዝብ ጋር ተጣልቶ አያውቅም:: ነገር ግን ማን እንዳጣላቸው? መቼ ምን ተሰርቶ እንደተጣሉና መሰል ነገሮችን እውነታ ማውጣት ነው የኮሚሽኑ ስራ:: ያ ያጣላቸውን አካል እንዲያወግዙና የሚያጣላቸውን ድልድይ በማፍረስ እንዲቀራረቡ የማድረግ ነው:: ዞሮ ዞሮ ችግር እንዲፈጠር ባደረገው አካል ምክንያት ህዝብ ተጣልቷል:: ምክንያቱም ከዚህ መልስ የእኔ ነው እንጂ የአንተ አይደለም በማለቱ ተቀያይሟል፤ መሬቱን እንዲፈልገው ያስደረገውና አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ አጀንዳ የሰጠው አካል ግን ሌላ ነው:: ህዝቡ አጀንዳ የሰጠው ማን እንደሆነ ካወቀ በኋላ ግን በመሬቱ ላይ ማንም ቢጠቀም ጥቅሙ የጋራ ነው፤ ፈጣሪ የሰጠን የተፈጥሮ ስጦታ ነው ማለት ይጀምራልና ይህን ነገር ነው ማጥራት ያለብን::

በዚህ መንገድ ወደህዝቡ ቀረብ ብሎ ታሪኩን ማጥናት ስንጀምር የማይፈታ ችግር እንደሌለ ማረጋገጥ ችለናል:: የማንም ተጨማሪ እገዛ እንኳ ሳያስፈልግ አገር በቀል በሆነ እውቀት ተመርተው አንዱን ከሌላው ማስታረቅና ማግባባት የሚችሉ የእዛው አካባቢ ሽማግሌዎች ያሉትን ችግሮች ራሳቸው ብቻቸውን መፍታት ይችላሉ::

 አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐምሌ  1/2013


Exit mobile version