Site icon ETHIO12.COM

ለኢንተርኔት ተጠቃሚ ወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ከሁለት አመት በፊት የተጀመረው የአሸዋ ሶሉሽን ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማህበር፤ ለሽያጭ ካቀረበው 200 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን መካከል 100 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉንም አቶ ዳንኤል በቀለ ገልጸው፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል የመፍጠር አላማንም ይዞ እየሰራ ነው።

አክሲዮን ማህበሩ በትናንትናው እለት “ሥራ ለሁሉም” የሚል ፕሮጀክቱን ይፋ አድርጓል። በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል በቀለ እንደተናገሩት፤ አሸዋ ሶሉሽን ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማህበር በቀጣይ አስር አመታት ለአምስት ሚሊዮን ሰው የስራ እድል የመፍጠር እቅድን ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ነው።

በትናንትናው እለት የተጀመረው ሥራ ለሁሉ የተሰኘው ፕሮጀክት ሰባት ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት በቅድሚያ 500 ፍላጎቱ ያላቸው የኢንተርኔት ተጠቃሚ ወጣቶችን፤ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎችን እና በኢንተርኔት ገበያ ላይ የተሰማሩ ሻጮችን ተሳታፊ እንደሚያደርግ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

አብዛኛው ወጣት ማህበራዊ ሚድያ አጠቃቀሙ ጤነኛ እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፤ የአሸዋ ሶሉሽን ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማህበር “ስራ ለሁሉም” ፕሮጀክት ግን የማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ ተጠቅሞ መስራት የሚችሉበትን እድል ይዞ መምጣቱንም ገልጸዋል።

የ“ሥራ ለሁሉም” ፕሮጀክት አላማ በዋናነት የኢንተርኔት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለገበያ የሚውሉ ምርቶችን ማቅረብ እንደሆነ ጠቁመው፤ ለማህበረሰቡም የሥራ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የሥራ ለሁሉም ፕሮጀክት ለጊዜው በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ሥራ የሚጀምር ሲሆን በቀጣይ የአዲስ አበባን ልምድ በመያዝና ፕሮጀክቱን በማስፋፋት ወደ ክልል ከተሞች የመሄድ እቅድ አለው።

በማህበሩ አማካኝነት የሥራ እድል ለሚፈጥርላቸው ወጣቶች የተለያዩ ማበረታቻዎችን እንደሚሰጥ የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፤ የስልክ የትራንስፖርትና ሌሎች ክፍያና ማበረታቻዎችን በማድረግ እንደሚደግፍም ገልጸዋል። አክሲዮን ማህበሩ አንድ ሚሊዮን ሚሊየነሮችን የመፍጠር ትልቅ ህልም ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑ ተነግሯል።

ከሁለት አመት በፊት የተጀመረው የአሸዋ ሶሉሽን ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማህበር፤ ለሽያጭ ካቀረበው 200 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን መካከል 100 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉንም አቶ ዳንኤል በቀለ ገልጸው፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል የመፍጠር አላማንም ይዞ እየሰራ ነው።

Exit mobile version