የቡድን ሰባት ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሲሰጡ እግረመንገዳቸውን ኢትዮጵያን አስመልክቶ በበጎ ጎኑንና በስጋት ከፍለው መግለቻቸው ላይ አክለዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩት ግጭቶች መቆሚያ ያጡ ውጥረቶች ” ይሳስበናል” ያሉት የጂ ሰባት አገራቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ግጭቶቹን ተንተርሶ የሚከተለው የኢኮኖሚ ቀውስና የዜጎች እንግልትን በስጋታቸው አካተዋል። የምግብ እጥረትንም አንስተዋል።
በጣልያኗ ካፕሪ ደሴት ሲያካሂዱ የሰነበቱትን ስብሰባ በቋጩበት ዕለት ባወጡት መግለጫ መንግስትና ህወሓት የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት የተወሰዱ እርምጃዎችን በቀና እንደሚያዩ አስታውቀዋል።
መንግስት “የሽግግር ፍትህ” በሚል አዘጋጅቶ እየሰራበት ያለውን አግባብ በሰብዓዊ መብቶች፣ በሰላማዊ ሰዎች ደህንነት ጥበቃ፣ ውጥረቶችን ለመፍታት በሚደረግ ፖለቲካዊ ውይይት፣ በዕርቅ፣ በብሔራዊ ውይይት፣ የሽግግር ፍትህ እና በግጭት ወቅት ወንጀል የፈጸሙ ተጠያቂ ለማድረግ፤ ተጨማሪ እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ አበረታተዋል። መንግስት ህጉን አርቅቆ ወደ ተግባር መግባቱ የሚታወስ ነው።
በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በመካሄድ ላይ በሚገኙ ግጭቶች የሚሳተፉ ወገኖች፤ በንግግር ሰላም ለማውረድ ተመሳሳይ ቁርጠኝነት እንዲኖራቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሌላ መንገድ እየታገሉ ይገኛሉ ያላቸው አካላት ወደ ምክክር መድረኩ እንዲገቡ በያዝነው ሳምንት ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል። ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡ ቢታወስም፣ አሁንም ” ወደ ምክክር መድረኩ ኑ ” ያለው ኮሚሽኑ ፤ ለታጠቁ አካላት ተገቢውን የጥበቃ ዋስትና በኮሚሽኑ እንደሚያመቻች ገልጿል። ይህ የተሰማው በምክክር ጉባዔው የሚሳተፉ የኦሮሚያ ክልል ማህበረሰብ ተወካዮች የማጠቃለያ ልየታ መድረክ በሻሸመኔ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ነው። በርካታ አገራትም ኮሚሽኑንን እንደሚደግፉ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
በግጭት የተጎዱ ማህበረሰቦች በማገገም እና መልሶ ግንባታ፣ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ በመበተን እና መልሶ በማዋሀድ እንዲሁም ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በማበጀት ከተገኘው ሰላም በአፋጣኝ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያሻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በመግለጫቸው አሳስበዋል።
የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መግለጫ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ከአራት ወራት ገደማ በፊት የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ጉዳይ ጭምር ያነሳ ነው። የመግባቢያ ስምምነቱ “እንደሚያሳስባቸው” የገለጹት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው የተፈጠረው ውጥረት እንዳይባባስ ሁሉንም የውይይት “ቻናሎች” ክፍት እንዲያደርጉ መክረዋል።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ እና በሁለትዮሽ መገናኛዎቻቸው ተጠቅመው፤ ከቀጠናዊ አጋሮቻቸው እንዲሰሩም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ አሳስበዋል። ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ልዩነታቸውን ለመፍታት የሚከተሉት አካሄድ፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር ከሰፈረው የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መርህ ጋር የተጣጠመ መሆን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።