Site icon ETHIO12.COM

የፖለቲካ ጨዋታውን አልቻልንበትም !

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በመታሰሩ እጅግ አዝኛለሁ። ሀዘኔ ጋዜጠኛው በመታሰሩ ብቻ አይደለም ይልቁንስ ፖለቲካችን ወደኃላ መራመድ በመጀመሩ እንጂ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን ወደ ስልጣን ያመጣው ለውጥ ከመጣ ወዲህ የዲሞክራሲ መብቶች ይበል በሚያሰኝ ደረጃ በሰፊው ናኝተዋል። የመገናኛ ብዙሃን ( በተለይም ኢንተርኔትን መሰረት ያደረጉት ) ያለ ገደብ በሚባል ደረጃ ተለቀዋል። ዜጎች ከማድ ቤት እስከ አደባባይ ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲናገሩ የፖለቲካ ሆደሰፊነት ተስተውሏል።

ነጻነት ከኃላፊነት ጋር ነው የሚመጣው። በጨቋኝ አገዛዞች የኖረው ህዝባችን ነጻነቱን ለማጣጣም ያለውን ጉጉት ያህል ተያይዞ የሚመጣውን ኃላፊነት ትኩረት ሲሰጠው አይታይም። ከልሂቅ እስከ ‘ ተራው ሰው ‘ አንጻራዊ ነጻነቱን የተጠቀመው እነርሱ የሚላቸውን ከእርሱ እምነትና አስተሳሰብ የሚለዩ ወገኖችን ለማጥቃት ነው። ሀገሪቱ በግጭት ስትናጥ የከረመችው በመንግስት ቸልታና አቅም ማጣት ብቻ አልነበረም ዜጎች የጥላቻ ፖለቲካ ውስጥ ቡድንና ወገን ለይተው በመሳተፋቸውም ጭምር እንጂ።

መንግስትን የሚመሩ ሀይሎች ከህዝብ ውስጥ የወጡ ናቸው። እንደተቀረው ኢትዮጵያዊ በጭቆናና እመቃ ውስጥ ያደጉ ልዩነትንም በዚሁ መልኩ የምፍታት ልምምድ ያላቸው። ለውጡ ሲመጣ ለጋዜጠኞች ፣ ሰብአዊ መብት ተሟጓቾችና ፖለቲከኞች ሹመኞቹን ከማስደንበር ይልቅ በብልሀት የዲሞክራሲ ሽግግሩን እንዲያስኬዱ ስንመክር ቆይተናል። ብዙዎች የመረጡት ግን ‘ የማስደንበርን ‘ ፖለቲካ ነው። የማስደንበር ፖለቲካ ደግሞ ሁላችንንም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ‘ እንዘጭ እንቦጭ ‘ ሲሉ ወደሚጠሩት የዜሮ ድምር ሂደት zero sum game ብቻ ነው የሚከተን።

የእነ ተመስገን ደሳለኝ መታሰር ፖለቲካችን ወደኃላ እየሄደ እንዳለ ጽኑ ማስረጃ ነው። ለዚህ የቁልቁለት ጉዞ ደግሞ የሁላችንም ድርሻ አለበት። ፍለጠው ቁረጠው ሲል ከሚውለው ተራ ዜጋ አንስቶ ፣ እስከ ወገንተኛው ሚዲያና ራሱ መንግስትም ጭምር።

ቆም ብሎ ለማሰብ አሁንም ጊዜው አልረፈደም !

Samson michalovich opinion

Exit mobile version