Site icon ETHIO12.COM

በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ከሚሰራጩ የጥላቻ ይዘቶች አንጻር የቲክቶክ ቸልተኝነትና ዝምታ

ግንቦት 15፣ 2015 ዓ.ም

የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋትን እና የተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ማሻቀብን ተከትሎ ከተከሰቱ አሉታዊ ውጤቶች መካከል የጥላቻ ንግግር በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ነው።

ምንም እንኳ አሉታዊ ውጤቱ ዓለም አቀፍ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዝቅተኛ የሚዲያ አጠቃቀም ንቃት እና ያልተረጋጋ ሀገረ መንግስት ባለባቸው አገሮች መሬት ላይ ወርዶ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍ ያለ መሆኑ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ታይቷል።

በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጭ የጥላቻ ንግግርን ከመዋጋት አንጻር አገልግሎቱን የሚሰጡ ኩባንያዎች ግዴታ እንዳለባቸው በውስጥ ደንቦቻቸው እና በፖሊሲዎቻቸው ሰፍሮ የሚታይ ነው።

ከዚህ አኳያ አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎች ግዴታቸውን ለመወጣት በመጠኑም ቢሆን ሲንቀሳቀሱ የሚታዩ ሲሆን በአንጻሩ ሌሎቹ ፕላትፎርማቸውን ለጥላቻ ሰባኪዎች ልቅ ማድረጋቸውን መመስከር ቀላል ነው።

በዚህ ረገድ ቲክቶክን በምሳሌነት ማቅረብ ይቻላል።

ኢትዮጵያ ቼክ ባደረገው ክትትል እንደታዘበው በኢትዮጵያ ቋንቋዎች በቲክቶክ ከሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች የብሔርንና የሃይማኖት  ማንነትን መሰረት ያደረጉ ይዘቶች ጎላ ብለው ይታያሉ።

የጥላቻ ንግግሮቹ ግልጽ፣ የማያሻሙ፣ ተደጋጋሚ፣ ጫፍ የረገጡና የማህበረሰቡን ግንኙነት የበለጠ የሚያሰልሉ ብሎም ግጭት የሚጋብዙ መሆናቸን መናገር ይቻላል።

ይዘቶቹን ከሚያሰራጩ አካላት መካከልም በርካታ ተከታዮች ያላቸው እና በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያ ዎች እግድ የተጣለባቸው በዛ ብለው እንደሚገኙ መመስከር ይቻላል።

እንዲህ ያሉ አሉታዊ ይዘቶች ከጠቃሚዎች ምርጫና ፍሎጎት በተቃራኒ በፕላትፎርሙ አልጎሪዝም ግብዣ ‘ለእርስዎ’ (For You) ተብለው መቅረባቸውም የተለመደ መሆኑን መታዘብ ችለናል።

በተጨማሪም በቲክቶክ የፍለጋ ቁልፍ (Search Engine) አማካኝነት የሚገኙ ውጤቶችም የጥላቻ ንግግር የሚገኝባቸውን ይዘቶች ማቅረባቸው የተለመደ መሆኑን አይተናል።

ለምሳሌ ‘አማራ’፣ ‘ኦሮሞ’ ወዘተ ያሉ የተለየ ቡድን መጠሪያዎችን በፍላጋ ቁልፉ ቢጭኑ የጥላቻ ይዘት ያላቸው ቪዲዮዎች ተሰባጥረው ሊመጡ ይችላሉ።

የቲክቶክ ደንብና ፖሊሲ እንደሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎች ሁሉ ደንበኞች ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ሲጠቀሙ ብሔርን፤ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም ሌሎች የተለዩ ቡድኖችን መሰረት በማድረግ ጥላቻ የሚያስፋፋ ንግግር ማድረግን የሚከለክል ቢሆንም ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው በፕላትፎርሙ የሚታየው ሃቅ ግን ከዚህ የተለየ ነው።

አሉታዊ ድርጊቱ እየሰፋና እየተደጋገመ መሄዱ የአደባባይ ሚስጥር ቢሆንም ይህ ነው የሚባል እርምጃ በኩባንያው በኩል ሲወሰድ አላየነም።

አንዳንድ አገሮችና የበይነ መንግስታት ተቋማት እንዲህ ያለው የቲክቶክን ቸልተኝነት ባለመታገስ ጠበቅ ያሉ እርምጃዎችን መውሰድ የጀመሩ ሲሆን የአውሮፓ ህብረትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።

ህብረቱ ቲክቶክን ከጥላቻ ንግግር አንጻር የስነምግባር ደንብ (Code of Conduct) ያስፈረመው ሲሆን ይህም ኩባንያው በአባል አገራቱ ጥብቅ የክትትልና የቁጥጥር ስርዐት እንዲተገብር አስገድ ዶታል።

እንደፓኪስታን ያሉ አገራት በበኩላቸው በፕላትፎርሙ ላይ ተደጋጋሚ ዕቀባ በመጣል አሉታዊ መልዕክቶችን በተመለከተ በአትኩሮት እንዲሰራ ጫና አድርገዋል።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ቲክቶክ የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር የሚያሳየው ቸልተኝነት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በተለይም የፕላትፎርሙ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ግንዛቤ ውስጥ ከገባ የሚያደርሰው ጥፋት የከፋ ይሆናል።

ethiopiacheck

Exit mobile version